‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› (፩ኛ ሳሙ.፱፥፮)

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ኅዳር፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ዓለም ፈጥሮ እንዲሁ የተወው አይደለም፡፡ በብዙ መንገድ ይጠብቀዋል፤ ያስጠብቀዋል፤ ያስተምረዋል፤ ይመክረዋል፤ ያስመክረዋል፤ በየዘመኑ እንዲሁ ሲያደርግ እንደኖረ እንረዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በአንድም በሌላም ይናገራል››  እንዲል መጽሐፍ እግዚአብሔር በተለይ የሰውን ልጅ ከፍጥረት አልቆ ከፈጠረው በኋላ መለኮታዊ ጥበቃ፣ መልአካዊ ጥበቃ እንዲሁም ሰዋዊ ጥበቃ እንዳይለየው አድርጎታል፡፡ (ኢዮ.፴፫፥፲፬)

ሰዋዊ ጥበቃ በነገሥታቱ፣ በካህናቱ እንዲሁም በነቢያቱ ምክር፣ ትምህርት፣ ተግሣጽና ጥበቃ ሥር አድርጎ በየጊዜው ከክፉ ነገር ጠብቆ አኑሮታል፤ እያኖረው ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በብሉይ ኪዳኑ ዘመን ከአባታችን አዳም ጀምሮ በየዘመኑ በትውልዱ ቅብብሎሽ ሕዝቡን  እንዲመክሩ፣ እንዲያስተምሩ፣ እንዲገሥጹ  ወደ ፊት ሊመጣ ካለው መቅሠፍት እንዲጠበቁ፣ አስተማሪ፣ መካሪ ፣በመከራም ወቅት አጽናኝ አድርጎ ከላካቸው ቅዱሳን ዋነኞቹ ነቢያት ናቸው፡፡

በክፍል አንድ እንዳቀረብነው ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች እና የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ደግሞ ትክክለኛና እውነተኛ ሰዎች በመሆናቸው የተናገሩት ሁሉ የሚፈጸም ነው፡፡ በአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ላይ  እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ ‹‹…እነሆ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፤ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ  በእውነት ይፈጸማል …፡፡›› (፩ሳሙ.፱፥፮) ይህ ቃል የተነገረው ስለ ነቢዩ ሳሙኤል ነው፡፡ ነቢያት ከእውነተኛው እግዚአብሔር የተነገራቸውን እውነተኛ ትንቢት፣ እውነተኛ ትምህርት፣ እውነተኛ ቃል በእውነት የሚናገሩ፣ የሚያሰተላልፉ፣ የራሳቸውን ሳይሆን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የሚያደርሱ ታማኝ መልእክተኞችና አፈ እግዚአብሔር ናቸው፡፡

አንዳች ቃል ከራሳቸው አይናገሩም፤ ለክብራቸውና ለዝናቸውም ሆነ ለሥጋዊ ጥቅማቸውና ዓላማቸው አንዳች ተጨንቀው፣ ከንቱና ምድራዊ ሐሳብን ከልባቸው አንቅተው፣ ከአንደበታቸው አውጥተው የሚናገሩ አይደሉም፡፡ ሲናገሩ እንኳን ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤›› ይሉ ነበር፡፡ (አሞ.፩፥፫፤፮፥፱) ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ሀብት ጸጋ እንጅ በሰው ፈቃድ የመጣ ወይም የሚገኝ አይደለም፡፡ ቃለ መልእክቱም የአናጋሪው እግዚአብሔር እንጂ የተናጋሪው አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹..ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደለትም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ…›› ያለው ለዚያ ነው፡፡ (፪ጴጥ.፩፥፳፩) ከሐዋርያው መልእክት የምንረዳው ብዙ ነገር ነው፡፡

  • አንደኛ ትንቢት በሰው ፈቃድ የመጣ አለመሆኑን፤
  • ሁለተኛ ማንም ለራሱ ፈቃድ ትንቢትን መተርጎም የማይገባው መሆኑን፤
  • ሦስተኛ ከእግዚአብሔር ያልተላከ የማይናገረው መሆኑን፤
  • አራተኛ ከእግዚአብሔር ተልኮ ትንቢት ለመናገር መልክተኛው ራሱ ቅዱስ መሆን የሚገባው መሆኑን ወዘተ ነው፡፡

