yeledete 2

የልደት ምንባብ ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ታኅሣሥ 24/2004 ዓ.ም

ይህ ጽሑፍ  ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “መጽሐፈ ምሥጢር”  ምዕራፍ 6 ላይ “የልደት ምንባብ” ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}ledet04{/gallery}

“… እግዚአብሔርም ሳሙኤልን “ልዩ ቅብዓት ይዘህ ወደ ቤተልሔም ሒድና ወደ ዕሤይ ቤት ግባ ከልጆቹ እኔ የመረጥኩትን አሳይሃለሁ” አለው፡፡ ሳሙኤልም ወደ ቤተልሔም ደረሰ ከዕሤይ አጥር ግቢ ገብቶ “ልጆችህን አምጣቸው” አለው፡፡ እርሱም ኤልያብን አምጥቶ ለእግዚአብሔር ሹመት የሚገባ ይህ ነው አለ፡፡ እግዚአብሔርም የመረጥኩት ይህን አይደለም አለው፡፡

ዳግመኛ ሳሙኤል አሚናዳብን አስመጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊትም አቆመው፡፡ እግዚአብሔር “ይህንንም አልመረጥኩትም አለ፡፡ ዕሤይ ስድስቱን ልጆቹን አቀረበለት፡፡  በሳሙኤል ፊትም የእግዚአብሔር ምርጫ በእነርሱ ላይ አልሠመረም፤ ሳሙኤል ዕሤይን “የቀረ ሌላ ልጅ አለህን?” አለው፡፡ እርሱም፡- “ታናሹ ገና ቀርቶአል፣ እነሆም በጎችን ይጠብቃል” አለ፡፡ ሳሙኤልም “በፍጥነት ልከህ አስመጣው” አለው፡፡ ዳዊትን አምጥተው በሳሙኤል ፊት አቆሙት፤ እግዚአብሔር ሳሙኤልን “ያልኩህ ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለ፡፡ (1ሳሙ.16፡1-13)

yeledete 2

በሌላም ቃል “አገልጋዬ ዳዊትን አገኘሁት፤ ልዩ ዘይትንም ቀባሁት ኀይሌ ትረዳዋለች፣ ሥልጣኔም ታጸናዋለችና ጠላት በእርሱ ላይ አይሠለጥንበትም፣ የዓመፅ ልጆችም መከራ ማምጣትን አይደግሙም፣ ጠላቶቹንም ከፊቱ አጠፋለሁ፣ የሚጠሉትን አዋርዳቸዋለሁ፣ ይቅርታዬና ቸርነቴ ከእርሱ ጋር ነው በስሜም ሥልጣኑ ከፍ ከፍ ይላል፤ ግዛቱንም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አደርግለታለሁ፤ ሥልጣኑም ከዳር እስከ ዳር ይሆናል እርሱም አባቴ ይለኛል እኔም ልጄ እለዋለሁ፤ በዐራቱ ማእዘን ከነገሡት ነገሥታት ይልቅ ታላቅ ንጉሥ አደርገዋለሁ፡፡  (መዝ.88፡20-27) በሌላ ቃልም እኔ ለዳዊት ሥልጣንን እሰጣለሁ ለቀባሁት መብራትን አዘጋጃለሁ፤ ጠላቶቹንም የኀፍረት ማቅን አለብሳቸዋለሁ፤ በእርሱ ቅድስናዬ ያፈራል፡፡” (መዝ.131፡17-18) በሌላም ቃል “ቀብቶ ላነገሠው ምሕረትን ያደርግለታል፤ ለዳዊትና ለዘሩ እስከ ዘላለም ድረስ ያደርጋል” ይላል፡፡

ኢሳይያስም “ከዕሤይ ሥር በትር ትወጣለች፣ ከግንዱም አበባ ይወጣል፡፡ በእርሱም  የእግዚአብሔር መንፈስ ያርፍበታል” አለ፡፡(ኢሳ.11፡1) እነሆ የእግዚአብሔር በረከት ወደ ዳዊት ቤት አለፈች፡፡ የዘይት ቀንድ በራሱ ላይ ፈላ፡፡ የመንግሥትም በትር ከቤቱ በቀለች፡፡ ከዘሩ እግዚአብሔር የመድኀኒታችንን ሥልጣን አስነሥቶአልና ዳግመኛ ወደ ገሊላ ነገሥታት አውራጃዎችም አልገባም፡፡ የሄሮድስን ሴት ልጅ አልመረጣትም፡፡ ከታላላቅ የይሁዳ ነገሥታት ይልቅ የድሆችን ሴት ልጅ መረጠ እንጂ እግዚአብሔር ፈጣሪ ሲሆን በሴት ማኅፀን አደረ፡፡ ደም ግባቷን ወድዶ ባፈቀራት ጊዜ በጽርሐ አርያም እናት ትሆነው ዘንድ ወደ ሰማይ አላወጣትም፡፡ እርሱ ራሱ ወርዶ በጠራቢው በዮሴፍ ቤት አደረ /ሰው ሆነ/ እንጂ፡፡ በዚያ ትፀንሰው ዘንድ ወደ ኪሩቤል ሠረገላ ላይ አላወጣትም፡፡ ናዝሬት ገሊላ በምትባል አገር ሳለች ራሱ በማኅፀኗ አደረ እንጂ፡፡ በጌትነቱ ሰው በሆነ ጊዜ አላሰፋትም፡፡ ገብርኤልን “በሆዷ ዘጠኝ ወር ትሸከመኝ ዘንድ ድንግልን ወደዚህ አምጣት” አላለውም፡፡

