ዘመነ ክረምት ክፍል አንድ

ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በበአተ ክረምት ጽሑፋችን እንደ ጠቀስነው በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት አኳያ አሁን የምንገኘው ዘመነ ክረምት ላይ ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ይህ ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የመጀመሪያውን ክፍለ ክረምት የተመለከተ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል፤

ከሰባቱ የዘመነ ክረምት ክፍሎች መካከል የመጀመሪያው ክፍል (ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ) ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመናና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ <<በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው መጡ፤>> በማለት እንደ ተናገረው /መዝ.፻፳፭፥፭-፮/፣ ይህ ወቅት አርሶ አደሩ በእርሻና ዘር በመዝራት የሚደክምበትና የምርት ጊዜውን በተስፋ የሚጠባበቅበት ጊዜ ነው፤ ይህም የሰውን ልጅ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ እንደዚሁም በክርስቲያናዊ ምግባር ስለሚያገኘው ሰማያዊ መንግሥት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስና የሐኖስ ድንበር ይኾን ዘንድ በውሃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውሃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን ካደረገ በኋላ ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር አድርጎታል፡፡ ሢሶውም ከጠፈር በላይ ያለው ውሃ ሲኾን፣ ስሙም ሐኖስ ይባላል፡፡

ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ምድርም እንደ ጉበት ለምልማ በታየች ጊዜ እግዚአብሔር በነፋስ ኃይል ጸጥ ካደረጋት በኋላ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስ፤ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስ አስወጥቶ ደመናን አስገኝቷል /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት ፻፴፬፥፯/፡፡

ደመና ዝናምን የሚሸከመው የማይጨበጠው ጢስ መሰል ፍጥረት ሲኾን፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖስና ከወንዞች በትነት አማካይነት ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውሃ ደግሞ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ <<ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያው፤ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤>> እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፡፡

ይህም በረዶውን በምድረ በዳ አፍሶ የጠራውን ውሃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲኾን፣ ምሥጢሩም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዕ በልዩ ጥበቡ መፀነሱንና የሰውን ሥጋ ለብሶ ማስተማሩን፤ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን <<ሑሩ ወመሐሩ>> ብሎ በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሰማራቱን ያመለክታል /ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ፪፥፭-፮/፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በረቂቅ ጥበቡ ውሃን ከውቅያኖሶች በደመና እየጫነ ወደ ሰማይ ካወጣ በኋላ እንደ ገና መልሶ ወደ ምድር እያዘነመ ይህንን ዓለም ሲመግብ ይኖራል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህንን ጥበብ በማድነቅ <<ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት አምላክነ በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘያአቍሮ ለማይ ያዐርጎ እምቀላይ ወያወርዶ እምኑኀ ሰማይ፤ ረቂቅ በኾነ የጉም ተን ውሃውን የሚቋጥረው፤ ከወንዝ ወደ ላይ የሚያወጣው፤ ከሩቅ ሰማይም የሚያወርደው እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ልዩ፣ ምስጉን አሸናፊ አምላክ ነው፤>> በማለት እግዚአብሔርን ያመሰግናል /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡

ዝናም በአንድ በኩል የቃለ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፤ ይኸውም ለዘር መብቀል፣ ማበብና ማፍራት ምክንያት እንደ ኾነ ኹሉ በቃለ እግዚአብሔርም በድንቁርና በረኃ የደረቀ ሰውነት ይለመልማል፤ መንፈሳዊ ሕይወትን የተራበችና የተጠማች ነፍስም ትጠግባለች፤ ትረካለችና፡፡ <<ሲሲታ ለነፍስ ቃለ እግዚአብሔር፤ የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤>> እንዲል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ዓለም የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ፈተናም በዝናም ይመሰላል፤ ጌታችን በወንጌል እንደ ነገረን ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውል ክርስቲያን ቤቱን በዓለት ላይ የመሠረተ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ጐርፍ ቤቱን በገፋው ጊዜ አይናወጥምና፡፡

ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ግን ያለ መሠረት በአሸዋ ላይ ቤቱን የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በዝናብ፣ በጎርፍና በነፋስ ተገፍቶ የከፋ አወዳደቅ ይወድቃልና፡፡ ይህም ሃይማኖቱን በበጎ ልቡና የያዘ ክርስቲያን ከልዩ ልዩ አቅጣጫ በሚደርስበት መከራ ሳይፈራና በሰዎች ምክር ሳይታለል፤ እንደ ኢዮብ ዓይነት ፈተና ቢደርስበት ሳያማርር፤ እንደዚሁም በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን እየታገዘ አጋንንትን ድል እያደረገ ሃይማኖቱን ጠብቆ እንደሚኖር፤ በአንጻሩ ሃይማኖቱን በበጎ ሕሊና ያልያዘ ክርስቲያን ግን ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ እንደሚክድና ለአጋንንትም እጁን እንደሚሰጥ የሚያስረዳ ምሥጢር አለው /ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ.፯፥፳፬-፳፯/፡፡

ዝናም ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበላት ቤት እንዲያፈርሱ፤ ንብረት እንዲያወድሙ በክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያጋጥም ፈተናም በእምነት መዛል፣ መከራ፣ ችግር፣ ውጣ ውረድ ያጋጥማል፡፡ ዝናም ለጊዜው እንዲያስበርድና ልብስን እንዲያበሰበስ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ ያዝላል፡፡ ነገር ግን ዝናም፣ ጎርፍና ማዕበል ጊዜያዊ እንደ ኾነ ኹሉ ፈተናም ከታገሡት ያልፋል፡፡

