የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት አቋቁማ መደበኛ የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቈጥረዋል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አጀማመርና ጠቅላላ አገልግሎት በአጭሩ የሚያስቃኝ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!

በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ታሪክ እንደሚታወቀው ያልተበረዘና ያልተከለሰ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ሥርዓተ አምልኮ፣ የትርጓሜና የባሕረ ሐሳብ ትምህርት፣ በብራና የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ መሥዋዕተ ኦሪት ይቀርብባቸው የነበሩና እስከ አሁን ድረስ ተጠብቀው የቆዩ ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት፣ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶች፣ ሥርዓተ ማኅሌትና የመንፈሳውያን በዓላት አከባበር ሥርዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በሙሉ ዓለምን የሚያስደምሙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሀብቶችና ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በመጽሐፋቸው እንደ ጠቀሱት ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፣ እምነት፣ ነጻነት፣ አንድነት፣ የአገር ፍቅር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበረከተቻቸው ብዙ ስጦታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ማብራሪያ አሁንም ቢኾን ትውልዱ ጀግንነትን፤ አገር ወዳድነትን፤ ለሃይማኖት፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ረገድ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ አላት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ካሁን በፊት በየጊዜው የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቃል በማስተማርና መጻሕፍትን በማሳተም እነዚህን ሀብቶቿን ለመጠበቅና ለዓለም ለማስተዋወቅ ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ከኅትመት ውጤቶች ባሻገርም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ቃለ እግዚአብሔር ለማስተማር ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ብዙ ደክመዋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ባይሰጥም ቀደም ሲል የተጀመረው የሬድዮ መርሐ ግብር እንደዚሁም አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት መንፈሳዊ መጽሔቶች፣ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃንን በተለይም የቴሌቭዥን ሥርጭትን በመጠቀም ረገድ እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያሉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን በመክፈት ትምህርተ ወንጌልን በመላው ዓለም በማዳረስ ላይ ትገኛለች፡፡ በምእመናን ብዛት ከኢትዮጵያ ብዙ እጥፍ የምታንሰዋ ግብጽ በዚህ መልኩ የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ ከኾነች ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ብቻ ሳይኾን በርካታ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓት አያጠያይቅም፡፡ ይህን እውነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዓመታት በፊት የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ማሠራጨት ጀምራለች፡፡

በ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት እንደ ተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት እንዲቋቋም ለማድረግ ጥናት እንዲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው በጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነው፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ ሦስት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በርካታ ባለሙያዎችና ሊቃውንት የተሳተፉበት ጥናት ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ፣ የአርትዖትና የቴክኒክ መመሪያ ጸድቆ ሥራው እንዲጀመር ተወስኗል፡፡

ድርጅቱ፣ በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመው የቦርድ ሥራ አመራር ከአንድ ዓመት በላይ ተጨማሪ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በጥቅምት ወር ፳፻፰ ዓ.ም ለሥራው የሚያስፈልገው በጀት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖለታል፡፡ ቦርዱ የተፈቀደውን በጀትና የተጠናውን ጥናት ወደ ተግባር ለመለወጥ ውድድር በማድረግ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲቀጠር አድርጓል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ መመሪያ ሰጭነት አስፈላጊ ቅድመ ኹኔታዎችን በሟሟላት፣ ተደጋጋሚ ውይይቶችንና ዓለም አቀፍ ዳሰሳዎችን በማድረግ ለሥርጭቱ ያመነበትን የሳተላይት ጣቢያ አወዳድሮ በመምረጥና የውል ስምምነት በማዘጋጀት በአፋጣኝ የሥርጭት አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡ በኢየሩሳሌም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረትም የቴሌቭዥን መርሐ ግብራቱ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ኢየሩሳሌም በሚገኘው የሳተላይት ድርጅት አማካይነት ይሠራጫሉ፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያው የሥርጭት አድራሻም የሚከተለው ነው፤

Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Television (EOTC TV)

Satellite: Eutelsat/Nilesat (ኢትዮጵያ)

Frequency …. 11353 (5) Vertical

Symbol rate …. 27500/FEC…5/6

Satellite: Galaxy 19 (G-19) (ሰሜን አሜሪካ)

Frequency …. 11960/Vertical

Symbol rate …. 22000/FEC…3/4

የድርጅቱ መዋቅርና አገልግሎት የተሟላ እንዲኾን በአስተዳደርና ፋይናንስ፣ በመርሐ ግብር ዝግጅት እና በቴክኒክ ዘርፍ ቦርዱ በሰየማቸው የቅጥርና የምዘና ኮሚቴ አባላት አስፈጻሚነት የሠራተኞች የቅጥር ሒደት ተከናውኗል፡፡ በቅጥር ሒደቱም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ላመለከቱ ሠራተኞችና ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡ የሥርጭቱን አጠቃላይ ይዘትና ዓይነት በተመለከተም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቦርድ አባላትና የሚዲያ ባለሙያዎች የሚገኙበት የይዘትና የዓይነት ዝግጅት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ይዘቱንና ዓይነቱን የሚያርምና የሚገመግም የኤዲቶሪያል ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ የኤዲቶሪያል ኮሚቴው አባላትም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪጁ የተሰየሙና በቦርዱ የተመረጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ድርጅቱ ካለበት ሠፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አኳያ በቋሚነት የሚያስፈልጉት በርከት ያሉ ስቱዲዮዎች፣ የቅድመ ሥርጭትና ድኅረ ሥርጭት ተግባራት ማከናወኛነት የሚያገለግሉ በርካታ ክፍሎች፣ አብያተ መዛግብት፣ አስተዳደርና የባለሙዎች ቢሮዎች እንዲሟሉ ለማድረግ ድርጅቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መመሪያን በመቀበል በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

(ምንጭ፡- ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ፱ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፲፪፤ ጥቅምት ፳፻፱ ዓ.ም፣ ገጽ 77-78)፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያኽል፣ የሥልጣኔ ውጤቶች በተበራከቱበትና አብዛኞቹ ወጣቶች ዓለማዊ መልእክት በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ውስጥ በወደቁበት በአሁኑ ዘመን ወጣቱን ትውልድ ወደ ጥፋት ከሚወስዱ መልእክቶች ለመታደግ ያመች ዘንድ ትምህርተ ወንጌልን ለማዳረስና ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትን ለማስተማር፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓተ እምነት፣ ትውፊትና ልዩ ልዩ ሀብቷን ወይም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ለትውልድ ለማቆየት ብሎም ለዓለም ለማስተዋወቅ፤ እንደዚሁም በየጊዜው በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ መመሪያዎችንና መልእክቶችን በአፋጣኝ ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙኃንን፣ ከመገናኛ ብዙኃንም የቴሌቭዥን ሥርጭትን መጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

በዚህ ዓላማ መሠረት የተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ሥርጭትም በልዩ ልዩ ዓምዶቹ ትምህርተ ወንጌል በመስጠት፤ ቅዱሳት መካናትን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶችን በማስተዋወቅ፤ ጠቃሚ የኾኑ ማኅበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማቅረብና መንፈሳዊ ዜናዎችን በመዘገብ አገልግሎቱን እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስቀጠልና ለምእመናን ለማዳረስ ይቻል ዘንድም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ሐሳብ አስተያየት በመስጠትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ በተቻለን አቅም ዂሉ የቤተ ክርስቲያናችንን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት በመደገፍ የሚጠበቅብንን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት እንወጣ ሲል የማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል መንፈሳዊ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