የኤማኁስ መንገደኞች

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ሚያዚያ ፳፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዓለም ላይ ብዙ መንገዶች አሉ፤ ሰዎችም በመንገድ ይጓዛሉ፤ ሆኖም ለተለያየ ዓላማ ነው፤ ግን ያች የኤማኁስ መንገድ ምን ያህል ዕድለኛ ናት? ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የሚወራባት፣ ክርስቶስ በእግሩ እየባረከ የነቢያትን ትምህርት የሚተረጉምባት መንገድ፣ የጠወለገ የደከመ የሚበረታባት መንገድ!

የእጁን ተአምራት፣ የቃሉን ትምህርት የሰሙ፣ ከዋለበት የሚውሉ፣ ካደረበት የሚያድሩ ከመቶ ሃያው ቤተሰቦቹ ሉቃስ (ቀለዮጳ) እና ኒቆዲሞስ ጌታችን በአይሁድ እጅ ተላልፎ መሠጠቱን ዓይተው “እስራኤልን ያድናቸዋል” ብለው ተስፋ ያደረጉት ሞተ ሲባሉ ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ወጣ ብላ ወደ ምትገኘው ኤማኁስ መንገድ ጀመሩ። ታሪኩ በሉቃስ ወንጌል እንዲህ ተመዝግቧል። “እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማኁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው አላቸው። ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። እርሱም፦ ይህ ምንድን ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፣ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው።” (ሉቃ.፳፬፥፲፫-፳፩)

በዚህ የወንጌል ክፍል በክርስቶስ የደረሰበትን መከራ ዘወትር ማሰብ እንዳለብን ይነግረናል፦ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምንም እንኳን ከጌታ ቤተሰብ ተለይተው ወደ ኤማኁስ መንገድ ቢጀምሩም የሚነጋገሩት የሚያስቡት ግን ነገረ ቀራንዮን ነበር። ክርስቲያኖች እከብር አይል ክቡር እነግሥ አይል ንጉሥ ማንም የማያበድረው ባለጸጋ አምላካችን ስለ እኛ ሲል የከፈለውን ዋጋ አስቡ! መላእክት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአይሁድ አደባባይ ሲያቆሙት፣ ክቡር ዳዊት “እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም” ብሎ የተናገረለትን እጆቹንና በገነት የተመላለሱትን እግሮቹ በችንካር ሲቸነከሩ፣ ወደ ምድር እንትፍ ብሎ ከደረቅ ግንባር ላይ ዓይን የፈጠረውን ምራቃቸውን ሲተፉበት፣ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪታይ ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጅራፍ ሲገረፍ፣ ለቅዱሳን ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የእሾህ አክሊል ሲያቀዳጁት፣ የብርሃን ልብስ የሚያለብሰንን ዕርቃኑን በመስቀል ላይ ሲሰቅሉት … እኛን ስለመውደዱ ይህን የእኛን መከራ የተቀበለልንን ክርስቶስ ልንረሳው አይገባምና ዘወትር ልናስታውሰው ይገባል። (መዝ.፻፲፰፥፸፫)

ክቡር ዳዊት “ዘልፈ እሬእዮ ለእግዚአብሔር ቅድሜየ ውእቱ በኲሉ ጊዜ፤ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ” እንዳለ ዘወትር ዓይነ ልቡናችንን ወደ እርሱ እናቅና፤ (መዝ.፲፮፥፰) ቀራንዮ ላይ ዕርቃኑን ተሰቅሎ “የሚሠሩትን አይውቁምና ይቅር በላቸው” እያለ ሲጸልይ እንስማው። (ሉቃ.፳፫፥፴፬) ሉቃስና ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን ከኢየሩሳሌም እየራቁ ቢሆንም የሚነጋገሩትና የሚያዝኑት ግን በቀራንዮ ላይ ደሙ ስለፈሰሰው ሥጋውን ስለተቆረሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ሲራቡ ኅብስት አበርክቶ ስላበላቸው ባሕር ከፍሎ ስላሻገራቸው “እንግዲህ ማን ያበላናል? ማንስ ያጠጣናል?” በማለት አልነበረም፤ ይልቁንም ለከሳሾቹ ተላልፎ ስለተሰጠው ክርስቶስ እንጅ። ክርስቲያኖች ከሳሽ ፈራጅ ሲሆን አይታችሁ ታውቃላችሁን? በቀራንዮ ግን ከሳሾች አይሁድ ፈራጅ ሆኑ፤ በዚህም ያለ ከልካይ የሚችሉትን ሁሉ ሥቃይ አደረሱበት። ሉቃስና ኒቆዲሞስ ስለዚህ ጉዳይ እየተነጋገሩ አዝነውና ተክዘው ሳለ ጌታችን ወደ እነርሱ ቀረበ፤ አብሮአቸውም መንገድ ጀመረ።

