የምሕረት ቤት

መጋቢት ፳፭፳፻፲ ..

የፍቅር ባለቤት፣ የምሕረት ጌታ፣ የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት፣ የሰው ልጆች ቤዛ ጌታችን በተወለደባት በኢየሩሳሌም ከተማ በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ የምትገኝ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ቤተ ሳይዳ” በአማርኛው ደግሞ “የምሕረት ቤት” የተባለች የመጠመቂያ ቦታ ነበረች፡፡ ይህች ቅድስት ስፍራ አምስት በሮችና መመላለሻዎች ነበሯት፡፡ በዚያም “እውሮችና አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡” (ዮሐ.፭፥፫) የእግዚአብሔር መልአክም ሰንበት በተባለች ቀዳሚት ዕለት ከሰማይ በመውረድ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ ቀድሞ ወደ ውስጥ የገባ ይፈወሳል፡፡ ይህን ድንቅ የአምላካችን ተአምርና የድኅነት ሥራ በማመን እንዲሁም ቸርነቱን ተስፋ በማድረግ ብዙዎች ተፈውሰዋል፡፡

በቤተ ሳይዳ የሕሙማን መመላለሻ በአንደኛው በርም ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ በሥቃይ የኖረና ከበሽታው ጽናት የተነሣም ስሙ ጠፍቶ በበሽታ ስም “መፃጉዕ” በመባል የሚታወቅ ሰው ነበር፡፡ በዚያም ዘመን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያች ምሕረት በሚደረግባት ቤት ሲያልፍ ይህን በሽተኛ ተመልክቶ ለብዙ ዘመናትም በአልጋ ተኝቶ እንደ ኖረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን” በማለት ጠየቀው፡፡ መፃጉዕም መልሶ “ ‹‹ጌታ ሆይ አዎን! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም እንጂ፤ ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› አለ። ጌታ ኢየሱስም ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፤ ያም ቀን ሰንበት ነበረ፡፡›› (ዮሐ.፭፥፯-፲)

የአምላካችን ምሕረት ብዙ ነውና ምንም የእኛ ኃጢአት ቢበዛ በደላችንን ሳይቆጥር እንደ ቸርነቱ ድኀነተ ሥጋና ድኅነተ ነፍስን የምናገኝበትን መንገድ አዘጋጅቶልናል፡፡ በዓለማችን ዙሪያ ብዙ ቤተ ሳይዳዎች ይገኝሉ፡፡ የጠፋው ግን እምነትና በጎነት ነው፡፡ እስራኤላውያን በብዙ መንገድ ምሕረት ተደርጎላቸው ፈውሰ ሥጋንና ፈውሰ ነፍስን አግኝተዋል፡፡ ከሕመማቸው ተፈውሰዋል፤ ከደዌያቸው ነጽተዋል፡፡ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ የምናገኘው በመሆኑ ልናምን ይገባል፡፡

በሀገራችንም በርካታ ፈውስ የተደረገባቸው የጸበል ቦታዎች እንደሚገኙ አንብበንም ሆነ ሰምተን እንዲሁም አይተን ሊሆን ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እንኳን በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ከሁለት መቶ በላይ የሚያህሉ የጸበል ቦታዎች አሉ፡፡ በእነዚህም ሁሉ አምላካችን ለቅድስት እናቱ እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ ለቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሰማዕታት በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ፈውሰ ሥጋን አድሎናል፡፡ የከበረ ቅዱስ መስቀሉ ግማድ አርፎበት በነበረው በርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዓለም ደረጃ መድኃኒት ባልተገኘለት በኤች አይ ቪ ኤድስ የተያዙ በርካታ ሰዎች ፈውስን አግኝተዋል፡፡ በቅርቡም በመላው ዓለም ተዛምቶ የነበረውና ሚሊዮኖችን የጨረሰው የኮኖና በሽታም ፈውስ ሳይገኝለት ቢቀርም በሀገራችን ግን በጸበል የዳኑ ሰዎች መስክረዋል፡፡ ጌታችን የተጠመቀበት የዮርዳኖስ ውኃ በ ”ግሸን ደብረ ከርቤ” ይገኛል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በሰንሰለት ታስረው ለአስታማሚ አስቸግረው በሕመም የሚማቅቁ በሽተኞች በጻድቁ አባት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም “ደብረ ሊባኖስ” በሚገኘው ጸበል ተፈውሰዋል፡፡

ሰዎች የሥጋ ፈውስን ስናገኝ ማሰብና ማገናዘብ ያለብን ግን አንድ ነገር አለ፡፡ አምላካችን ካለብን ደዌ ሥጋ የሚያድነንና የሚያነጻን በእርሱ እምነት እንዲኖረን ብቻም ሳይሆን ከሃሊነቱን ተረድተን ፈውሰ ነፍስንም እንድናስብ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት ሲያሠቃየን ከኖረ ሕመም፣ በሽታ አልያም ችግር ወይም ሥቃይ መላቀቅ አቅቶን ስንቸገር የኖርን ሰዎች በእምነት ኃይል በአንድ ቅጽበት መዳን ሲቻለን የምንጠራጠር ከሆነ የእምነታችን ጎዶሎነት ለነፍሳችን ድኅነትም ይነሣናል፡፡ መፃጉዕም የገጠመው ይህ ነው፡፡ ጌታችን ይህን ሰው ሊፈውሰው ፍቅዶ “ልትድን ትወዳለህን” በማለት ሲጠይቀው ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ወደ መጠመቂያው ውኃ ሊያስገባው የሚችል ሰው አለመኖሩን ነው፡፡

ጌታችን መፃጉዕን መዳን እንደሚፈልግ ቀድሞ የጠየቀው በኋላ እንደሚክደው ስላወቀ ነው፡፡ አይሁድም ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ያዳነውን አላወቀም፤ ጌታችን በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሠውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያን ያዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና፥ ‹‹እነሆ፥ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ›› አለው፡፡ (ዮሐ.፭፥፲፬) ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአይሁድ ወገን ጋር በመሆኑ የጌታችንን ፊት ጸፍቶ ከሳሹ ሆኖ እስከ መቅረብ ደርሷል፡፡

ከመፃጉዕ ታሪክ ልንማር ይገባል፤ አምላካችን ካለብን በሽታ ፈውሶ ሊያድነን ብቻም ሳይሆን የነፍሳችንን ድኅነት አብልጦ እንደሚሻ መገንዘብ አለብን፡፡ መፃጉዕ ግን ይህን ሊያውቅም ሆነ ሊረዳ ባለመቻሉ አምላክን እስከ መክሰስ ደረሰ፡፡ የምሕረት ሁሉ ባለቤት የሆነውን ጌታን አሳዘነው፡፡ እኛም ከእንዲህ ዓይነት ተግባር ልንቆጠብና የትኛውንም ዓይነት ፈውስ ካገኘን የአምላካችንን አዳኝነት በማሰብ ጊዜያዊ ከሆነው ሥጋ ደዌ መላቀቃችን ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለማዊ ሥቃይ ከሚዳርገን የነፍስ ሕመም ፈውስ ለማግኘት በእምነት ልንኖር ይገባናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት ነውና ፈውሰ ሥጋን ፈውሰ ነፍስን ከእርሱ እንደምናገኝ በማወቅና በመረዳት፣ ለእርሱ በመታመን በሃይማኖት እንዲሁም በበጎ ምግባር መኖር ያስፈልጋል፡፡

የአምላካችን ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!!!