እግዚአብሔር ባሕርያት  

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

መጋቢት ፲፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን!  እንኳን ለታላቁ ዐቢይ ጾም አደረሳችሁ! በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርት መማርንም አትዘንጉ! ከምን ጊዜውም በተለየ መልኩ በጸሎት መትጋት አለብን ዕድሜአችን ከሰባት ዓመት በላይ የሆነን እየጾምን ነው አይደል! መልካም!!!

ግን ልጆች ከሰባት ዓመት ጀምሮ ለምን መጾም እንደሚጀመር እናስታውሳችሁ! አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን እግዚአብሔር ከፈጠራቸው በኋላ በገነት አኖራቸው፤ ለሰባት ዓመት በገነት ከተቀመጡ በኋላ ሰይጣን አሳሳታቸውና አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በልተው ከገነት ተባረሩ፤ ስለዚህም ክርስቲያን የሆነ ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ እንዲጾም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ታዟል፡፡ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፡፡ ባለፈው “ሀልዎተ እግዚአብሔር” በሚል ርእስ ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የእግዚአብሔር ባሕርያት ምን እንደሆኑ እንማራለን!-

ባሕርይ ማለት የፍጥረት ሁሉ ጥንት ሥር፣ አኳኻን፣ ሁኔታ፣ ጠባይ፣ ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፬፻፺፫)

የእግዚአብሔር ባሕርያት የምንላቸው ደግሞ ምን ምን እንደሆኑ እንማራለን፡፡ ባሕርይ ስንል የራስ የሆነ መገለጫ ማለታችን እንደሆነም ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ እንግዲህ አምላካችን እግዚአብሔር የሚታወቅባቸውን ባሕርያት እንመልከት!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የእግዚአብሔር ባሕርይ በእኛ አእምሮ ተመራምሮ አይደረስበትም፤ በእኛም አንደበት የማይገለጥ ነው፤ እግዚአብሔር ለቅዱሳን አባቶቻችን በገለጠላቸው መጠን ብቻ እንመለከታለን፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ባሕርያት ብዙ ናቸው፤ አንዱ በሁሉ ቦታ የሚገኝ መሆኑ ነው፤ በቦታ አይወሰንም፤ በዚህ ቦታ ብቻ አለ አንለውም፤ ሁሉም ጋር አለ፤ ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ያስረዳናል፤ ‹‹…ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ፤ እንደ ንስር የንጋት ክንፍ ብወስድ እስከ ባሕር መጨረሻ ብበር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝህም ትይዘኛለች፡፡››         (መዝ.፻፴፱፥፯) አያችሁ ልጆች! ይህ ንጉሥ ዳዊት የተናገረው ኃይለ ቃል የሚያስረዳን እኛ ሰዎች መገኝት የምንችለው በአንድ ጊዜ አንድ ቦታ ብቻ ነው፤  ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ስንሄድ  በሁሉ ቦታ ያለ እግዚአብሔርን ያገኘናል፤ ምክንያም እርሱ በቦታ አይወሰንምና፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን ሁሉን ያስገኘና የፈጠረ እግዚአብሔር መሆኑን ተምረናል፤ ፍጥረትን ሲፈጥር የማንንም እገዛ አልፈለገም፤ ሁሉንም በጥበቡ በመፍጠሩ ጥበብም የባሕርይ ገንዘቡ ነው፤ ፍጥራት ሳይፈጠሩ ነበረ፤ አሁንም አለ፤ ወደ ፊትም ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ዘለዓለማዊ ነው እንለዋለን፤ በጊዜም ብዛት አይለወጥም፡፡ ለምሳሌ ልጆች! እኛ በየጊዜው ለውጥ ይታይብናል፤ አሁን ልጆች ነን፤ ከዚያ በጊዜ ሂደት ደግሞ እናድጋለን፤ እናረጃለን፤ ከዚያም ደግሞ እንሞታለን፤ ለውጥ ይታይብናል፤ እግዚአብሔር ግን አይለወጥም፤ ማርጀት፣ ማለፍ በእርሱ ዘንድ የለበትም፤ እንደገናም የማይታይ መንፈስ ነው፡፡ አንዳስሰውም፤ አናየውም፤ እርሱ ግን በወደደው በፈቀደው መልኩ ለቅድስና ሕይወት ለበቁ አባቶቻችን ይገለጥላቸዋል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ደግሞ የአምላካችን የእግዚአብሔር ባሕርይ የሆነው ሁሉን አዋቂ ነው፤ ሰዎች አንድን ነገር የምናውቀው ከሌላ ሰምተን ነው ወይም እግዚአብሔር ሲገልጥልን ነው፤ ለዚያውም ደግሞ እውቀታችን ውስን ናት፤ እግዚአብሔር ግን እውቀት የራሱ የሆነ ከማንም አላገኘውም፤ ሁሉንም ማድረግ ይቻለዋል፤ የሚሳነው አንዳች ነገር የለውም፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብሏታል፤ ‹‹…ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም …፡፡›› (ሉቃ.፩፥፴፯) እኛ ሰዎች እግዚአብሔር ካልረዳን  በራሳችን የምናደርገው አንዳች ነገር የለንም፤ የዓቅም ውስኑነት አለብን፤ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ቻይ ነው፡፡

ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ሲል መስክሮለታል፤ ‹‹…ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፤ አሳብህም ይከለከል፤ ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ…፡፡›› (ኢዮ.፵፪፥፪) እውነተኛ ዳኛ ነው፤ ለማንም አያዳላም ‹‹…እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፤ ኃይለኛም ታጋሽም ነው…፡፡›› (መዝ.፯፥፲፩)

እስኪ ልብ እንበል! እኛ በሰዎች መካከል ባለ አለመግባባት አስማሙ ብንባል ፍርዳችን ሊዛባ ይችላል፤ ለአንዱ ወገን እናዳላለን፤ እስኪ ለሰከንድ እናስብ፤ በጓደኞቻችን መካከል የተዛባ ፍርድን (ምስክርነትን) በማዳላት ሰጥተን የለ!፤ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰት እና አድሎ በእርሱ ዘንድ የለበትም፤ ሁላችንንም በምሕረት የሚመለከተን ይቅር ባይ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የአምላካችን ባሕርይ ከሆኑና ለቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን በጸጋ የሚሰጣቸው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፤ በቅዱስ መጽሐፍ ብዙ ቦታ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ ተጽፎልናል፡፡ መላእክትን፣ አባቶችን፣ እናቶችን ቅዱሳን ብለን ብንጠራቸው እርሱ በሰጣቸው በጸጋ ባገኙት ነው፤ እግዚአብሐርን ግን ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ‹‹…እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ…፡፡›› ( ዘሌ.፲፱፥፪)

አምላካችን እግዚአብሔር የማንንም ርዳታ አይፈልግም፤ ዘለዓለማዊ ነው፤ የማይለወጥ ነው፤ የማይታይ መንፈስ ነው፤ ሁሉን አዋቂ ነው፤ ጠቢበ ጠቢባን ነው፤ ሁሉን ቻይ ነው፤ ቅዱስ ነው፤ እውነተኛ ዳኛ ነው፤ መሐሪ ነው፤ እውነተኛ ታማኝ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሕይወታችን መልካም ነገርን በመሥራት ልንቀደስ ያስፈልጋል፤ ሐሰትን ከእኛ በማራቅ እውነተኞች፣ ታማኞች እና በማስተዋልና በጥበብ በመኖር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መግለጥ (ማስመስከር) አለብን፡፡ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!