የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

ክፍል ስድስት

ዲያቆን ዳዊት አየለ

ጥር ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

የቅዱሳት በዓላት አከባበርና ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች

በዓል “አብዐለ” “አከበረ፣ አስከበረ” ካለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን በቁሙ ትርጉሙ “የደስታና የዕረፍት ቀን፣ በዓመት በወር በሳምንት የሚከበር” ማለት ነው፤ በዓላት የሚከበሩ፣ የደስታ ዕለታት፣ የዕረፍት ቀናት፣ የመታሰቢያ ዕለታት በመሆናቸው ነው፤ (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፻፸፬) በአጠቃላይ በዓል ማድረግ ማለት “ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ፣ ማክበር” የሚል ትርጉም አለው።

በዓልን ያስጀመረውና የሠራው ዓለማትን ፈጥሮ የሚገዛ የሁሉ ባለቤት እግዚአብሔር ነው፤ “ሰማይና ምድር ዓለማቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት፤ ቀደሳትም፤ ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በዓልን የጀመረውና የቀደሰው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳየናል፤(ዘፍ.፪፥፩-፫)  የመጀመሪያ በዓልም ሰባተኛ ቀን የተባለችው ቀዳሚት ሰንበት ናት።

በዓል በሚውልባቸው ዕለታት መደበኛ ሥራዎችን አቁመን ለበዓሉ የሚገቡና መንፈሳዊ በሆኑ ክንውኖች ልናሳልፋቸው የሚጠበቅብን ሲሆን በሥርዓቱ መሠረት ልናከብር ይገባናል። በዓል መንፈሳዊ ሥራ የምናከናውንበት ይሁን እንጂ “በሰንበትና በከበሩ በጌታ፣ በእመቤታችንና በሚካኤል በዓላት ስግደት አይሁን፤ እነዚህ የተድላ፣ የደስታ ዕለታት ናቸውና” እንደተባለው በሥጋ ድካም የሚያመጣውን ስግደት እንዳንሰግድ መታዘዛችን በዓል ዕረፍትነቱን ከደስታ ጋር ያስተባበረ መሆኑን ያጠይቃል። (ፍት.ነገ ንባቡና ትርጓሜው ገጽ ፪፻፶፰) ስለዚህም በዓል ከሥጋ ድርጊት ተቆጥበን በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በምስጋና፣ በምጽዋት፣ በጸሎት፣ የታመመንና የታሰረን በመጠየቅና በመሳሰሉት ተግባራት የምናከብረው ነው።

በዓላት ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ›› እንደ ተባለው በዓል የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ ዕለት ሳይሆን ደስ የሚሰኙበት፣ በደስታ ውስጥም ሆነው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቀን ነው፡፡ (መዝ.፵፩፥፭) ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ደስ ያለው ይዘምር›› እንዳለው የደስታ ቀን በሆነው በበዓል ስብሐተ እግዚአብሔር በስፋት ይቀርባል፡፡ (ያዕ.፭፥፲፬) ትልቁ የደስታ ምንጭ መብል መጠጡ፣ ዘፈን ጨዋታው ሳይሆን መንፈሳዊ ምግብ መመገቡ፣ ይልቁንም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመቀበል መብቃቱ ነው።

እግዚአብሔር እርሱ ለሠራው ድንቅ ሥራና በቅዱሳኑ አድሮ ለሠራው ሁሉ መታሰቢያ (በዓል) ይደረግለታል፤ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ከሥራው ያረፈባትን የሰንበት ዕለት እንድናስባት አዝዞናል፡፡ ተአምራት ያደረገባቸውን፣ እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣበትንና የመሳሰሉትን ሁሉ በበዓላት እንዲታሰቡ አዝዟል፡፡ (መዝ.፻፲፥፬) በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት አዝዟል፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፲፱) የፈጣሪን ሥራም ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን ጻድቃንንና ሥራዎቻቸውን መዘከር የበዓላት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለለም ይኖራል›› ተብሎ መጻፉም ስለዚህ ነው፡፡ (መዝ.፻፲፩፥፮) ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በዓል ስለሚደረግባት ዕለት ይበልጥ አጽንዖት ሲሰጥ እንዲህ ይላል፤ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች፤ ሐሴትን እናድርግ፥ በእርሷም ደስ ይበለን” በማለት በዓላት የሚውሉባቸውን ዕለታት በዕረፍት፣ በመታሰቢያነት፣ በምስጋናና በደስታ የሚከበር መሆኑን ያስረዳል። (መዝ.፻፲፯÷፳፬)