ነቢያት ዘወትር በእግዚአብሔር ውሳኔ ስለሚፈጸሙ ድርጊቶች፣ መንግሥታት ሕግ ሲተላለፉ ስለሚመጣባቸው መቅሠፍት ወይም ማድረግ የሚገባቸውን እንዲያድርጉ፣ ስለ ኃጢአት ወይም ወደፊት ስለሚከሰቱ ነገሮች ወዘተ በምሳሌም፣ በቀጥታም፣ በቃልም፣ በድርጊትም፣ የሚገልጡና የሚያሰተላልፉ መሆናቸውን በብዙ መልኩ ተጽፏል፡፡ (ኢሳ.፭፥፩-፯፤ሕዝ.፬፥፪) ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም በሥጋ ብእሲ ሲመጣ ከፈጸማቸው አገልግሎቶችም ትንቢተ ነቢያት ዋናው ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፲፯)

እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን አገልግሎቱ የጎላም ባይሆን በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ነቢያትን እንዳስነሣና ከሐዋርያቱ ጋር ቤተ ክርስቲያንን እንደ መሠረቱ፣ ከመምህራንም ጋር እንዳገለገሉ በሐዋርያት ሥራ ፲፫፥፩ እንዲሁም በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ላይ ተጽፎ እናነባለን፡፡ (ኤፌ፪፥፳) በአብዛኛው የሐዲስ ኪዳን ነቢያት አገልግሎታቸው እንደ ብሉይ ኪዳን የጎላና የታወቀ ብዙም ትኩረት የሚሰጠው አይደለም፡፡

ትንቢትና ራእይ የሚባሉትም በዚያ ልክ የሚተኮርባቸው አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሊቃውንቱ እንደሚሉት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነቢያትም ሆነ የትንቢት አስፈላጊነት ከፍ ያለ እንዲሆን ምክንያቱ ዓመተ ፍዳ፥ ዓመተ ኩነኔ ነበር፤ ዘመኑ የሰው ልጅ በአዳማዊና በሔዋናዊ በደል ምክንያት በመከራና በጨለማ የነበረበት በመሆኑ፣ በሥጋ ወደ መቃብር፣ በነፍስ ወደ ሲኦል የሚወረድበት ዘመን ስለ ነበር  ‹‹ሁላችንም እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል›› እንዳለ ሕዝቡ በመከራ ውስጥ ስለ ነበሩ ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ እግዚአብሔር ትቶናል እንዳይሉ፣ ነቢያት አጽናኝ መካሪ ሆነው፣ የእግዚአብሔርን ማዳን እየሰበኩ፣ ነገረ ምጽአቱን እየነገሩ ተስፋ የሚሰጡ፣ የሚመክሩ፣ የሚያጽናኑ ስለሆኑ ነበር፡፡ (ኢሳ.፷፬፥፮፣፵፥፩) በሐዲስ ኪዳን ግን ገና ሊመጣ ያለው፥ ክርስቶስ ያልነገረን አዲስ ሊነግሩን የሚችሉት ያላወቅነው፥ ግን ልናውቀው የሚገባ እምብዛም ነገር ስለሌለ ነቢይነትና ትንቢት ጎልተው የሚነገሩበት ዘመን አይደለም፡፡

ይልቁንስ ሐሰተኛች ነቢያት ነቢይ ሳይሆኑ ነቢይ ነን የሚሉ፣ ሀብተ ትንቢት ሳያድርባቸው ትንቢት እንናገራለን የሚሉ፣ ትንቢትን ለራሳቸው ፈቃድ የሚተረጉሙ፣ ሐሰተኛ ሆነው በሐሰት ትምህርታቸው የሚያስቱ ብዙዎች እንደሚመጡ ባለቤቱ የነገረን እንደ ብሉይ ኪዳኑ ዘመን ብዙ ነገራችን በትንቢትና በትንቢት ተናጋሪዎች አጀንዳ እንዳይወሰድ ነው፡፡ ይህ ማለት በሐዲስ ኪዳን ዘመን “ትንቢትም፣ ነቢይም የለም፤ አይኖርም” ብሎ ለመደምደም አይደለም፤ እግዚአብሔር ባወቀ በዚህ ጸጋ የጎበኛቸው ኃላፍያትንና መጻእያትን ማየት የሚችሉ የሉም ለማለት አይደለም፡፡ በሐዲስ ኪዳን ነቢያት ቢኖሩ እንኳን ሥራቸው ቤተ ክርስቲያንን መምከር፣ ማጽናትና ማነጽ ነው እንጂ ትንቢት መናገር አይደለም፡፡ (መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፻፵፩፤የሐዋ.ሥራ.፲፭፥፴፪)

እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስነው ሐሰተኞች ነቢያት እንደሚነሡ፣ ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፣ ክርስቶስም፥ ሐዋርያትም ብዙ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹..የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑ ሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› እንዳለ የበግ ለምድ የለበሱ ናቸው፤ (ማቴ.፯፥፲፭) በጦር የተወጉትን፣ በመጋዝ የተተረተሩትን፣ በቅድስና ዘመናቸውን የፈጸሙትን፣ ሕዝቡን በቅንነት የመሩትን፣ ያገለገሉትን መልካሙን የነቢያትን ስም ለብሰዋል፤ ውስጣቸው ግን በተንኮል፣ በፍቅረ ንዋይ፣ በፍቅረ ዝሙት፣ በሟርትና በጥንቆላ፣ በክፋትና በሽንገላ የተሞላ ክፉ ነጣቂዎች፣ ከሕይወት ወደ ሞት  የሚነጥቁ፣ ቀልብ አጥተው ቀልብ የሚያሳጡ፣ ክፉ፣ ቀማኞችና ሐሰተኞች ነቢያት ዛሬ በዘመናችን መጥተዋል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በበኩሉ ‹‹ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳን ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ›› በማለት አስተምሮናል፡፡ ( ጴጥ.፪፥፩) ዛሬ በዘመናችን አንዳችም ሳይሸራረፍ ይህ ቃል ተፈጽሟል፡፡ በሐሰተኛ የኑፋቄ ትምህርት ሕዝቡን የበከሉ፣ መንጋውን ከበረት አስወጥተው ተቅበዝባዥ ያደረጉ፣ በነፋስ እንደሚገፋ ገለባ አየር ላይ በምኞትና በከንቱ ተስፋ የሚያንሳፍፉ ሐሰተኞች ነቢያት ብዙ ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ሐዋርያት በመልእክታቸው የነገሩንን የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ፣ የዋጃቸውን ጌታ የካዱ ትውልዱን ወደ እቶን እሳት የሚጨምር፣ ክፉና የተሳሳተ የጥፋት ትምህርትን አሾልከው ያስገቡ፣ ስተው የሚያስቱ፣ ጠፍተው የሚያጠፉ ክፉ ነቢያት፣ ሐሰተኛ መምህራን መጥተዋል፡፡ ቅዠታቸውን ራእይ፣ ምኞታቸውን ትንቢት፣ ተረታቸውን ወንጌል ብለው የሚያስተምሩ ነጣቂ ተኩላዎች ከዚህም ከዚያም በዝተዋል፡፡ ግን ጌታ ምን አለን? ከእነዚህ ተጠንቀቁ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ ‹‹ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና›› ይላል፡፡ (፩ዮሐ.፬፥፩) ቆም ብሎ መመርመር፣ ሐሰተኞችን ከእውነተኞች መለየት፣ ከነጣቂዎችና ከክፉ ትምህርታቸው መጠበቅ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ሊሆን ያለውን ነገር እያንዳንዱን ነግሮናል፤ አስቀድሞ አስጠንቀቅቆን ሳለ ድንቅ የሆነ አዲስ ነገር ፍለጋ በክፉ መንፈስ በሚመሩ፣ ከእግዚአብሔር ባልሆነ የአጋንንት መንፈስ በሚጓዙ፣ በመልካሙ ስም በነቢይነት፣ በከበረው ስም በመምህርነት የሚመጡትን እናውቃቸውና እንጠነቀቃቸው ዘንድ ተነግሮናል፡፡

ተወዳጆች ሆይ! ሐሳቡ ሰፊ በመሆኑ ልንጨርሰው አልተቻለንም፡፡ ስለሆነም ሐሰተኖች ነቢያት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? ሐሰተኛ የሚያስብሏቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?  የሚሉትንና ተዛማጅ ነገሮችን በቀጣይ በክፍል ሦስት ልናቀርብላችሁ እንሞክራለን፡፡

የበረከት ጾምና የመጽናናት ሳምንት ይሁንልን፤ አሜን!