“የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ. . . ይጠቅማል” ክፍል ሁለት

 ግንቦት 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

አዋልድ መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያላቸው ተዛምዶ፡

ቀደም ተብሎ እንደተለጠው አዋልድ መጻሕፍት ልጅነታቸው ለአሥራው መጻሕፍት (ለመጻሕፍት አምላካውያት) ነው፡፡ ልጅ ከአባቱ አብራክ፣ ከእናቱ ማኅጸን ተከፍሎ ወላጆቹንመስሎ እንዲወጣ እነዚህም በምሥጢርም በእምነትም በሥርአትም የአሥራውን መጻሕፍት ሥርና መሠረት ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በምሥጢርም ኾነ በሥርዓት ከአሥራው መጻሕፍት ጋር የሚቃረኑት መጻሕፍት ከአዋልድ አይቆጠሩም፡፡ ምክንያቱም በሐዋርያው ቃል “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን” ተብሏልና (ገላ.፩፥፰)፡፡

አዋልድ መጻሕፍት ከአሥራው መጻሕፍት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሚከተሉት ነጥቦች መረዳት ይቻላል፡፡

ሀ. በዓይነታቸው፡- አሥራው መጻሕፍት ተብለው የሚታወቁት ሰማንያ አንዱ መጻሕፍት የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብ፣ የትንቢት ተብለው ይመደባሉ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ አዋልድ መጻሕፍት በዚሁ አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህንን የማሳያ ሰንጠረዥ እንመልከት፡-

የመጻሕፍቱ

ዓይነት

የመጻሕፍቱ ይዘት

የሕግ

የታሪክ

የጥበብ

የትንቢት

አሥራው

ብሔረ ኦሪት

መጽሐፈ ሳሙኤል

መዝሙረ ዳዊት

ትንቢተ ኢሳይያስ

አዋልድ

ፍትሐ ነገሥት

ተአምረ ማርያም

ውዳሴ ማርያም

ፍካሬ ኢየሱስ

 

 

 

  

 

 

 

ለ. በባለቤታቸው፡-የቅዱሳት መጻሕፍት ባለቤታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ገንዘቦች፣ በእርሱም ፈቃድና ምሪት የተፃፉ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት በምድር የእግዚአብሔር እንደራሴ የሆነች፣ የጸጋው ግምጅ ቤት ናት (የሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ስለሆነም ከእግዚአብሔር የተላኩ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ወንጌልንና መልእክታትን የጻፉት ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

የአዋልድ መጻሕፍት ጸሐፊዎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሲሆኑ እነርሱም መንፈሰ እግዚአብሔር እንደገለጠላቸው መጠን መጻፍቱን የጻፉት ለቤተክርስቲያን ልጆች ለምእመናን ነው፡፡ በመሆኑም ባለቤታቸው ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ለትርጉማቸው፣ ለታሪካቸውና ለምሥጢራቸው መጠየቅ ያለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ሐ. በቅድስናቸው፡- አሥራው መጻሕፍትንም ሆነ አዋልድ መጻሕፍትን ያጻፈው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የአሥራው መጻሕፍትን ጸሐፍት እንደመረጠ እንዳተጋ ምሥጢር እንደገለጠላቸው፣ የአዋልድ መጻሕፍትን ጸሐፍት የመረጠ፣ ያተጋ፤ ምሥጢር የገለጠላቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ከአንዱ ምንጭ ከመንፈስ ቅዱስ በመገኘታቸውም የአሥራውም ሆኑ የአዋልድ መጻሕፍት ዓላማቸው ነገረ ሃይማኖትን ማስረዳት ደግሞም ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር መጥቀም ነው፡፡(፪ኛ.ጢሞ.፫፥፲፮)

በልዩ ልዩ ዘመናትና ሰዎች በተራራቀ ሀገር ተጽፈው ለየብቻቸው የነበሩትን አሥራው መጻሕፍት ከመሠረተ ሃይማኖት አንጻር መርምራ አረጋግጣ በአሥራው መጻሕፍትነት የተቀበለችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አዋልድ መጻሕፍትንም የምትቀበለው በተመሳሳይ መልኩ ከትምህርቷ አንፃር መርምራ አረጋግጣ ነው፡፡