ዝናም ሲመጣ የውሆችን ሙላትና ጎርፉን ሳንፈራ ወደ ፊት የምናገኘውን ምርት ተስፋ እንደምናደርግ ፈተና ሲያጋጥመንም የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ በትዕግሥት ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ኹላችንም እምነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት በውሃ ሙላትና በማዕበል ከሚመሰል ውድቀት ማምለጥ ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡

የደመና አገልግሎቱ ዝናምን ከውቅያኖስ በመሸከም ወደ ምድር እያጣራ ማውረድ ቢኾንም ነገር ግን በሰማይ የሚዘዋወርና በነፋስ የሚበታተን ዝናም አልባ ደመናም አለ፡፡ በመልካም ግብር፣ በትሩፋት ጸንተው የሚኖሩ ምእመናን ዝናም ባለው ደመና ሲመሰሉ፣ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር በስመ ክርስትና ብቻ የምንኖር ምእመናን ደግሞ ዝናም በሌለው ደመና እንመሰላለን፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ <<… በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፤ …>> በማለት የተናገረውም የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ሕይወት ይመለከታል /ይሁዳ ፩፥፲፪/፡፡

ስለዚህም ውሃ ሳይይዝ በባዶው በነፋስ እንደሚበታተን ዝናም አልባ ደመና ሳይኾን፣ ዝናም እንደሚሸከም ደመና በምግባረ ሠናይ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ አንድም ዝናም ያለው ደመና የእመቤታችን የቅድስት ደንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ እርሷ ንጹሑን የሕይወት ውሃ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታልናለችና፡፡ <<አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም፤>> እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም /ውዳሴ ዘረቡዕ/፡፡ እኛም እንደ እመቤታችን የእግዚአብሔርን ቃል ሕይወታችን በማድረግ ራሳችንን ከማዳን ባሻገር ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ምድርን ከፈጠረ በኋላ በጥፍር የሚላጡትን (ሎሚ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ፣ ወዘተ)፤ በማጭድ የሚታጨዱትን (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ወዘተ)፤ በምሳር የሚቈረጡትን (ወይራ፣ ዋርካ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ)፤ የገነት ዕፀዋትን ፈጥሯል፡፡ ተፈጥሯቸውም እንደ ሰው ከአራቱ ባሕርያት ነው፡፡

ከነፋስ በመፈጠራቸው በነፋስ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡ ከእሳት በመፈጠራቸው እርስበርሳቸው ሲፋተጉ እሳት ያስገኛሉ (አንዳንዶቹ)፡፡ ከውሃ በመፈጠራቸው ፈሳሽ ይወጣቸዋል፡፡ ከአፈር በመፈጠራቸው ሲቈረጡ በስብሰው ወደ አፈርነት ይቀየራሉ፡፡ እነዚህም በራሳቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ስንዴ፣ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ)፤ በጎድናቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ወዘተ)፤ በውስጣቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ዱባ፣ ቅል፣ ወዘተ)፤ በሥራቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ድንች፣ ወዘተ) ተብለው በአራት ይመደባሉ /ምንጭ፡- ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት ፩፥፮-፲፫/፡፡

እኛ የሰው ልጆችም በተፈጥሯችን (በባሕርያችን) ከዕፀዋት ጋር እንመሳሰላለን፤ በነፋስ ባሕርያችን ፍጥነት፤ በእሳት ባሕርያችን ቍጣ፤ በውሃ ባሕርያችን መረጋጋት፤ በመሬት ባሕርያችን ትዕግሥት ወይም ሞት ይስማማናልና፡፡ በሌላ በኩል የአዘርዕት ከበሰበሱ በኋላ መብቀልና ማፍራት የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው፡፡ አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ ፍሬ እንደሚያስገኙ ኹሉ ሰውም ከሞተ በኋላ ተነሥቶ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላልና፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ እንዲህ ሲል፤ <<… የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል፤ ባለመበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኃይል ይነሣል፡፡ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። …>> /፩ኛቆሮ.፲፭፥፵፪-፵፬/፡፡

አዝርዕት ተዘርተው ከበሰበሱ በኋላ በቅለው፣ አብበው በራሳቸው፣ በጎድናቸው፣ በውስጣቸውና በሥራቸው እንደሚያፈሩ ኹሉ እኛም በራስ እንደ ማፍራት ፈሪሃ እግዚአብሔርን፤ በጎድን እንደ ማፍራት እርስበርስ መደጋገፍንና መተሳሰብን፤ በውስጥ እንደ ማፍራት ንጽሕናን፤ በሥር እንደ ማፍራት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግን ከዕፀዋትና ከአዝርዕት መማር ይገባናል፡፡

እንደዚሁም ዕፀዋት ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶና ከዚያ በላይ መልካም ፍሬ እንደሚያፈሩ እኛም በመልካሟ መሬት በክርስትና የተዘራን ምእመናን ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ተምረን ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፤ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት በሚያደርስ የጽድቅ ሥራ በመትጋት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መፋጠን ይኖርብናል /ማቴ.፲፫፥፳፫/፡፡

በአጠቃላይ “… ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤”  የሚለውን ኃይለ ቃል በማሰብ /ማቴ.፫፥፲/፣ ፍሬ የማያፈሩ ዕፀዋት በምሳር ተቈርጠው እንዲጣሉ እኛም ያለ መልካም ሥራ ከኖርን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍርድ ከገነት፣ ከመንግሥተ ሰማያት የመባረር ዕጣ እንዳይደርስብን ከሃይማኖታችን ሥርዓት፤ ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ሳንወጣ የቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገን ለጽድቅ ሥራ እንሽቀዳደም፡፡ <<እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤>> ተብሎ ተጽፏልና /ዕብ.፲፪፥፩-፪/፡፡

ይቆየን፡፡