የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ያስገነባው ሕንፃ ተመረቀ

ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

•    የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ 25ኛ ዓመት የብር እዩቤልዩ በዓልም ተያይዞ ተከብሯል

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}abunekerilos{/gallery}

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ያስገነባው ባለ ሁለት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ተወካዮች፣ የመንግሥት አመራር አካላት፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ህዳር 10/2004 ዓ.ም የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና በአቶ ሓየሎም ጣውዬ የወልድያ ከተማ ከንቲባ ተመረቀ፡፡

 

መልአከ ሐይል ስጦታው ሞላ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ኃላፊ  የአዳጎ ሕንፃ መሠራቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በስብከተ ወንጌል የምታደርገውን እንቅስቃሴ በጉልህ የሚደግፍ ነው ብለዋል ፡፡ የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ ሓየሎም ጣውዬ በምረቃው ወቅት ‹‹ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሕዝቡን በእምነቱ የጸና፣ ሀገር ወዳድና በልማት ዋነኛ ተሳታፊ ለማድረግ እያከናወናቸው ያለው አበረታች የልማት ተግባራት መንግሥት ከያዛቸው የድኅነት ማስወገጃ ስትራቴጂዎች አንፃር የሚሄዱ ለመሆናቸው ምስክርነት የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሀገረ ስብከቱ ከጀመራቸው የልማት ሥራዎች መካከል የወልድያ ከተማችን የኢንቬስትመንት እድገት የሚያሠራውን አዳጎ ላይ የተገነባው ሕንፃ ለሌሎችም አርአያ ከመሆን አልፎ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ያለፈና አሁንም እየፈጠረ ያለነው ቢባል መጋነን አይሆንም ›› በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

ቦታው የሀገረ ስብከቱ ይዞታ በመሆኑ፣ በመሐል ከተማ ያለ ሆኖ ሕንፃው መገንባት ስላለበት እንዲሁም በመንግሥት አካላት በሕንፃ እንድትሰሩ እድሉ የእናንተ ነው ስለተባለ፤ ሕንፃውን ልንሠራ ችለናል በማለት መልአከ ሐይል ስጦታው ሞላ ተናግረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሕንፃውን ፕላን በነጻ ሠርቶ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ነው በማለትም አክለዋል ፡፡

 

ሀገረ ስብከቱ ያስገነባው አዳጎ ሕንፃ ባለሁለት ዘመናዊ ፎቅ ሲሆን ስድስት ሱቆች፤ አንድ ካፍቴሪያና ሬስቶራንት ፣ አንድ መለስተኛ አዳራሽ እና ሃያ ስድስት ለጽ/ቤት አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ያሉት ነው ፡፡ ሕንፃውን ለመሥራት ሁለት ዓመት የወሰደ ሲሆን በአጠቃላይም በ3.8 ሚሊዮን ብር ተጠናቋል፡፡

 

ከዚህ በፊት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከበጎ አድራጊዎች ጠይቀው ባገኙት ከ300,000.00 ባላነሰ ወጪ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና (ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ) እንዲሁም የካህናት ማሠልጠኛ በብር 260,000.00 መሠራቱ የሚታወስ ነው፡፡ ተያይዞም የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ላሊበላ ደብር የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓልም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል ፡፡

 

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስበከት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከመሾማቸው በፊት በወሎ ሀገረ ስብከት ሥር የነበረ መሆኑና ብፁዕነታቸው ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ ከህዳር ወር 1980 ዓ.ም ጀምሮ ከሀገረ ስብከቱ ባለመለየት በትጋት የወንጌል አገልግሎታቸውን እየተወጡ ያሉ አባት መሆናቸውን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ዓለሙ አስማረ በወልድያ ከተማ ባህል አዳራሽ በተካሄደው ዝግጅት ተናግረዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ አያይዘው ብፁዕነታቸው ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ቀድሞ አንድ ብቻ የነበረውን ሰ/ት/ቤት አሁን ላይ አራት መቶ ሦስት መሆናቸውን ፣ አራት መቶ ሠላሳ አንድ  መምህራን መሰልጠናቸው፣ ከመቶ 20% ከብር 70,220.41 ወደ ብር 3,236,486.48 ማደጉን፣ በወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ከሠላሳ አራት ወደ ሠባ ስድስት፣ ሀገረ ስብከቱ ሲመሰረት አምስት ሠራተኞች የነበሩ ሲሆን አሁን ሃያ ሁለት ሠራተኞች መጨመሩን፣ አጎራባች አህጉረ ስብከቶችን ሳይጨምር ለሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች 7,618 የዲቁናና የቅስና ማዕረግ መስጠታቸውን፣ በምዕመናን ቁጥር በ173,791 ዕድገት መታየቱን፣ በወረዳ ደረጃ፣ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በኩልና ሐዋርያዊ ጉዞ ያደረጉትን ግልጋሎት በሪፖርት አቅርበዋል፡፡

 

ከበዓሉ ታዳሚዎች ቅኔና መወድስ የቀረበ ሲሆን ምዕመናንም ለብፁዕነታቸው ረጅም የአገልግሎት ዕድሜን ከጤና ጋር እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው ተመኝተዋል፡፡

 

ብፁዕነታቸው ያለባቸውን ከፍተኛ ሕመም በመቋቋም ለሠሩት ሥራም ከልዮ ልዮ አካላት ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም ሙሉ መቀዳሻ አልባስ፣ ቆብና የእጅ መስቀል እንዲሁም ጥና ሲሸልሙ፤ የቅዱስ ላሊበላ ደብር በበኩሉ በትረ ሙሴ አበርክቶላቸዋል፡፡ ተያይዞም በአዳጎ ሕንፃ  አስተዋጽኦ ላደረጉ ልዩ ልዩ አካላት የሽልማትና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

 

በዕለቱም የብፁዕነታቸውን ከልጅነታቸው ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለውን ሐዋርያዊ አገልግሎት የያዘ መጽሔት ለንባብ በቅቷል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ግንቦት 30/1979 ዓ.ም የበዓለ መንፈስ ቅዱስ ዕለት ከአምስት አባቶች ጋር ለጵጵስ  ሹመት የበቁ ሲሆን እንደተሾሙም የተመደቡት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ብፁነታቸው በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አሁጉረ ሰብከት በዋናነት ያገለገሉና እያገለገሉ ያሉ ሲሆን በተጨማሪም የአሰብ፣ የደቡብ ወሎ እና የደቡብ ሸዋ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና ደርበው እንዲሁም በ1986 ዓመተ ምሕረት በምሥራቅ ሸዋ ተዛውረው ለስምንት ወራት አገልግለዋል ፡፡