መ. የእግዚአብሔርን ሥራ በመግለጥ፡- የቅዱሳት መጻሕፍት ተቀዳሚ ዓላማ የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር በቀጥታ ራሱ ወይም በወዳጆቹ አድሮ ለሕዝቡ ያደረገውን ተአምር፣ መግቦት፣ ቸርነት ያብራራሉ፡፡ይህ እውነታ በአሥራው መጻሕፍት በስፋትና በይፋ የተገለጠ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ከመሆኑ የተነሣ የእግዚአብሔር ሥራ ተአምር የተፈጸመላቸውንና የተፈጸመባቸውን ሰዎች፣ ቦታዎች እምብዛም ትኩረት አይሰጧቸውም፡፡ ተአምሩን ብቻ ገልጠው የሰዎችንና የቦታዎችንስምእገሌ፣አንድሰው ብለው ያልፋሉ፡፡ (ማቴ.፳፮፥፲፰፣፩ኛ. ነገ፲፫፥፩፣ ማቴ.፰፥፪፣ ሉቃ.፲፩፥፲፭) ይህ በአሥራው መጻሕፍት ብቻ የሚንጸባረቅ ሳይሆን የአዋልድ መጻሕፍትም ዓላማ ነው፡፡ በገድለ ተክለሃይማኖት፣ በገድለ ጊዮርጊስ፣ በተአምረ ማርያም ውስጥ በቅዱሳን አማላጅነት የእግዚአብሔር ሥራ (ተአምር) የተፈጸመላቸው ወይም የተፈጸመባቸው ሰዎችን ስም፣ ቦታ ሳያነሡ እገሌ፤ እገሊት አንድ ሰው ብለው የሚጠሩት ሰዎቹና ቦታዎቹ መጠሪያ ስለሌላቸው ሳይሆን ዓላማቸው የእግዚአብሔርን ሥራ መግለጥ ስለሆነ ነው፡፡

ሠ. የሃይማኖትን ታላቅነት በመግለጥ፡- ቅዱሳት መጻሕፍት በሃይማኖት፣ ለሃይማኖት፣ ስለሃይማኖት የተጻፉ ናቸው፡፡ ከጥርጥር፣ ከአጉል አሳብ ተጠብቆ በመጻሕፍቱ የተገለጠውን፣ የታዘዘውን ለጠበቀ የተባለው ይፈጸምለታል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ሃይማኖትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ በሃይማኖትም ሕግ ታዝዘው ለጣዖት መስገድን እምቢ አሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ከእሳት ቢጣሉ በሃይማኖት የእሳትን ኃይል አጠፉ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በሃይማኖት የአናብስትን አፍ ዘጋ፡፡ ጌዴዎን ያለ ጦር መሣሪያ አእላፍ የአሕዛብን ሠራዊት ድል አደረገ፡፡ ይህ የሃይማኖትን ታላቅነት ያስረዳል (ዕብ.፲፩፥፴፫-፴፬)፡፡ በአዋልድ መጻሕፍትም አቡነ ኤውስጣቴዎስ በአጽፋቸው (በመጎናጸፊያቸው) ባሕር ሲከፍሉ፣ ፃድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከንብ ቀፎ ተከተው በቆዳ ተጠቅልለው ከተወረወሩበት ገደል ሲወጡ፣ ከእሳት መካከል ቆመው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፤ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚቆራርጥ መርዝ ሲያጠጡት ሕያው ሆኖ የሚያሳየን የሃይማኖትን ታላቅነት ነው፡፡

በአሥራውም ሆነ በአዋልድ መጻሕፍት የተጠቀሱት ሰዎች ታላላቅ ተአምራት ሲፈጽሙ የምንመለከተው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “አማን አማን እብለክሙ ዘየአምን ብየ ዘአነ እገብር ውእቱሂ ይገብር ወዘየዐቢ ይገብር፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤” ያለው ቃል ተፈጽሞላቸው ነው፡፡(ዮሐ.፲፬፥፲፪)፡፡

