ዘመነ ክረምት – ክፍል አንድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ እንደዚሁም በመጽሐፈ ግጻዌ እንደ ተገለጸው እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደ ማስገንዘብያ፡- ክረምቱ የሚጀምረው ሰኔ ፳፮ ቀን ቢኾንም ከዋይዜማው ጀምሮ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ስለ ኾነ ከሰኔ ፳፭ ቀን ጀምረን መቍጠር እንችላለን፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስረዱን ከዋይዜማው ወይም ከመነሻው ጀምረን ቀኑን መጥቀሳችን የአስተምህሮ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይህ አቈጣጠር ለሌሎች ወቅቶች እና ለዘመነ ክረምት ክፍሎችም ተመሳሳይ መኾኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ!

‹ክረምት› ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ይኸው ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፤ የክፍፍሉ መሠረት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲኾን፣ ክፍሎቹም የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲ – ፳፯ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭ (፮) ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዓልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩ – ፯ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፰ – ፲፬ ቀን ፍሬ፤

፯ኛ ከመስከረም ፲፭ – ፳፭ ቀን ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ) ወይም ዘመነ መስቀል፡፡

እያንዳንዱን ክፍለ ክረምትም በመጠኑ እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን፤

፩. በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

በአተ ክረምት (የክረምት መግብያ)

በዘመነ ክረምት መጀመርያ (መግብያ) ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር የሚከተለው ነው፤

‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡-

‹‹የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ ድሆች ይደሰታሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ አምላካችን ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ፈጠረ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡››

ይህ መዝሙር ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ ያለው ወቅት ክረምቱ የሚገባበት እና ዝናም በብዛት የሚጥልበት ጊዜ መኾኑን የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እኽልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡ በዚህ ሳምንት በዕለተ ሰንበት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፤

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፴፫ – ፶፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ዅሉ የሰው ልጅም ከሞተ በኋላ ከሞት እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው፤ እንደዚሁም የሰው ልጅ ሞቱንና የሚያገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ከኀጢአት መለየት እንደሚገባው ያስረዳል፡፡

ያዕቆብ ፭፥፲፮ እስከ ፍጻሜው

ፍሬ ዐሳቡ፡- ነቢዩ ኤልያስ በጸሎት ዝናም እንዳይዘንምና እንደገና እንዲጥል ማድረጉን በመተረክ እኛም እምነቱ ካለን በጸሎት ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለን ይናገራል፡፡

ግብረ ሐዋርያት ፳፯፥፲፩ – ፳፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- ቅዱስ ጳውሎስና ተከታዮቹ መርከባቸው በማዕበል ክፉኛ መናወጧንና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸውን፤ በባሕሩ ውስጥም በጨለማ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን በማውሳት ይህ ወቅት (ዘመነ ክረምት) የውኃና የነፋስ ኃይል የሚያልበት ጊዜ መኾኑን ያስተምራል፡፡

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፵፮፥፰

ኃይለ ቃሉ፡- ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡- ‹‹ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ የሚያበቅል እርሱ ነው፡፡››

የመዝሙሩ ፍሬ ዐሳብ፡- እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡

ወንጌል፡- ሉቃስ ፰፥፩-፳፪

ፍሬ ዐሳቡ፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔርን በዘርዕ፣ የምእመናንን ልቡና (የመረዳት ዓቅም) ደግሞ በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾኽና በመልካም መሬት በመመሰል ቃሉን ሰምተው በሚለወጡትና በሚጠፉት መካከል ስላለው ልዩነት ማስተማሩን ያስረዳል፡፡

ቅዳሴው፡- ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ስለ ዝናም፣ ደመና፣ መብረቅ፣ ባሕርና መሰል ፍጥረታት ዑደት፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ የሚገዛና የሚመግብ አምላክ መኾኑን ስለሚያብራራ በዘመነ ክረምት ይቀደሳል፡፡

ጠቅለል አድርገን ስንገልጸው በዘመነ ክረምት መጀመርያ ሳምንት ከአዝርዕት፣ ከዝናም፣ ከልምላሜ፣ ከውኃ ሙላትና ከባሕር ሞገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶች ከሰው ልጅ ሕይወትና ከምግባሩ እንደዚሁም በምድር ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ጋር እየተነጻጸሩ ይቀርባሉ፡፡ የወቅቱን ትምህርት ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተውም ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ ገበሬ በክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይቆየን