‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› (መዝ.፴፫፥፯)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፲፰፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁልን? ትምህርት እንዴት ነው? ደጋግመን ስለ ትምህርታችሁ የምንጠይቃችሁ በዚህ ጊዜ የእናንተ ተቀዳሚ ተግባራችሁ መሆን ያለበት እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ መማርና ማወቅ ብልህና አስተዋይ ያደርጋል፤ ታዲያ ስትማሩም ለማወቅ እና መልካም ሰው ለመሆን መሆን አለበት! ደግሞም የዓመቱ አጋማሽ ፈተናም እየደረሰ በመሆኑ በርትታችሁ ማጥናታችሁ መምህራን የሚያወጡትን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጥያቄውን ከመመለስ በተጨማሪ ምን ያህል እውቀት እንዳገኛሁ ልታውቁበት ይገባል!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ የምንነግራችሁ ታሪክ በታኅሣሥ ፲፱ ቀን ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ስለሚከበርለት ቅዱስ ገብርኤልና ስላዳናቸው ሦስቱ ሕፃናት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ገብርኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት መካከል አንዱ አንደሆነ በባለፈው ትምህርታችን አስተምረናችሁ ነበር፤ ታስታውሱ እንደሆነ ገብርኤል ማለት ምሥራች ነጋሪ (የጌታን ሰው መሆን ያበሠረ)፣ ሰውና አምላክ ማለት ተምራችኋል፡፡ ያዘኑትን የሚያጽናና፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ጥበብን ማስተዋልን የሚሰጥም እንዲሁም የምሥራች መልአክ ነው፡፡ ታስታውሳላችሁ አይደል? መልካም! በዚህ የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ደግሞ ሦስቱን ሕፃናትን አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ከነደደ እሳት ውስጥ ያወጣቸው ቅዱስ ገብርኤል እንደሆነ እንማራለን፡፡

ባቢሎን በሚባል ሀገር ናቡከደነጾር የተባለ ጨካኝ፣ እግዚአብሔርን የካደና ጣዖት የሚያመልክ ንጉሥ ነበር፤ ልጆች! ጣዖት ማለት ሰዎች ራሳቸው ከድንጋይ ወይም ከእንጨት እየሠሩ የሚያመልኳቸው ናቸው፡፡ ታዲያ! እርሱ ተሳስቶ ሌሎችንም ለማሳሳት ጣዖት አሠርቶ ስገዱ እያለ ማስፈራራት ጀመረ፤ ይገርማችኋል ልጆች! ብዙ ሰዎች ንጉሡን ፈርተው ላልፈጠራቸው ራሳቸው ለሠሩት ጣዖት አምላክ እያሉ መስገድ ጀመሩ፤ በዚያ ሀገር ደግሞ ከኢየሩሳሌም ከተማ ተማርከው ባቢሎን ወደ ሚባል ሀገር የሄዱ ሰዎች ነበሩ፡፡

ልጆች! ከእነርሱም መካከል ሦስት ወጣቶች ንጉሡን በመቃወም እነርሱ የሚያመልኩት ዓለምን የፈጠረና የሁሉንም አምላክ እግዚአብሔርን እንደሆነ ተናገሩ፡፡ ንጉሡም እሳት እንዲነድ ካዘዘ በኋላ ካልሰገዱ በእሳት እንደሚያቃጥቸላው ነገራቻው፡፡ እነርሱ ምን አሉ መሰላችሁ? ‹‹…የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት…›› (ዳን.፫፥፲፯)

ንጉሡ በዚህ ተበሳጨ ሦስቱን ሕፃናት በትልቅ ጉድጓድ ተዘጋጅቶ ይነድ ወደ ነበረው እሳት እንዲጣሉ አደረገ፡፡ በዚህን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና ከሕፃናቱ ጋር አብሮ በእሳቱ መሐል ቆመ፤ እሳቱንም አቀዘቀዘላቸው፤ እነርሱም ምንም ሳያቃጠጥላቸው በእሳት መካከል ሆነው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ልጆች! ንጉሡ ይህንን ሲመለከት በጣም ተገረመ፤ ከእሳቱ የተጨመሩት ሦስት ሕፃናት ነበሩ፡፡ እርሱ ግን አራተኛ ሆኖ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልን በእሳቱ ውስጥ ተመለከተ፡፡ ተደንቆም ለባለሟሎቹ (ለአገልጋዮቹ) ‹‹ሦስት ሰዎችን ዐሥረን ከእሳት ጥለን አልነበረምን?…. እነሆ አሁን አራት ሰዎችን በዚያ አያለው፤… የአራተኛው መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል››አለ፡፡ (ዳን.፫፥፲፯)

ከዚያም ሦስቱን ሕፃናት ከእሳቱ ውስጥ አስወጣቸው፤ እሳቱም ምንም ሳያቃጥላቸው ደኅና ሆነው ወጡ፤ ንጉሡም በአናንያ በአዛርያና በሚሳኤል አምላክ እንደሚያምን ተናገረ፤ ሕዝቡ ሁሉ በእነርሱ አምላክ እንዲያምን አወጀ፡፡ (ዳን.፫፥፳፰-፳፱) ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል…›› እንዳለው ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔርን በመፍራትና በማምለክ የሚጥሩትን ሦስቱን ሕፃናት ከነደደ እሳት አዳናቸው፡፡ (መዝ.፴፫፥፯)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከሦስቱ ሕፃናት ብዙ ነገር እንማራለን፡፡ በሥነ ምግባር የታነጽንና እምነታችን የጸናን ልጆች ሆነን ማደግ አለብን፡፡ሦስቱ ሕፃናት ሀገራቸው በነበሩበት ጊዜ ነቢያት መምህራኑ የሚያስተምሯቸውን ትምህርት በደንብ ያደምጡ ነበር፡፡ በምርኮ ሀገር ሳሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቁ ነበር፡፡ስለዚህ መከራ በገጠማቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን (ከቤተ ክርስቲያን አባቶች) የምንማራቸውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች በሕይወታችን መተግበርና ያወቅነውን ለሌሎች ማሳወቅ አለብን፡፡ ከዚህ ታሪክ እውነትን በእምነት መመስከር እንዲሁም በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግርም ጊዜ በእምነት መጽናት እንዳለብን፣ ሰዎችን በጸሎት መርዳትና ስለ እውነት ስለመመስከር እንማራለን፡፡

ልጆች! ሁል ጊዜም ቢሆን በትምህርት ቤት፣ በሰፈር ውስጥና ለሌሎች ስፍራዎች የመልካም ልጅ ምሳሌ መሆን ይገባናል፡፡

አምላከ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል በረከታቸውን ያድለን፤ አሜን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!