ዐቢይ ጾምና ሳምንታቱ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ?! የጾምን ወቅት እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? አባቶቻችን ሊቃውንት ስለ ጾም እንዲህ ይላሉ፤ ጾም ማለት ከምግብና ከውኃ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከክፉ ሥራም መታቀብ (መከልከል) ነው፤ ጾም የጽድቅ በር ናት፤ ጾም ለመልካም ነገር የምታነሣሣን ናት፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ከጸሎትና ከስግደት ጋር እንዲሁም ትምህርት በማይኖረን በዕረፍት ጊዜያችን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በማስቀደስ፣ ታዛዦች በመሆን የጾሙን ጊዜ ልናሳልፍ ይገባል፡፡ መልካም!

ባለፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ስለ ዐቢይ ጾምና በጾሙ ወቅት ስላሉት ሳምንታት እስከ እኩለ ጾም ድረስ ተመልክተናል፤ ለዛሬ ደግሞ ቀጥሎ ያለውን እንመለከታለን፤ መልካም ንባብ!!!

በዐቢይ ጾም ወቅት የሚገኘው አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል ጌታችን በደብረ ዘይት (ኢየሩሳሌም በሚገኘው) ተራራ በመጨረሻ ለፍርድ የሚመጣበት መቼ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ ሲጠይቁት ምልክቱን እንደነገራቸውና ጌታችን ለፍርድ እንደሚመጣ ተዘጋጅተን እንድንኖር ሰፊ ትምህርት የሚሰጥበት ሳምንት ነው፡፡ (ማቴ. ፳፬፥፩-፶፩)

ስድስተኛው ሳምንት ደግሞ ገብርኄር ይባላል፤ ትርጉሙም ‹ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ታማኝነት በምሳሌ ያስተማረበት ነው፤ በዚህ ሳምንት የመክሊት ትርጓሜ ከሰው ሕይወት ጋር እየተነጻፀረ በስፋት ትምህርት ይሰጥበታል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር፤ ወደ ሌላ ሀገር ሲሄድ እስኪመለስ ድረስ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሠርተው እንዲያተርፉበት አደራ ሰጣቸውና ሄደ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ተመለሰና አገልጋዮቹን ጠርቶ ከሰጣቸው መክሊት ትርፉን ሲጠይቃቸው አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው በርትቶ ሠርቶ አምስት አትርፎ ጠበቀው፤ ሁለት የተቀበለውም እንደዚሁ ሁለት አትርፎ ጠበቀው፤ አንድ የተቀበለው ግን ምንም ሳይሠራ ያቺኑ ደብቆ ቆየው፤ ከዚያም ሁለቱን ታታሪ ታማኝ አገልጋዮች አመሰገናቸው፤ በብዙ ኃላፊነት ላይ ሾማቸው፤ ምንም ሳይሠራ የቆየውነን ደግሞ ወቀሰው፤ ያለውም እንዲወሰድበት አዘዘ፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ጌታችን ይህን በምሳሌ ያስተማረው ብዙ ምሥጢር አለው፤ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠው ጸጋ (መክሊት) አለ፤ በዚያ በተሰጠን ነገር መልካም ሠርተን ልናተርፍበት ይገባል፤ በትምህርት ቤታችን በትምህርታችን ጎበዝ የሆንን ደከም የሚሉትን ልናግዛቸው ዕውቀታችንን ልናካፍላቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ ለሌሎች ልናካፍል ይገባልናል፤ መምህራን የሚሰጡንን ትምህርት በርትቶ በማጥናትና መጻሕፍትን በማንበብ ውጤታማ በመሆን ልንመሰገን ይገባል፤ መልካም ነገር በማድረግ ደካሞችን ማገዝ አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን ወደፊት ደግሞ ትልቅ ሰው ስንሆን በጎ ሥራዎችን እያበዛን እንሄዳለን፤ ከዚያም በጎ አገልጋይ፣ ታማኝ አገልጋይ እንባላለን፤ ለትልቅ ኃላፊነትም እንሾማለን፡፡  ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን እየሰማን፣ ቅዳሴ እያስቀደስን፣ እየጾምን፣ እየጸለይን፣ እየሰገድን በሃይማኖት፣ በምግባር ኖረን እንድንጠብቀው ታማኝ አገልጋይ በሚለው ሳምንት ትምህርቱ በሰፊው ይሰጣል፡፡

ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ኒቆዲሞስ መምህር የሆነ ማታ ማታ ጌታችን ዘንድ እየመጣ ይማር የነበረ ትጉህ ሰው ነው፡፡ (ዮሐ.፫፥፩-፳፩) ኒቆዲሞስ በአንድ ወቅት ወደ ጌታችን ዘንድ መጥቶ ሲማር ስለምሥጢረ ጥምቀት አስተማረው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ኒቆዲሞስ የተባለው መምህር ቀን የራሱ ሥራ ስለነበረበት ማታ ማታ ጊዜ አመቻችቶ በርትቶ ከጌታችን ዘንድ እየመጣ በትጋት በመማሩ ምሥጢር ተገለጠለት፡፡ በሕይወታችን በምናደርገው መልካም ሥራ ምንም ነገር ፈተና በዛብን ብለን ሳንሰንፍ ጊዜ እያመቻቸን በርትተን መማር እንዳለብን ከእርሱ ሕይወት ተሞክሮ እንማራለን፤ ቀን በዘመናዊ ትምህርት ብንቆይም ጊዜ አመቻችተን ደግሞ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ልንማር ያስፈልገናል፡ ፡ቤተ ክርስቲያንም ይህ ሳምንት ስለኒቆዲሞስ ትጋት (ታታሪነት) እና ስለ ምሥጢረ ጥምቀት ታስተምርበታለች፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ ጥምቀት አንዲት መሆኗን በስፋት የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ (ኤፌ.፬፥፭፣ ይሁ.፩፥፫)

ስምንተኛው ሳምንት ደግሞ ሆሣዕና ይባላል፤ ሆሣዕና ማለት በልዕልና ጸንቶ የሚኖር መድኃኒት ማለት ነው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፩-፲፪) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሲገባ ሕዝቡ ልብሳቸውን እያነጠፉ፣ ዘንባባ ይዘው እየዘመሩ ተቀበሉት፤ ሕፃናትም እየዘመሩ አመሰገኑት፤ ጌታችን በትሕትና በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌመም ከተማ ገባ፤ ልጆች ይገረማችኋል! የሁሉ ፈጣሪ ነውና ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ድንጋዮችም አመሰገኑት፤ በዚህ ቀን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን  ትሕትና፣ የሕፃናቱ ምስጋና፣ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ናት›› ብሎ ስለማስተማሩ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ እኛም ውለታውን አስበን በዚህ ዕለት ዘንባባ ይዘን ‹‹ሆሣዕና በአርያም ብለን እየዘመርን በዓሉን በድምቀት የምናከብርበት ነው፡፡

አያችሁ ልጆች! ጌታችንን ድንጋዮች እንኳ አመስግነውታል፤ ዘወትር ውለታውን እያሰብን በምንችለው አቅም ልናመሰግን ይገባናል፡፡ ትሑታን፣ ሰዎችን አከባሪ፣ በመሆን በቤተ ክርስቲያን አያገለገልን ልናድግ ይገባናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ለዛሬ በዚህ አበቃን፤ የመጨረሻው ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን ትንሣኤ ነው፤ በቀጣይ ትምህርታችን በዚህ ርዕስ እንማማራለን፤ አምላካችን ጾሙን ጾመን በረከት የምናገኘኝበት ያድርግልን፤ ለብርሃነ ትንሣኤው በቸርነቱ ያድርሰን!

ይቆየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!