‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› (፩ሳሙ.፱፥፮)

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ኅዳር፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የዚህ ጽሑፍ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ዘመነ ክረምቱን/ዘመነ ጽጌን እግዚአብሔር ረድቶን ብዙ ተምረንበት አልፏል፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅቶችን ከፋፍላ ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ማርያምን እና ነገረ ቅዱሳንን ታስተምራለች፤ ትዘክራለች፡፡ ከፊታችን ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፰/፳፱ ድረስ ደግሞ ዘመነ ነቢያትን የምንዘክርበት፣ ‹‹ጾመ ነቢያት›› ብለን ከጾም ጋር አገናኝተን ስለ ነቢያትና ነቢይነት፣ እንዲሁም ስለ ትንቢት ዓላማና ምክንያቱ  ቤተ ክርስቲያን ብዙ የምታስተምርበት  ወቅት ነው፡፡ እኛም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› በሚል ርእስ ስለ ነቢያት ምንነትና ማንነት ይህችን ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

በመጽሐፈ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደተጠቀሰው ነቢይ ማለት ‹‹የእግዚአብሔር ሰው›› ማለት ነው፤ ነቢይ ለአንድ፣ ነቢያት ለብዙ፣ ነቢይት ለሴት መጠሪያዎች ናቸው፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፻፵፩) በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም በሌሎች መጻሕፍትም እንደምንረዳው

፩ኛ. ነቢይ ማለት ቃልን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለሕዝብ የሚናገር፤

፪ኛ. የእግዚአብሔር ሰው፤

፫ኛ. ባለ ራእይ /ራእይ የሚያይ/፤

፬ኛ. የእግዚአብሔር ባሪያ አገልጋይ፤

፭ኛ. ኃላፍያትን፣ መጻእያትን በእርግጠኝነት የሚያውቅ የሚናገር….ወዘተ ማለት ነው፡፡

ነቢያት ለብዙ ቁጥር ሲሆን ትርጉሙ አይለወጥም፡፡ በጥቅሉ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ወደ ፊት የሚሆነውን፣ የሚከሰተውን ሁሉ በእርግጠኝነት የሚናገሩ፣ የሚናገሩትም ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል›› እያሉ ነው፡፡ (፩ሳሙ.፱፥፮፣አሞ.፩፥፫፣መክ.፫፥፰) እግዚአብሔርም የሚገለጥላቸውና የሚያናግራቸው በራእይ፣ በሕልም፣ በመልአክ አማካኝነት ነው፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፮፣ዳን.፲፥፲፩፣፣ዕብ፣ ፩፥፩)

የነቢያት ሥራ

ትንቢት ይናገራሉ፤ ሕዝቡን ይመክራሉ፤ ያስተምራሉ፤ ይገሥፃሉ እንዲሁም ያጽናናሉ፡፡ ‹‹አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ›› እንዳለ፡፡ (ኢሳ.፵፥፩) በእግዚአብሔር ውሳኔ ስለ ሚፈጸሙ ድርጊቶች ስለ መንግሥታት፣ ስለ ስለ ሕዝቡ፣ ስለ ኀጢአት፣ ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ክስተቶች ወዘተ  በምሳሌ ወይም በድርጊት ይገልጹ ነበር፡፡ (ኢሳ.፭፥፩፣ኤር.፩፥፲፱) ስለዚህ ነቢይ ማለት አፈ እግዚአብሔር፣ መምህር፣ ሰባኪ ማለትም ነው፡፡ ስያሜውም መንፈሰ ትንቢት ላደረባቸው፣ ራእይን የማየት ጸጋ ለተሰጣቸው እውነተኛ ነቢያት የሚሰጥ ስያሜ ነው፡፡

የነቢያት አከፋፈል

ነቢያት ብዙ ወገን ናቸው፡፡ ቀደምት ነቢያት ደኃርት ነቢያት፣ ዐበይት ነቢያት ደቂቀ ነቢያት፣ እውነተኛ ነቢያት ሐሰተኛ ነቢያት፣ ወንድ ነቢያት ሴት ነቢያት፣ የቃል ነቢያት የጽሑፍ ነቢያት ወዘተ እየተባሉ ይከፈላሉ፡፡

ከአዳም እስከ ዳዊት ያሉትን ነቢያት ብዙ ጊዜ ቀደምት ነቢያት እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አበው ቅዱሳን ነቢያትን በአራት ከፍለን እንማራቸዋለን፡፡

