የመዝሙር ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

  በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ 
ሰኔ 29፣ 2003 ዓ.ም
 
ማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የመዝሙር ንዑስ ክፍል የተዘጋጀ የመዝሙር ዐውደ ርዕይ ሰኔ 28/2003 ዓ.ም በሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም እና በመዝገበ ጥበባት ጌትነት በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ላይ ተከፈተ፡፡  
 
የመዝሙሩ ዐውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸዋትወ ዜማ፤ የዜማ ይትበሃል፤ የዜማ (የመዝሙር) መሣሪያዎችና ምሥጢራዊ ምሳሌነታቸውን፤ የአማርኛ መዝሙራት እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙርያ ያከናወናቸው ተግባራትን ያስቃኛል፡፡
በመጀመሪያው ትዕይንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸዋትወ ዜማ በሚል÷ በውስጡ የቅዱስ ያሬድን የዜማ ስልት(ዓይነት)፤ የቅዱስ ያሬድን የዜማ ድርስቶች እና የዜማ ምልክቶች እንዲሁም ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያደረገው አስተዋጽኦ የቀረበበት ነው፡፡ ሁለተኛው ትዕይንት በውስጡ ስለ የዜማ ይትበሃል፣ ምንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ያስቃኛል፡፡ የሦስተኛው ትዕይንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዜማ (የመዝሙር) መሣሪያዎችና ምስጢራዊ ምሳሌነታቸውን የሚቀርብበት ነው፡፡ አራተኛው ትዕይንት ስለ አማርኛ መዝሙር ምንነትን ፣ የመዝሙር ጥቅምን ፣ የአማርኛ መዝሙር አጀማመርና መስፈርቶች ፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና መዝሙርን ሁሉ እንዳገኘን ብንዘምር ምን ችግር ያስከትላል የሚሉ ንዑሳን ርዕሶች ተካተዋል፡፡ የመጨረሻው ትዕይንት ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙርያ ያከናወናቸውን ተግባራት ያስቃኛል፡፡

ዐውደ ርዕዩ አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አሻራ የሆነውን ዜማችንን የሚያሳውቅ፣ የሰንበት ት/ቤቶች መዝሙር አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ እንዲሁም በመዝሙር ዙሪያ ላሉ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ የሚወሰድበት ነው፡፡

በዕለቱ አንዳንድ እንግዶች አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከነዚህ መሀል መዝገበ ጥበባት ጌትነት እንዳሉት ‹‹ያየሁት ለሰሚ ድንቅ ነው፡፡ ብዙዎች ቢያዩት መልካም ነው›› ሲሉ ሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወልደ ቂርቆስ በበኩላቸው ‹‹ያለው የነበረው የቀረበበት›› ዐውደ ርዕይ ነው ብለዋል፡፡

 
ከዝግጅቱ አስተባባሪ ወ/ት ገነት አባተ እንደተረዳነው ዝግጅቱ ከሰኔ 29/2003 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 3/2003 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 ለምዕመናን ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን÷ በመዝጊያው ዕለት ሐምሌ 3/2003 ዓ.ም ከ7፡30 እስከ 11፡30 ለየት ያለ ዝግጅት እንደሚኖር ነግረውናል ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙሪያ ዐውደ ርዕይ ሲያዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