ዘመነ ክረምት – ክፍል ሰባት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጳጕሜን ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል ስድስት ዝግጅታችን አራተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል ማለትም ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን እና መዓልትን መነሻ አድርገን ወቅቱን ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ መንፈሳዊ ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ደግሞ አምስተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል (ቀዱስ ዮሐንስን) የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!

፭. ዮሐንስ

ከመስከረም ፩ – ፰ ቀን (ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ) ያለው አምስተኛው ክፍለ ክረምት ‹ዮሐንስ› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ክፍለ ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማጥመቅ የተመረጠው፣ የዓዋጅ ነጋሪው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርቱ፣ ጥምቀቱ፣ ምስክርነቱ፣ አገልግሎቱ፣ ክብሩ፣ ቅድስናው፣ ገድልና ዕረፍቱ በአጠቃላይ ዜና ሕይወቱ ከአዲሱ ዓመት ጋር እየተጣጣመ የሚዳሰስበት የብሥራት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የቅዱስ ዮሐንስን አገልግሎት የሚመለከቱ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን በስፋት ይቀርባሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቍጥር የቅዱስ ዮሐንስ ክብረ በዓልም አብሮ ይዘከራል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑም ለአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን ‹‹ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ›› እያሉ መልካም ምኞታቸውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መግለጻቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ከአዲስ ዓመት መባቻ ጋር በአንድነት ሲከበር ለመቆየቱ ማስረጃ ነው፡፡ ይኸውም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከጳጕሜን ፩ ቀን ጀምሮ በእስር ቤት ከቆየ በኋላ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ቅዱሱ የሐዲስ ኪዳን አብሣሪ ነውና፣ ደግሞም ዕለቱ ቃል ኪዳን የተቀበለበት ቀን ነውና ስሙና ግብሩ ከዘመን መለወጫ ጋር አብሮ ይታወስ ዘንድ በዓሉ መስከረም ፩ ቀን በሥርዓተ ማኅሌት ይከበራል፡፡ ለዚህም ነው – ሊቃውንቱ ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ›› እያሉ የአዲስ ዓመት መጀመርያ፣ የመጥቅዕ እና አበቅቴ መነሻ መኾኑን በሚገልጽ ኃይለ ቃል ቅዱስ ዮሐንስን የሚያወድሱት፡፡

ታሪኩን ለማስታወስ ያህል ዮሐንስ ማለት ‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው› ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የካህኑ ዘካርያስና የቅድስት ኤልሳቤጥ ልጅ ነው፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ መካን (ካ ይጠብቃል) በመኾኗ እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር በጸሎት ይማጸኑት ነበር (ሉቃ. ፩፥፭-፯)፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የካህኑ ዘካርያስ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙን ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱ ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት የእግዚአብሔር መልአክ ለዘካርያስ ነገረው (ሉቃ.፩፥፰-፲፯)፡፡ በዚህ ቃለ ብሥራት መሠረት ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን ተወለደ፡፡ ሕፃኑ ዮሐንስም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ (ሉቃ. ፩፥፹)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ፴ ዓመት ሲሞላውም በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!›› እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ዅሉ ወጣ (ሉቃ. ፫፥፫-፮)። የይሁዳ አገር ሰዎች ዅሉ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። እርሱም ቃለ ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር (ሉቃ. ፫፥፯-፲፬)፡፡ በመጨረሻም ‹‹ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ›› እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ካረፈ በኋላም የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል።እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ለሕዝቡ ተናግሯል (ማቴ. ፲፩፥፱-፲፩)። እንደዚሁም ቅዱስ ዮሐንስን ከነቢዩ ኤልያስ ጋር በማመሳሰል ስለ አገልግሎቱ አስተምሯል (ማቴ. ፲፩፥፪-፲፱)።

ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ብሎ ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፣ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፣ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፣ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንደዚሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና አገልግሎቱን በሰማዕትነት መፈጸሙ በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ) እና በገድለ ዮሐንስ መጥምቅ በሰፊው ተጽፏል፡፡

እንግዲህ እኛም እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከኀጢአት ተለይተን፣ ራሳችንን ለጽድቅ ሥራ አስገዝን፣ በንጽሕና ኾነን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ከዅሉም በላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንዘጋጅ፡፡

ይቆየን