እርሱ ትሕትናዋን ተሳትፎ ከገብርኤል ጋር ወርዶ ወደ ድኻይቱ ቤት ገባ፡፡ መልአኩ “መንፈስ ቅዱስ ወዳንቺ ይመጣል” ባላት ጊዜ የአምላክBeserate እናት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ከበረች፡፡ “የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል” ብሎ በደገመ ጊዜ በሰማያዊ አባቱ ሥልጣን ወልድን ለመፅነስ በቃች፡፡ “ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” አላት፡፡ ያን ጊዜ ከእርሷ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያንን ተረዳች፡፡ እርሷም ወልድ ከአባቱ ጋር ወዳለበት ወደ ጽርሐ አርያም ኅሊናዋን አወጣች /አሳረገች/፡፡ እርሱም ራሱን ዝቅ አድርጎ በትሐትና ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በማኅፀኗ ተፀነሰ፡፡ ዳግመኛ ድንግል መልአኩን “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” አለችው፡፡(ሉቃ.1፡26-32) ያን ጊዜ አካላዊ ቃል ከእርሷ በተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡ አይታው እንዳትደነግጥ ተመልክታው እንዳትፈራ  ኪሩቤልን ከእርሱ ጋር አላመጣም፡፡ በወዲያኛው ዓለም በአባቱ ሥልጣን እንዳለ በዚህ ዓለም ለቅዱሳን ተልእኮ የሚጠቅም ምድራዊ ሕግን ሠራ፤ የማይታይ የማይመረመር ኀይል በዚህ ዓለም እርሱ ብቻውን በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ህልው ሆነ፤ በወዲያኛውም ዓለም የማይዳሰስ መለኮት ከሚዳሰስ ሥጋ ጋር በዚህ አለ፡፡

yeledeteበወዲያኛው ዓለም የእግዚአብሔርን መንበር የተሸከሙ ኪሩቤል አሉ፡፡ በወዲህኛውም ዓለም ሥጋ የተገኘባቸው ዐራቱ ባሕርያት አሉ፡፡ ወልድ በወዲያኛው ዓለም  አባት ያለ እናት በዚህ እናት ያለ ምድራዊ አባት አለው፡፡ በወዲያኛው ዓለም ቅዱስ ገብርኤል በፍርሃት ይቆማል፡፡ በዚህኛው ዓለም ቅዱስ ገብርኤል በደስታ ያበሥራል፡፡ በዚያ በጽርሐ አርያም ከአብ የማይታይና የሚደነቅ የልደት ክብር አለው፡፡ በወዲያኛው ዓለም ሰማያውያን ካህናት በወርቅ ጽንሐሕ የዕጣን መዓዛ ያቀርቡለታል፡፡ በዚህኛው ዓለም ከሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ይቀርብለታል፡፡

በወዲያኛው ዓለም ከግርማው የተነሣ ሱራፌልና ኪሩቤል ይንቀጠቀጣሉ፡፡ በዚህኛው ዓለም ድንግል ማርያም ትታቀፈዋለች፣ ሰሎሜም ትላላከዋለች፡፡ ከዚያ በፊቱ የመባርቅት ብልጭልጭታ ከፊቱ ይወጣል የእሳት ነበልባልም ከአዳራሹ ቅጥር ይወጣል፡፡ በዚህ አህያና ላም በእስትንፋሳቸው ያሟሙቁታል፡፡