ረ. የሃይማኖትሰዎች ያደረጓቸውን ልዩ ልዩ ተጋድሎዎችን መግለጥ፡- እግዚአብሔር ድንቅ የሆነ ሥራውን ለፍጥረቱ የሚሠራው በፍጥረቱ አማካኝነት ነው፡፡ ይህም በልዩ ልዩ መንገድ ይፈጸማል፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ በስፋትና በግልጥ ከሚሠራባቸው ፍጡራን መካከል ደግሞ ቅዱሳን ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ለሕገ እግዚአብሔር ተገዝተው ፈቃዱን በመፈጸማቸው ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ አደረጉ፡፡ በዚህ ሰውነታቸውም ከእግዚአብሔር በተቀበሉት ኃይል ብዙ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ የአሥራውም ሆኑ አዋልድ መጻሕፍት ይህን የቅዱሳንን የተጋድሎ ሕይወት ይገልጣሉ፡፡ ነሕምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መሥራቱ፣ አስቴር በጾም በጸሎት ሕዝበ እሥራኤልን ስለመታደጓ፣ ዮዲት በጥበብ ሆሊፎርንስን መግደሏ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው ሕሙማንን መፈወሱ፣ እመቤታችን፣ጻድቃን ሰማእታት ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት መፈጸማቸው በየቅዱሳት መጻሕፍቱ ተገልጦ እናገኛለን፡፡

አዋልድ መጻሕፍትን ቤተ ክርስቲያን የምትቀበለው እንዴት ነው?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍትን የምትቀበልበት ሥርዓት አላት፡፡ ቀደም ተብሎ በተደጋጋሚ እንደተገለጠው የአዋልድ መጻሕፍት ልጅነታቸው በይዘት፣በመንፈስ፣ በምሥጢርና በመሠረተ ሐሳብ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት “አሥራው መጻሕፍት” ይባላሉ፡፡ አሥራው ማለት ሥሮች ማለት ሲሆን፣ አሥራው መጻሕፍት ሲላቸው ደግሞ የሌሎች መጻሕፍት መገኛዎች፣ ሥሮች ማለት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ማለት ለአዋልድ መጻሕፍት በይዘትና በመንፈስ፣ በምሥጢርና በመሠረተ ሐሳብ አስገኚ ሥራቸውና ወላጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ኾኖ በእርሱ ሥርነት የሚበቅሉና የሚያድጉ ማለት ነው፡፡

ይህ ኾኖ ሳለ በአንዳንድ ይዘታቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ቢመስሉም ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ፣በጌታችን ከተገለጠውና ከሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ ከመጣው የቤተክርስቲያንእምነትና ትምህርት ጋር ተቃርኖ ያላቸውን መጻሕፍት ቤተ ክርስቲያን ታወግዛለች እንጂ አትቀበልም፡፡ መጻሕፍቱም “ዲቃሎች” እንጂ “አዋልድ” አይባሉም፡፡

አዋልድ መጻሕፍትን በተመለከተ በሚከተሉት ነጥቦች መለየት እንደሚቻል ሕንዳዊው የነገረ መለኮት ሊቅ ጢሞቴዎስ አለን ይገልጡታል፡-

  • ዓላማቸው መንግሥተ እግዚአብሔር የሆነ፣

  • በሃሳብ፣ በመንፈስ፣ በምሥጢር፣ በነገረ መለኮት ከአሥራው መጻሕፍትና ከቅዱሳት የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር የማይጋጩ፣

  • ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ሕይወትና አኗኗር ተስማሚ የሆኑ፣

  • የቤተ ክርስቲያን አበው፣ትውፊት ወይም ጉዞ ምስክር ያላቸው፣

  • ውስጣዊ ተቃርኖ የሌለባቸው፡፡

እንግዲህ በጎ ትምህርት የሚያስተምሩንን፣ ስለ ቅዱሳን አበውና እመው ሃይማኖታዊ ተጋድሎ የምንረዳባቸውን፣ አሥራው መጻሕፍትንም የሚያብራሩልንና የሚተረጉሙልንን አዋልድ መጻሕፍትን በመጠቀም በሃይማኖት ለመጽናት፣ በጎ ሥራ ለመሥራት ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር