የሀዋሳ ማእከል ሕግና ዕቅበተ እምነት ዋና ክፍል ተጠሪ የነበሩት አቶ አስማማው ታመነ አረፉ

በካሣሁን ለምለሙ

በማኅበረ ቅዱሳን የሀዋሳ ማእከል ሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠሪ የነበሩት አቶ አስማማው ታመነ ሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም በደረሰባቸው ድንገተኛ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ የሀዋሳ ማእከል አስታወቀ፡፡

አቶ አስማማው ታመነ ከአባታቸው ከአቶ ታመነ ተገኝ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ የሺሐረግ አሰፋ በምዕራብ አርሲ ዞን በዶዶላ ከተማ ነሐሴ 25 ቀን 1982 ዓ.ም ተወለዱ። ዕድሜቸው ለትምህርት ሲደርስ  የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቱሉ ዶዶላ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በዶዶላ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የከፍተኛ ደርጃ ትምህርታቸውን  በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ትምህርት ዘርፍ በደረጃ ፭ ከጨረሱ በኋላ በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ  ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

አቶ አስማማው ታመነ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋል በአለታወንዶ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በመምህርነት  የሥራ መስክ የሠሩ ሲሆን በሀዋሳ ተግባረ ዕድ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ እንዲሁ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በደቡብ ክልል ኢትዮ ቴሌኮም ለኩ እና ሀዋሳ ከተማ በፊክስድ ኔትወርክ ቴክኒሻን ባለሙያነት እና በኃላፊነትም ለአምስት ዓመት ከአምስት ወር አገልግለዋል።

አቶ አስማማው ታመነ በመንፈሳዊ አገልግሎት በነበራቸው ተሳተፎ በማኅበረ ቅዱሳን አለታ ወንዶ ወረዳ ማእከል በሰብሳቢነት፣ በሀዋሳ ማእከል የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ንኡስ ክፍል ኃላፊ እንዲሁም በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ የሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠሪ በመሆን እስከ ኅልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት አገልግለዋል።

አቶ አስማማው ታመነ  በአገልግሎት ዘመናቸው የሀዋሳ ማእከል የሚሰጣቸውን ተልእኮ በትጋት የሚወጡ፣ ከሥራ ባልደርቦቻቸው ጋር ተግባቢ፣ ሰው አክባሪ እንዲሁም የሀገርና የሥራ ፍቅር ያላቸው ሰው ነበሩ። አቶ አስማማው ታመነ ሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ድንገት በደረሰባቸው የትራፊክ አደጋ ምክንያት በተወለዱ በ29 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አብሮ አደግ ጓደኞቻቸው፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሀዋሳ ማእከል አባላት እና የሥራ ባልደርቦቻቸው በተገኙበት ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በትውልድ ቦታቸው በዶዶላ  ማኅደረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

በአቶ አስማማው ታመነ  ድንገተኛ ሞት የሀዋሳ ማእከል የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጦ ለሟቹ አገልጋይ ወንድም ዕረፍተ ነፍስን፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እና ለማኅበረ ቅዱሳን አባላት መጽናናትን ተመኝቷል።