ዜና ዕረፍት

መጋቢት ፬፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት የሮቸስተር ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው ተገልጿል።

ዕረፍታቸውንም ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ያደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ክቡር አስከሬናቸው በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት ፱/፳፻፲፭ ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም አስታውቋል።

ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሣልሳይ ከ፲፯  ዓመታት በፊት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  አንብሮተ ዕድ  የተሾሙ ናቸው።

ብፁዕነታቸው አስኬማ መላእክት ከሚለበስበት የኤጲስ ቆጶስነት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን  በተለያዩ  አካባቢዎች ሲያገለግሉ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። በተለይ አገልግሎታቸውን ከጀመሩበት ከአገው ምድር አዊ  ጀምሮ በባሕርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች  አገልግለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ብፁዕነታቸው በድሬዳዋ ብሎም በቤተ ክርስቲያናችን  ፈቃድ ጀርመን  ሀገር ተልከው የሚገባውን ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን ከዚያም በሰሜን አሜሪካ በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በመንበረ ጵጵስና ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይነት እስከ የበላይ ጠባቂነት በአባትነት እንዳገለገሉ ታሪካቸው ያስረዳል።

በረከታቸው ይደርብን!