‹‹የቅድስት ማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል›› ቅዱስ ያሬድ

ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፤ የቅድስት ማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል›› በማለት የመሠከረው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ነው፡፡ እርሷ በምድር ላይ በአይሁድ ክፋት ብዙ መከራና ኃዘን ካሳለፈች በኋላ በዘመነ ሉቃስ፣ ጥር ሃያ አንድ ቀን፣ በዕለተ እሑድ፣ በስድሳ ዐራት ዓመቷ ወደ ዘለዓለም ደስታ ትገባ ዘንድ ዐርፋለችና፡፡ (ጾመ ድጓ)

በዚህች የተቀደሰች ቀንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክቱን አስከትሎ ‹‹እናቴ ሆይ፥ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ›› አላት፡፡ ‹‹ልጄ፥ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕፀኔ ተሸክሜህ፤ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁ?›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ ‹‹እናቴ ሆይ፥ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹እነዚህን ከማርክልኝስ ይሁን›› አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅድስት ነፍሷ ለይቶም በዝማሬ መላእክት ዐሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት በማድረስ እመቤታችንን እንዲቀብሩአት አዘዛቸው፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)

ሐዋርያትም ሊቀብሩዋት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሴማኒ ይዘው በመሄድ ላይ ሳሉ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ‹‹ከዚህ አስቀድሞ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ያልተነሣውን ተነሣ፤ ያላረገውን ዐረገ እያሉ ሲያውኩንና ሲያስቸሩን ኖረዋል፤ አሁን ደግሞ እርሷ ተነሣች፤ ዐረገች፤ እያሉ ያውኩን አይደለምን? በእሳት አስከሬኗን እናቃጥለው›› ብለው ተሰብስበው ሄዱ፤ ከመካከላቸውም ታውፋንያ የሚብለው አይሁዲዊ ተራምዶ የእመቤታችንን አስከሬን አጎበሩን ጨበጠው፤ የታዘዘ መልአክ በሰይፍ ሁለት እጁን ሲሰይፈው እጁ ከአጎበሩ ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ነገር ግን በሐዋርያት ጸሎት እጆቹን በተአምራት ተቀጥለው እንደቀድሞው ሆነውለታል፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፤ ሆኖም ሐዋርያት ዮሐንስን እመቤታችን ‹‹እንደ ምን ሆነች?›› ብለው ሲጠይቁት ‹‹በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ናት‹‹ ብሏቸዋል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፤ ፳፩ ቀን)

ከዚህም በኋላ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሁሉ ክብር አይቶ እኛስ አናይምን?›› ብለው በነሐሴ መጀመሪያ ጾም ያዙ፤ ሁለት ሱባዔ ጾመው በዐሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)

ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና›› ብሎም መሥክሯል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍት በዓል ታላቅ በረከት የምናገኝበት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ (ጾመ ድጓ)
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ ተረዳኢነት፣ ረድኤትና በረከት አይለየን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር