የላይ ቤት የአቋቋም ደቀ መዛሙርት ተመረቁ

ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ /ጎንደር ማእከል/

01 kehaበጎንደር ከተማ በደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም 61 የላይ ቤት የአቋቋም ደቀ መዛሙርት ተመረቁ፡፡

የደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ስብሐት ቀሲስ ሞገስ አለሙ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት ባስተላለፉት መልእክት ልጄ ሆይ አደራህን ጠብቅ 2ኛ. ጢሞ.1፡-14 በሚል ኃይለ ቃል አባትክን መስለህ፣የአባቾችህን ጉባኤ ቤት ጠብቅ በማለት ተመራቂ ደቀ መዛሙርት በተማሩት ትምህርት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲገለግሉ እና አደራቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

መልአከ ስብሐት ቀጥለውም ቦታው ቀደምት ነው ነገር ግን ለእነዚህ የአብነት ተማሪዎች የምግብ፣የመጠለያ፣የአልባሳት ችግር እንዳለ ሆኖ በጋራ ሆነው የሚማሩበት የመማሪያ ቤት እንኳን የላቸውም፤ በመሆኑም ሁሉም አካል ይህ የላይ ቤት አቋቋም እንዳይጠፋ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ ብለዋል፡፡

ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱም ከቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ከመልአከ ስብሐት ቀሲስ ሞገስ አለሙ መስቀል እና የምሥክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

02kehaበምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መምህር ዳንኤል ኃይሉ የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ቅኔ፣ መሪጌታ ድረስ ቦለድ በቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ሰሎሞን ምቅናይ እና የድጓ ዜማ፤ የማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል የመዝሙር ክፍል አባላት እና የደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡

የደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ከጎንደር ካሉት ቀዳሚ አድባራት የሚጠቀስ ሲሆን፤ በ1355 ዓ.ም የተተከለ ነው፡፡