የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መዋቅራዊ ለውጡን እንደሚደግፉ አስታወቁ

ጥር 9/2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

• “የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያኗ የምታምንባችሁ፤ እናንተም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ ልጆች እንደሆናችሁ እናምናለን፡፡” /ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ /
• በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን ሙስና፤ ዘረኝነት፤ ብልሹ አሠራሮች አንገታችንን ደፍተን እንድንሔድ አድርጎን ነበር፡፡/የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች/

የአዲስ አባባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሓላፊዎችና አባላት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተንሠራፋውን ብልሹ አስተዳደር፤ ሙስናና ዘረኝነትን ያስተካክላል ተብሎ የተዘጋጀውን አዲሱን መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚደግፉ ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሸ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስታወቁ፡፡

ተወካዮቹ በመግለጫቸው “በርካታ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እስከ እስር ድረስ በመድረስ ሲታገሉለት የነበረውንና አይነኬ የሚመስለውን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የተንሰራፋውን ብልሹ አሠራርን እናወግዛለን፡፡ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥም በግንባር ቀደምትነት እንሰለፋለን፡፡ እስካሁን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን ሙስና፤ ዘረኝነት፤ ብልሹ አሠራሮች አንገታችንን ደፍተን እንድንሔድ አድርጎን ነበር፡፡ ዛሬ የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ደርሷል፡፡ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያናችን ክብር እንደሚመለስልን እናምናለን፡፡ እኛም ከቅዱስነትዎና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅብንን ለማበርከት ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረጉ ብልሹና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ሲፈጸሙ በመጋፈጥ ፊት ለፊት በመናገራቸው አንዳንድ የደብር አለቆችና ጸሐፊዎች በቀጥታ ለፖሊስ በመጻፍ አባላት እየተደበደቡና እየታሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት አባላቱ አንዳንድ ፖሊሶችም ጉዳዩን ሳያጣሩ የድርጊቱ ተባባሪ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ማሳያነት በአሁኑ ወቅት በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ችግር በተወካዩ አማካይነት አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አማካይነት ለቅዱስ ሰሲኖዶስ ቀርቦ የነበረውና በእንጥልጥል የቀረው የተሐድሶ መናፍቃንን ጉዳይ በተመለከተ ተጨባጭ መረጃዎችን ማቅረባቸውንና የተወሰኑ ግለሰቦችና ማኅበራት ተወግዘው መለየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ውሳኔ ሳይሰጣቸው የቀሩ ግለሰቦችና ማኅበራት ስለሚገኙ በቀረበው ማስረጃ መሠረት ጉዳዩ ታይቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል፡፡

 

መናፍቃኑ በየብሎጎቻቸው ቅዱሳንን እየተሳደቡ እንደሚገኙና በአሁኑ ወቅት የገጠር አብያተ ክርስቲያናትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ በመዝመት የራሳቸውን መምህራንን በማሰልጠንና በመቅጠር ወረራ እያካሔዱ እንደሚገኙ በመጥቀስ መፍትሔ እንዲፈለግለት አሳስበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያኗ የምታምንባችሁ፤ እናንተም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ ልጆች እንደሆናችሁ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ሰንበት ትምህርት ቤት ዓለማቀፋዊ ነው፡፡ ሁሉም ወጣት በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲታቀፍ ነው የምንመኘው፡፡ መበርታት አለባችሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተደነቀረውን መሠናክል የገንዘብ ብክነት፤ የአስተዳደር ብልሹነትን ለመቅረፍና አማሳኞችን ለመታገል እናንተ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት መዝመት አለባችሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሀብት ባክኗል፤ መልካም አስተዳደር የለም፤ ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል፡፡ ሃቀኝነት አይታይም፡፡ ይህንን ለመከላከል ትጉ” ብለዋል፡፡
ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ የሚያስተምሩና ችግር የሚፈጥሩ ካሉ በተረጋገጠ መረጃ አስደግፈው ማቅረብ እንደሚገባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፤ የማኅበራት ደንብን አስመልኮቶ ወጣቱ በአንድ ሕግ፤ በአንድ ሰንበት ትምህርት ቤት መታቀፍ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ጉዳይ ዝም ብላ እንደማትመለከተው አሳስበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በየአጥቢያው የሚፈጠሩ ችግሮች ምን እንደሆኑ መታወቅ እንዳለባቸው በመግለጽ “ለምንድነው የምትታሰሩት? ማነው የሚያሳስራችሁ? ተጽእኖስ ለምን ይደርስባችኋል? ይህ ጉዳይ መጣራት አለበት፡፡ ችግሩ የማነው? ከነማስረጃው አቅርቡ፤ ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ ትሰጣለች፡፡ ልጆቿን ዝም ብላ አሳልፋ አትሰጥም” ብለዋል፡፡