በብሉይ ኪዳን የበዓላት መጀመሪያ ከሆነችው ከቀዳሚት ሰንበት ጀምሮ እስራኤላውያን የሚያከብሯቸው ከዐሥር የማያንሱ በዓላት ነበሩ፤ እነዚህም ቀዳሚት ሰንበት፣ ፋሲካ፣ በዓለ ሠዊት (የመከበር በዓል)፣ በዓለ መጸለት (የዳስ በዓል)፣ መለከቶች የሚነፉበት ቀን፣ የማስተሥረያ ቀን፣ በዓለ ፉሪም (ይህ በዓል እግዚአብሔር መርዶክዮስንና ወገኖቹ እስራኤልን በሐማ ተንኮል ከመጥፋት አድኖአቸዋልና በመርዶክዮስ ትእዛዝ እስራኤላውያን የሚያከብሩት በዓል ነው። (አስ. ፱ ፥ ፳-፳፰)፣ በዓለ ኅድገት (ይህ በዓል ሁሌ ከ፮ ዓመታት በኋላ ሰውም መሬትም የሚያርፉበትና ለድኆች ገቦውን እንዲበሉ የሚፈቀድበት በዓል ነው።(ዘፀ.፳፭፥፩-፯) የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ በዓል፣ ኢዮቤል(ዩ) እና መባቻ ናቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ሲነግረው “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የተቀደሰ ጉባ ብላችሁ የምታውጇቸው በዓላቶች የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው፤ ሙሴም የእግዚአብሔር በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ” ተብሎ እንደተጻፈ የበዓላቱ አዛዥ ሥርዓታቸውንም የሠራው እግዚአብሔር አምላክ ነው። (ዘሌ.፳፫፥፩-፵፬)

እግዚአብሔር በዓላቱን እንዲከበሩ የሚገባውን ሥርዓትና መንገድ ቢያመለክታቸውም እስራኤላውያን ሙሉ በሙሉ በሕጉና በሥርዓቱ ሄደዋል ማለት አይቻልም። እግዚአብሔር በዓላት እንዲከበሩ ያዘዘው ተግባረ ሥጋን በመተው፣ ልዩ መሥዋዕት በማቅረብ፣ ወደ ቤተ መቅደስ በመውጣት፣ ምስጋና በማቅረብ በመሳሰሉት እንዲሆን ቢሆንም መምህራነ አይሁድ በአብዛኛው የራሳቸውን ወጎች በመጨመር ከበዓሉ ዓላማ ውጭ ያደርጉ ነበር። (“በዓላት” በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ገጽ ፵)

በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ፲፪ ዓመት ሲሆነው አስቀድሞ ይከበሩ ከነበሩ በዓላት አንዱ የሆነውን ፋሲካ ለማክበር እንደ ሥርዓቱ ከእናቱ ከእናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተዋል፤ በዚያም ከበዓሉ በኋላ ጌታችን ከአይሁድ መምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው በማስተዋሉ እያስገረማቸው ተገኝቷል፤ እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን፥ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፥ ‘ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ’ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፥ ‘የቤትህ ቅናት በላኝ’ የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ” እንዳለውና በሌላም ቦታዎች በዓላት ላይ ጌታ ተገኝቶ ባደረጋቸው ነገሮች በዓላት በሐዲስ ኪዳን የሚኖራቸው አከባበር ከብሉይ ኪዳን የሚለይ፣ የሚበልጥና በክርስቲያናዊ ሥርዓት እንደሚከበሩ አስተምሮናል። (ዮሐ.፪፥፲፫-፲፰)

