የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን ከምን ይጀምራል?

መስከረም ፲፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ቤት ናት፡፡ በቤታችን ሁላችንም የሥራ ድርሻ እንዳለን ሁሉ በመንፈሳዊት ቤታችን በቤተ ክርቲያንም እንዲሁ ሁላችንም ድርሻ ሊኖረን ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሊቀ ጳጳሳት፣ የካህናት እና በቤተ ክርስቲያን በአስተዳደር ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ቤት ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ቤት ናት፡፡ እንደውም ከምንም በላይ አምላክ በቸርነቱ በሚሰጠን የመዳን ዕድል በትጋት በመጠቀምና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድርሻችንን በመወጣት የራሳችንን መዳን መፈጸም ይኖርብናል፡፡ ‹‹በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ›› ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ (ፊል.፪፥፲፪)

ቤተ ክርስቲያን ስንል በትርጉም ሕንፃውን፣ የክርስቲያኖችን ኅብርት (አንድነት) እና የእያንዳንዳችን የምእመናን ሰውነትን ያጠቃልላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በትርጓሜ የእኛን ሕይወት የሚወክል እንደመሆኑ የቤተ ክርስቲያን እድገት በእኛ የሕይወት ለውጥ ላይ የሚወሰን ይሆናል። በዚህም ምእመናን በሕይወታችን የምናሳየው መንፈሳዊ ለውጥ ትልቁና ዋናው በቤተ ክርስቲያን የምንወጣው ድርሻችን ይሆናል፡፡ ይህን ድርሻ ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማሳደግ በመትጋት መፈጸም እንችላለን፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ተግባራት ብንፈጽም መልካም ይሆናል፡፡

፩. ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም በመጸለይ

ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር (፻፳፩፥፮) ‹‹ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ›› እንዳለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በአባቶቻችን ካህናት አማካኝነት ዕለት ዕለት በሥርዓተ ቅዳሴያችን ‹‹ሐዋርያት ሰለሰበሰቡዋት በእግዚአብሔር ዘንድ የቀናች ስለሆነች ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ›› እያለች እኛን ምእመናን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንጸልይ ታስተምረናለች፡፡ ይህም እኛ ምእመናን በእናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖረን የሚገባ ትልቅ ድርሻ ነው፡፡ ቅዱስ ማር ይስሐቅም ‹‹ወተናገር ምስለ እግዚአብሔር ልዑል ከመ ዘይትናገር ወልድ ምስለ አቡሁ፤ በጸሎት ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ተጫወት (ተነጋገር)፤ ልጅ ከአባቱ ጋር እንዲጫወት›› ባለው መሠረት ይልቁንም በዘመናችን በእናት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እኛ ምእመናን በተሰበረ ልብ ወደ አምላክ በመጮኽ ከመናገር በላይ ትልቅ ድርሻ ሊኖረን አይችልም፡፡ (ማር ይስሐቅም ገጽ ፴)

፪. ቃለ እግዚአብሔርን በየዕለቱ በመማርና በማንበብ

ክርስቲያን መሆን የተግባር ሰው መሆን፣ ከማመን ባለፈ የምግባር (የሥራ) ሰው መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየዕለቱ ቃለ እግዚአብሔርን ማንበብና ከመምህራን እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር እና መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለመንፈሳዊ እድገት ጥረት የምናደርግ፣ የሃይማኖታችንን ዶግማና ቀኖና ጠንቅቀን የምናውቅ፣ ለምንጥየቀው ሁሉ አጥጋቢ ምላሽ የምንሰጥ፣ በአጠቃላይ የተሟላ መንፈሳዊ ትጥቅ ያለን የእምነት አርበኞች ከሆንን አሁንም ቤተ ክርስቲያን ከእኛ የምትፈልገውን ድርሻ ተወጣን ማለት ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፤›› (ኤፌ.፮፥፲፮) ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ብለው ያስተማሩን ቃለ እግዚአብሔርን ማወቅ ከምንም ጋር የማይነጻጸር የምእመናን ድርሻችን መሆኑን ሲነግሩን ነው፡፡ (፩ኛጴጥ.፫፥፲፭) መማራችንና በቃሉ ማደጋችን ትዕግሥተኞችና አስተዋዮች፣ አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳትንም ሆነ ካህናትን ለመተቸት የማንፋጠን እንድንሆን ይረዳናል። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንና በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሰነዘሩ ፍላጻዎችን ከመመከት አንጻር እኛ ምእመናን የድርሻችንን የዕቅበተ እምነት ሥራ መሥራት የምንችለው የእግዚአብሔርን ቃል በየዕለቱ ስንማርና ስናነብ ነው፡፡

፫. በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በአገልግሎት በመሳተፍ

አባቶቻችን ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንን ከእኛ ዘመን ያደረሱት የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ትምህርት በማጥናትና በብዙ መከራና ችግር በእነርሱ እግር ሥር ተተክተው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ መምህራንን በማስተማር ነው፡፡ ዘመኑን ለመዋጀት እና የቤተ ክርስቲያንንም ተልእኮ ለማሳካት ደግሞ ከአስተዳደር አንጻር ምእመናን በተሰጠን ጸጋና ከዓለም በቀሰምነው እውቀት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግና አባቶችን በማገዝ ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።

፬. ንስሓ በመግባትና ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን በመቀበል

አባቶቻችን “ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንዳሉት ምእመናን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል እና ድርሻችንን ለመወጣት የምንፈጽማቸው ተግባራት ሁሉ ሊሠምሩ የሚችሉትና ፍሬ የሚያፈሩት እውነተኛ ንስሓ ስንገባ ነው፤ በመቀጠልም የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ስንቀበል ብቻ ነው፡፡ ወደ ጌታችን ማዕድ መቅረብ በአምላክ ቸርነት ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ከማድረጉም በላይ በምድር የእግዚአብሔር መንግሥት መናገሻ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ተልእኮዋን እንድታሳካ የምንረዳበት ድርሻችን ነው፡፡ የአምላካችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የነፍሳችን ድኅነት ነው፤ ፍጹም ሰላምንም ያድለናል፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምንችለው መጠን አገልግለንና በረከትን አግኝተን እንድንኖር የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ረድኤት፣ የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን አማላጅነት ይርዳን፤ አሜን!

ይቆየን!