፩. ዐሥራ አምስቱ አበው ነቢያት

፪. አራቱ ዐበይት ነቢያት፤

፫. ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት እና

፬. ካልአን ነቢያት ናቸው፡፡

፩. ዐሥራ አምስቱ አበው ነቢያት

ዋና ዋናዎቹ አባታችን አዳም፣ ሴት፣ ሔኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ፣ ሄኖክ፣ ማቱሳላ፣ ላሜህ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ሳሙኤል ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ሀብተ ትንቢት ተሰጥቷቸው ኃላፍያትን፣ መጻእያትን ሲናገሩ፣ ሕዝቡን ሲመክሩ፣ ሲያሰተምሩ፣ ሲያስጠነቅቁ፣ ሲያጽናኑ የነበሩ አበው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- የመጀመሪያዎቹን ዐሥሩን አበው ከአዳም እስከ ኖኅ ያሉትን ብንወስድ፣ በደብር ቅዱስ ሆነው ልጆቻቸውን ሲመክሩ፣ ከደቂቀ ቃኤል እንዳይደባለቁ፣ ቅድስናቸውን እንዲጠብቁ፣ በደቂቀ ቃኤል ምክንያት ምድሪቱ በማየ አይኅ እንደምትጠፋ አስቀድመው እንደተናገሩ በገድለ አዳምና በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ላይ በሰፊው ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

፪. አራቱ ዐበይት ነቢያት

ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡

፫. ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት

ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ አብድዩ፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ኢዩኤል፣ ዕንባቆም፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው፡፡ ዓበይትና ደቂቅ መባላቸው በምሥጢር ሳይሆን በይዘት ሰፊና አነስ ያለ ትንቢት ከመናገር አንጻር ነው፡፡

፬. ካልኣን ነቢያት

ኢያሱ፣ ሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ ወዘተ ናቸው፡፡

ነቢያት በከተማና በዘመን ጭምር ይከፈላሉ፡፡ ለምሳሌ በከተማ የይሁዳ፣ የሠማርያ፣ የባቢሎን ምርኮ ነቢያት ወዘተ እየተባሉ ሲከፈሉ፣ በዘመን ደግሞ

  • ከአዳም እስከ ዮሴፍ የዘመነ አበው ነቢያት፤
  • ከሙሴ እስከ ሳሙኤል የዘመነ መሳፍንት ነቢያት፤
  • ከዳዊት እስከ ዘሩባቤል የዘመነ ነገሥት ነቢያት፤
  • ከዘሩባቤል እስከ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ የዘመነ ካህናት ነቢያት እየተባሉ ይጠራሉ፡፡

ነቢያት የሚከፈሉበት ሌላው አከፋፈል ደግሞ የጽሑፍ ነቢያትና የቃል ነቢያት ሲሆን የጽሑፍ ማለት የተናገሩት የትንቢት ቃል በጽሑፍ የሰፈረ፣ የተጻፈ ሲሆን ከኢሳይያስ እስከ ነቢዩ ሚልክያስ ያሉትን ዐሥራ ስድስቱን ነቢያት የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህም አራቱ ዐበይትና ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ያልናቸው ናቸው፡፡

የቃል ነቢያት የሚባሉት ደግሞ ትንቢት ተናግረዋል፤ ግን የተናገሩት ትንቢት በጽሑፍ ያልሰፈረ ያልተጻፈ ለማለት ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የሚወሰዱት ነቢዩ ጋድ፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ናታን፣ ወዘተ፡፡

ሌላኛው አከፋፈል ደግሞ ወንድ ነቢያትና ሴት ነቢያት የምንለው ሲሆን ከላይ በተለያየ መልኩ የገለጽናቸው ወንድ ነቢያት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በርካታ ሴት ነቢያትም መኖራቸውን እንረዳለን፡፡ ከእነዚህም መካከል የሙሴ እኅት ማርያም (ዘፀ.፲፭፥፳) የሰፊዶት ሚስት ዲቦራ (መሳ.፬፥፬)፣ በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የነበረችው ሕልዳና (፪ነገ.፳፪፥፲፬)፣ ነቢይት ሐና (ሉቃ.፪፥፴፮)፣ የፊልጶስ አራት ደናግል ሴት ልጆች ወዘተ ሴት ነቢያት ናቸው፡፡(የሐዋ.ሥ. ፳፩፥፱፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት)

እነዚህ ሁሉ የጠቀስናቸው ሀብተ ትንቢት ያደረባቸው፣ አፈ እግዚአብሔር ሆነው የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡም ለነገሥታቱም ሲያድረሱ፣ ሲያስተምሩ፣ ሲመክሩ፣ ሲዘክሩ፣ ሲያጽናኑ አልፎም ሲገሥፁ የነበሩ ነቢያት ሲሆኑ እውነተኞች ነቢያት ናቸው፡፡ ያናገራቸውም መንፈስ ቅዱስ ሲሆን የተናገሩት ሁሉ የተፈጸመላቸው ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታየው ሌላኛው ዓይነት አከፋፈል እውነተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ነቢያት ተብሎ ነው፡፡

ውድ አንባብያን! ሐሰተኛ ነቢያት በዘመናችን እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን በመሆኑ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ሐሰተኛ የሚባሉትስ ከምን አንጻር ነው? የሚለውን በክፍል ሁለት እናዳርሳችኋለን፤ ቸር እንሰንብት!