በሐዲስ ኪዳን በዓላትን እንደሚታሰበው አካልና እንደ በዓሉ ባለቤት፣ እንደሚውልበት ዕለትና እንደሚፈጸምባቸው ጉዳይ ወይም እንደ አከባበራቸው ሳምንታዊ፣ ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓላት ብለን ከፍለን እናከብራቸዋለን። በሐዲስ ኪዳን የሚከበሩና መታሰቢያ የሚደረግባቸው በዓላት ቀዳሚት ሰንበት፣ ሰንበተ ክርስቲያ(እሑድ)፣ የጌታ ዐበይት በዓላት (በዓለ ትስብእት ወይም ብሥራት፣ በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ደብረ ታቦር፣ በዓለ ሆሣዕና፣ በዓለ ስቅለት፣ በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ዕርገት፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይም ጰንጠቆስጤ)፣ የጌታ ንዑሳን በዓላት (ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ግዝረት (ልደተ ስምዖን)፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ዘይት፣ መስቀል)፣ ሰሙነ ሕማማት፣ ዘመነ ትንሣኤ፣ በዓላተ ቅዱሳን (እመቤታችን፣ መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት) እነዚህ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ሰፊና የራሳቸው የሆነ ልዩ ልዩ የአከባበር መንገድ አላቸው። (“በዓላት” በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ገጽ ፻፴፩-፻፴፬)

በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበሩ በዓላት ሁሉም የራሳቸው የሆነ ክብርና አከባበር አላቸው፤ ነገር ግን ሁሉንም በዓላት በሥርዓቱና በሕጉ እንድናከብር መሆኑ አንድ ያደርጋቸዋል፤ በዓላትን ስናከብር አስቀድሞ መግቢያ ላይ እንደጠቀስነው ለበዓላቶቹ በሚገባ ሥርዓት፣ ክብርና ቦታ ልናከብር ይገባል፤ ይልቁንም እኛ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ክርስቲያን ነንና በክርስቲያናዊ መንገድ ልናከበር ይገባል።

በዓላት የደስታና የዕረፍት ቀናት ናቸውና በፍጹም ደስታ ሊከበሩ ይገባል፤ በርግጥ ደስታው የሥጋ መሻትንና የዓይን አምሮትን በማሟላት ሥጋዊ ደስታን በማድረግ አይደለም፤ ይልቁንም ፈሪሃ እግዚአብሔር ባልተለየው መንፈሳዊ ሐሴት መሆን ይገባዋል እንጂ። የሥርዓቱ ሁሉ ምንጭ በሆነው ፍትሐ ነገሥትም “ረብሕ ጥቅም የሌለው ነገር ልትናገሩ፣ የማይገባ ሥራ ልትሠሩ አይገባም፤ ይልቁንም መንፈሳዊ ተድላ ደስታን ልታደርጉባት በሚገባ በዕለተ እሑድ ረብሕ ጥቅም የሌለው ነገር ልትናገሩ አይገባም” በማለት እንደተጻፈልን ሁሉንም በዓላት በሚገባና ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ ደስታ ልናከብር ይገባል። (ፍት.ነገ ትርጓሜው ገጽ ፻፶፱)

በዘመነ ሐዲስ የምንኖርና ክርስቲያን የሆንን ሁሉ በዓላትን ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ መልኩ ልናከብር ይገባል፤ “ሁል ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ። እንኳን ክርስቲያን አሕዛብም በዓል በሚያደርጉበት ቀን ከመሰብሰብ ወደ ኋላ እንዳይሉ እነሆ እናያቸዋለን፤……አንተ ምመን ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣት ወደ ኋላ የምትል ወዴት ነበርክ? ምንስ ሠራህ? ባለህ ጊዜ ለፈጣሪህ ምን ልትመልስ ነው” ተብሎ እንደተነገረን በዓልን በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን ጊዜያችንን ለሚጠይቀን ጥያቄ ምላሽ የሚሆኑ በጎ ነገሮችን በማድረግ ልናከብር ይገባል። (ፍት.ነገ. ምን አለ? ገጽ ፪፻፴፯)

