የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ዕረፍት

ሚያዚያ፤፳፻፲፬ ዓ.ም

በሚያዝያ ሃያ ሦስት ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ፡፡

የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው፡፡ ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል፡፡ ከቀጰዶቅያ ሀገር ነው፡፡ የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል። ከፍልስጥዔም ሀገር ናት። ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ፡፡ ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሄደ፡፡ ንጉሡም ጣዖትን እንዲያመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡ ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች፣ ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ፡፡ ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡ ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው። ጌታችን ግን ያጸናዋል ቍስሉንም ያድነዋል። ሦስት ጊዜም እንደሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርን አክሊልን እንደሚቀበል ነገረው፡፡ ቃል ኪዳንም ሰጠው። ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው፡፡

ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ፡፡ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ መልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው፡፡ ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር፡፡ ቅዱሱም ያንን ጽዋ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፡፡ ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ፡፡ ከእርሱም ጋር ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ፡፡ ቅዱሱንም ‹‹እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲያፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን›› አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ ጸለየ። እንዳሉትም አደረጋቸው። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቍጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት፡፡ አቃጥለው አሳርረውም ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ተራራ ላይ በተኑት፡፡ ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው፡፡ ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ፡፡ ቍጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡

ነገሥታቱም ደግመው ‹‹ሙታኖችን ብታሥነሣ አምላክህ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በእርሱም እናምናለን›› አሉት፡፡ ቅዱሱም ጸለየ። ከጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው። እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ። የገሃነምንም ወሬ ተናገሩ። ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ፡፡

ከሀድያን ነገሥታት ግን ‹‹ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ›› ብለው ተከራከሩ፡፡ ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት። እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች። የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት፡፡ የዚያች መበለትም የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ፡፡ ያቺም መበለት በተመለሰች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ ‹‹የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደ እኔ መጣ›› አለች፡፡ ቅዱስም ‹‹እኔ አምላክ አይደለሁም፡፡ የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ›› አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው፤ ‹‹የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ፡፡ ዕውር፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበ፤ ያን ጊዜም አየ፡፡ ቅዱሱም ‹‹በሌላ ጊዜ እንዲሰማ፣ እንዲናገርና እንዲሄድ እንዲያገለግለኝም እኔ እሻለሁ›› አላት፡፡

በዚያን ጊዜ ንጉሡ በሀገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ፤ ስለ እርሷም ጠየቀ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ተቆጣ፤ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው፤ በመንኰራኵርም አበራዩት፤ ሙቶም ከከተማ ውጭ ጣሉት፤ ጌታም ከሞት አስነሣው፤ ወደ ነገሥታቱም ተመለከተ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ፤ ስለ ሕይወቱም አደነቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ፤ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት ‹‹ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ፤ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ፤ እኔ ስሠዋ እንዲያዩ›› አለው፡፡ ንጉሡም እውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው፡፡ ለጸሎትም ተነሣ፤ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ፤ የዱድያኖስ ሚስቱ እለስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት፤ የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመናቸው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እስከሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀመረ፡፡ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡

በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ፤ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ እውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በአያት ጊዜ ፈገግ አለ፤ ‹‹ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው›› አላት፡፡ ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ ወደ አጵሎን ሂድ፤ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ስም እዘዘው›› አለው፡፡ ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሂዶ አዘዘው፡፡ በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ ‹‹እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም›› ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ፡፡ ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው፤ ጣዖታቱንም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው፤ ንጉሡም ከወገኖቹ ጋር ዐፈረ፡፡ ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ፡፡ እርሷም ‹‹አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አላልኩህምን?›› አለችው፡፡ ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጣ፤ ወደ ክብር ባለቤት ክርስቶስ እምነት የከበረ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፡፡ በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ፤ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲያርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት፡፡ ያን ጊዜም የክቡር ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ ድል አድራጊ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው፡፡ እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው፡፡ ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋር ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ፡፡ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፡፡

ከዚህ በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ በሰይፍ ቆረጡት፤ በመንግሥተ ሰማያት አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ከአገልጋዮቹም የቀሩት ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት፤ ወደ ሀገሩ ልዳም ወሰዱት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጥዋ አኖሩት፤ ከእርሱም ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን። የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን። ለዘላለሙ አሜን፡፡

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሚያዚያ፤ ፳፫ ቀን፡፡