ክርስቲያኖች እኔ እና እናንተ ዛሬ ስንገናኝ  ስለ ምንድን ነው የምናወራ? ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ምኞታችን አይደለምን? መቼ ነው እንደ ሉቃስና ኒቆዲሞስ ቀራንዮንን እያሰብን የምንጓዝ? ዛሬ ቀራንዮን እያሰብን ስንጓዝ ክርስቶስ ቢመጣ እኮ የነቢያቱን ትምህርት ብቻ አይደለም፤ የሚተረጉም የሐዋርያቱንና የሊቃውንቱን ትምህርት እየተረጎመ ልባችንን በፍቅሩ ያቀጣጥለዋል እንጅ፤ ብቻ ያችን መንገድ እስክናገኛት ድረስ እንጓዝ! በዚያች መንገድ ብዙዎች አልሔዱባትምና። በዚህች መንገድ ለሚጓዙት ድኩማን ተጓዦች ክርስቶስ ተከተላቸው አብሮአቸውም ወደ ቤታቸው ገባ።  ለጌታ የተገባ እርሱ የሚስተናገድበት ቤት ናት። ዛሬ እንግዳ ሲመጣ ላለማሳደር ስንት ምክንያት እንደምንደረድር አስተውሉ! ክርስቶስ ከቤታቸው ገብቶ አብሮአቸውም ራት ሊበላ ተቀመጠ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም ተከፈተ፤ ይህ ትሕትና ምን ይደንቅ ምን ይረቅ? “ሰማይኒ መንበርየ ወምድርኒ መከየደ እገርየ፤ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት” ያለ አምላክ እንጀራ ይበላ ዘንድ ከአንዲት ደሳሳ ጎጆ መግባቱ የጠወለጉትን ሊያለመልም የደከሙትን ሊያበረታ አይደለምን? (ኢሳ.፷፮፥፩)

ከቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ርቃችሁ ያላችሁ ክርስቲያኖች እናንተ ሉቃስንና ኒቆዲሞስን አብነት አድርጓቸው፤ መምህሮቻችሁ እነርሱ ይሁን ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” እንዳለው ዘወትር እግዚአብሔርን በፊታችሁ ተመልከቱት፤ (ገላ.፫፥፩) ከመስቀሉ ሥር አትጥፉ፤ እንደ ስምዖን ቀሬናዊ መስቀሉን ተሸክማችሁ ወደ ቀራንዮ ገሥግሱ እንጅ። በሥራና በሌላ ምክንያት ጊዜ አጥታችሁ ከቤተ ክርስቲያን የራቃችሁም እንዲሁ ሉቃስና ኒቆዲሞስን መምህራኖቻችሁ አድርጉ፤ ያኔ ክርስቶስ ወደ እናንተ መጥቶ፣ ድካማችሁን አስወግዶ ወደ ቅድስት አገር ይመልሳችኋልና።

ክርስቶስ ወደ ቤታቸው ገባ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ሰጣቸው፤ ያን ጊዜ ዓይናቸው ተከፈተ። በመንገድ ሲያወሩለት የነበረው የነቢያቱን ትንቢት እየተረጎመ ልባቸውን ሲያቃጥለው የነበረው “አንተ በዚህች ምድር እንግዳ ነህን” በማለት ሲመልሱለት የነበረው ክርስቶስ እንደ ሆነ አወቁት። ዛሬ በእውነት ክርስቶስን የማያውቀው ሰው እጅግ ብዙ ነው። ሉቃስና ኒቆዲሞስም እርሱ እንደ ሆነ ሲያውቁት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የትንሣኤው ብርሃን የምሥራችም አብሳሪዎች ሆኑ። የትንሣኤችን በኩር ሞትን ድል አድርጎ እንደ ተነሣ ለደቀመዛሙርቱ ተናገሩ። የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬስ የእኛ ዓይን አልታወረምን? እግዚአብሔርን ማየት እንችላለን? ቤተ ክርስቲያንንስ አይተናት እናውቃለን? የኃጢአት ሞራ ዓይናችንን ጋርዶት ዘወትር ስለ ቁሳዊ ነገር ብቻ እየተመለከትን ነውና ክርስቶስ ወደ ቤታችን እንዲገባና የትንሣኤውም ምስክሮች እንድንሆን እንለምነው!

አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል”  ብሎ እንደ ነገረን አምላካችን ዘወትር ከደጅ ቁሞ እያንኳኳ ነውና የልባችንን በር እንክፈትለት፡፡ (ራእ.፫፥፳) “የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ግባ! ሰላምንም አድለን” እንበለው። ያኔ ዓይናችን ይገለጣል፤ መንገዳችን ይቀናል፤ ሕይወታችን ይታደሳል፤ ያዘነው ከኀዘናችን እንረጋጋለን፤ ተስፋ የቆረጥን ተስፋችን ይለመልማል!

በመንገዳችን፣ በኑሮአችንና በሕይወታችን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ አይለየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለመስቀሉ ክቡር

ወለወላዲቱ ድንግል አሜን!!!