በዓላትን በምናከብርበት ዕለት ከሚጠበቁብን ዋና ዋና ነገሮች መካከል አንዱ ለሰዎች ምሕረት ማድረግ ነው። ምሕረትን የምናደርገው ምሕረት ለማግኘት ነው፤ ይቅር ካላልን ይቅር እንደማንባል ተነግሮናልና። ምሕረት ማለት የበደለንን ይቅር ማለት ወይም የበደልነውን ይቅርታ መጠየቅ ብቻ አይደለም ይልቁንም በበዓል ቀን እንዲደረግ የሚጠበቀው ምሕረት ከሱም ከፍ ይላል ይህም ምጽዋት፣ ዕዳ ብድር ቢቻል መተውን ባይቻል በዕለቱ አለመጠየቅን የሚመለከት ነው። ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት “ለፍርድ ሥልጣን ያላቸው ዳኞች እሑድ ቀጥረናችኋል አይበሉ። እሑድ ቀን አያሟግቱ፤ አይፍረዱ፤ ማንም ገንዘቤን አምጣ ብሎ አይያዝ ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሂዱ እንጂ” ባሉት መሠረት ሊሆን ይገባል በዓል አከባበራችን። (ፍት.ነገ.አን.፲፱)

የሰው ልጅ በማንኛውም ቀን፣ ሁኔታና ቦታ ከኃጢአት ራሱን መጠበቅና ማራቅ የሚጠበቅበት ሲሆን በዓሉን ሲያከብርም በዓላቱ ሊከበሩ በሚገባቸው መልኩ ባለ ማክበርና ለሥጋ ፍላጎት በማድላት ከሚመጣበት ኃጢአት ራሱን እየጠበቀ መሆን አለበት። በዓሉንም አስታኮ ከመጠን በላይ መብላት፣ ከሚገባው በላይ መጠጣትና መስከር፣ መዝፈን፣ መጨፈር፣ ዋዛ ፈዛዛ ነገር መጨዋወት፣ ሐሜት ከመሳሰሉት ሁሉ በመራቅ በንጽሕና፣ በቅድስና፣ በሕግና በሥርዓት፣ በደገኛው ትውፊት ማክበር ይገባናል።

የቅዱሳንን በዓል በምናከብርበት ወቅት እንዲሁ ልንፈጽመው ከሚገባን ውስጥ አንድ የቅዱሳኑን ሕይወት፣ ተጋድሎና ሰማዕትነት ማሰብ፣ ማሰላሰልና መዘከር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ ዐስቡት። ገና አልጸናችሁምና ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኃአትን ተጋደሉአት፥ አሸንፉአትም፤ ተስፋችሁን የምታገኙባትን ትምህርትም ውደዷት” (ዕብ.፲፪፥፫-፭) እንዲሁም በተጨማሪ “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው” (ዕብ.፲፫፥፯) የሚለው የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምክሮች የሚያስተምሩን ኃጢአትን አሸንፈው የጸኑትን ቅዱሳን ሕይወታቸውን ማሰብ፣ መመልከትና ማሰላሰል እጅጉን ጠቃሚና የሚገባ እንደሆነ ነው፤ ይህም ከቅዱሳን በረከታቸውን እንድንሳተፍ ከማድረጉም በላይ በሚደርስብን ሁሉ እየታገሥን ፈተናን ድል እንድንነሣና ለክብር እንድንበቃ ይረዳናል። ስለዚህም በቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳኑ የሚናገሩ ድርሳናትን፣ ትምህርታቸውን፣ ምስክርነታቸውንና ተጋድሎአቸውን በመስማት ብቻ ሳይሆን በማሰብና በማሰላሰል በዓላቸውን ልናከብር ይገባል፤ ይህም የእኛ የምእመናን ድርሻ ነው።

ሁላችንም ምእመናን እንደ ሥርዓቱና በእያንዳንዱ በዓል እንደ ድርሻችን ማኅሌት በመቆም፣ ቅዳሴ በማስቀደስ ቃለ እግዚአብሔርን በመማርና በመተግበር የምናከብር ከሆነ ከበዓሉ በረከት፣ ፍጹም ደስታ፣ ዕረፍት፣ ከድል ነሺዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ መሆንንና ሰማያዊ ሀብትን እናገኛለን፤ ከሥርዓቱ በወጣ መልኩ ማክበር እና ልናከብር የሚገባውን በዓል መሻር ሁለቱም ከረድኤተ እግዚአብሔር ይለያሉ፤ እንዲሁም ቅጣትን ያስከትላሉ። እኛም በሕጉና በሥርዓቱ አክብረን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!

ይቆየን!

ምንጭ፦ በዓላት በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ፣ ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ ፍትሐ ነገሥት ምን አለ? በመምህር በጽሐ ዓለሙ