በዚያ የእሳት መንበር በዚህ የድንጋይ ዋሻ አለ፡፡ በወዲያኛው የተሠራ የሰማይ ጠፈር (ዘፀ.24፡10) በዚህ የላሞች ማደሪያ /ማረፊያው/ ሆነ፡፡ በዚያ ትጉሃን መላእክት የሚገናኙበት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፤ በዚህኛው የእረኞች ማደሪያ የሆነች ዋሻ አለች፡፡ ዘመኑ የማይታወቅ ተብሎ በዳንኤል የተነገረለት ብሉየ መዋዕል አምላክ በወዲህኛው ዓለም የዕድሜው ቁጥር በሰው መጠን የሆነ አረጋዊ ዮሴፍ አለ፡፡ በጽርሐ አርያም ፀንሳው ቢሆን ኖሮ ክብርና ልዕልና ለብቻዋ በሆነ ነበር፡፡ እኛም በእርሷ ክብር ክብርን ባላገኘን ነበር፡፡ በሰማያት የሚደረገውን ምሥጢር ምን እናውቃለን? በአርያም ያለውን ስውር ነገር በምን እናየው ነበር?

በኪሩቤል ሠረገላ ላይ እንዳለ ብትወልደው ኖሮ በእቅፍ መያዙን ማን ባየ ነበር፤ አካሉንስ ማን በዳሰሰው ነበር በምድር ላይ ባይመላለስ ኖሮ የጥምቀቱን ምልክት ማን ባየ ነበር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ አብ ለማን በመሰከረ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስስ በነጭ ርግብ አምሳል በማን ራስ ላይ በወረደ ነበር፤ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ባይገለጽ ኖሮ በማን ስም እንጠመቅ ነበር? ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱን “ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” አላቸው፡፡ (ማቴ.28፡19) አብ ማን ነው? ወልድስ ማን ነው? መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? እንዳይሉ በዮርዳኖስ ወንዝ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ተገለጠ፤ በሰው ልጅ አምሳል ባይጎለምስ፣በሰው ልጅ አምሳል ባይታይ እኛን ስለማዳን ማን መከራን በተቀበለ ነበር? እነሆ! የሰው ልጅ ከሰማይ መላእክት ይልቅ ከበረ፤ እግዚአብሔር ከሴት ተወልዷልና፡፡ ስለዚህ ነገር ጳውሎስ “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” አለ፡፡(ዕብ.2፡16)

አሁንም የፎጢኖስን ተግሳፅ ፈጽመን የአምላክን ልጅ ሰው መሆን በዓል እናድርግ፡፡ ለተሸከመችው ማኅፀን ምስጋና እናቅርብ፡፡ ላቀፉት ጉልበቶች እንስገድ፤ ላሳደጉት ጡቶች እንዘምር፤ የዳሰሱትን እጆች እናመስግን፤ ለሳሙት ከንፈሮች እናሸብሽብ ከእረኞች ጋር እናመስግን፤ ከሰብአ ሰገል ጋር እጅ መንሻ እናቅርብ፡፡ እንደ ዮሴፍ እናድንቅ፤ እንደ ሰሎሜም እንላላክ፡፡ በተኛበት በረት እንስገድ፤ በተጠቀለለበት በረት እንበርከክ፡፡ ሰውን ለወደደ ለእግዚአብሔር በላይ በሰማይ ክብር ምስጋና፣ ሰላምም በምድር ይሁን እንበል፡፡ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ሰው ሆነ የሰው ልጅም የእግዚአብሔር እናት ሆነች፡፡ ለእርሱ ክብር ምስጋና ለእርሷም የክብር ስግደት ለዘለዓለም ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ያቃለላት፣ የወልድን መለኮት የለየ፣ የሃይማኖትን ገመድ የቆረጣት የገሞራ ሐረግ የፎጢኖስ ተግሳጽ ተፈጸመ፡፡ …Aba Georgise ze gasecha ጊዮርጊስ የቤተ ክርስቲያን ካህናት ትምህርት ልጅ፣ የሃይማኖትን መንገድ የወደደ ይህን ተናገረው፡፡ ድንግል ተቀዳሚ ተከታይ ከሌለው ከበኲር ልጇ ዘንድ ኀጢአቱን ታስተሰርይለት ዘንድ፣ በዚህ ዓለም ከመከራ ታድነው ዘንድ በሚመጣው ዓለም ወደ ቤቷ ታስገባው ዘንድ፣ ከሚደነቅ የሕይወት ማዕድ ታበላው ዘንድ፣ ከምሥጢር ወይን ታጠጣው ዘንድ፣ ለዘወትር መከራን እንዳያይ ከመከራ ደጃፍ ታርቀው ዘንድ ለምኑለት፡፡ ይህን መጽሐፍ ሥነ ምግባሯ በተከበረበት፣ የክብሯ ገናናነት በታየበት በመታሰቢያዋ ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን እንዲነበብ አዘዘ፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