የአሜሪካ ማእከል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያንን አሠለጠነ

የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ሥልጠናዉን የወሰዱ ሰባክያነ ወንጌል ከአሠልጣኞቻቸው ጋር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርተ ወንጌል ማስተማር የሚችሉ ሰባክያንን አሠለጠነ፡፡

በማእከሉ የትምህርት፣ ስብከተ ወንጌል እና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል በተዘጋጀው በዚህ ሥልጠና ከዐሥር ከሚበልጡ የአሜሪካ ክፍላተ ግዛት ከየንዑሳን ማእከላት እና ሌሎች ማኅበራት የተወከሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

በዋና ክፍሉ ሪፖርት እንደ ተገለጸው የሥልጠናው ዓላማ ሠልጣኞቹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወንጌልን ሊያዳርሱ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማገዝ ሲኾን፣ ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ)፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን እና የስብከት ዘዴ በሥልጠናው የተካተቱ የትምህርት ክፍሎች ናቸው፡፡ ሥልጠናው የተሰጠውም በዲሲና አከባቢው ሀገረ ስብከት በአትላንታ ጆርጅያ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ከየካቲት ፱-፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ነው፡፡

ለሦስት ቀናት በቆየው በሥልጠናው ቀሲስ ሰይፈ ሥላሴ ከኒውዮርክ፣ ዲ/ን ዶ/ር ብዕለ ጸጋ ከፊኒክስ፣ ዲ/ን ዓለማየሁ ከዳላስ ሥልጠና በመስጠት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከሥልጠናው ጎነ ለጎን ወቅታዊ የተተኪ ትውልድ አያያዝ እና የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲኾን፣ በውይይቱ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ የሠልጣኞቹን አስተያየት ዋቢ በማድረግ የአሜሪካ ማእከል ጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም በአትላንታና አከባቢው ለሚገኙ ወጣቶች የሁለት ቀን ትምህርታዊ ጉባኤ በአትላንታ ንዑስ ማዕከል ግቢ ጉባኤና ተተኪ ትውልድ ክፍል ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲኾን የአትላንታ ንዑስ ማእከል ያነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊ ወጣቶች በቀሰሙት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ልዩ ልዩ ተሳትፎ በማድረግ ለሥልጠናው አገልግሎት መሳካት ድርሻቸውን ለተወጡ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፤ ለደብሩ ሰ/ት/ቤት፤ ለአትላንታ ደ/ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ወቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሰ/ት/ቤት፤ ለአትላንታ ደ/ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት፤ ለአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሰ/ት/ቤት እና ለቀሲስ ኃይሌ የማእከሉ የትምህርት፣ ስብከተ ወንጌል እና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል በማኅበረ ቅዱሳን ስም መንፈሳዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠው የተተኪ መምህራን ሥልጠና ለወደፊትም እንደሚቀጥልና ከዚህ በፊት ሥልጠናውን ያልወሰዱ ሰባክያን ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ሥልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የአሜሪካ ማእከል አስታውቋል፡፡

ዘገባውን ያደረሰን በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ነው፡፡