ዘመነ ክረምት ክፍል ሦስት

ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹‹መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል›› እንደሚባል፤ ይህ ክፍለ ጊዜ የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ እንደዚሁም የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት እንደ ኾነ በማስታዎስ ሕይወታችንን ከወቅቱ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ መንፈሳዊ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩንና ሦስተኛውን ክፍለ ክረምት የተመለከተ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፰ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ›› ይባላል፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ጨምሮ የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በደስታ መኖራቸው፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙሪያቸው ያለው የውሃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ኹሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ኹሉ በእነዚህ ምሥጢራት ላይ ያተኰረ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለ ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያትና ዓይነ ኲሉ በቅደም ተከተል አጭር ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፤

ዕጕለ ቋዓት

‹‹ዕጕል፣ ዕጓል›› ማለት ‹‹ልጅ›› ማለት ሲኾን፣ ‹‹ቋዕ›› ደግሞ ‹‹ቍራ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቋዕ›› የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር ሲገለጽም ‹‹ቋዓት›› ይኾናል፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ዕጕለ ቋዓት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረትም ‹‹የቍራ ልጆች (ግልገሎች)›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የቍራ ጫጩቶች አስተዳደግ ከምእመናን ሕይወት ጋር ተነጻጽሮ ይነገራል፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ ቍራ ከእንቁላሉ ፍሕም መስሎ ይወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ባዕድ ነገር መስሏቸው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ እርሱም በራበው ጊዜ ምግብ ፍለጋ አፉን ሲከፍት እርጥበት የሚፈልጉ ተሐዋስያን ወደ አፉ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አፉን በመግጠም ይመገባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ተሐዋስያን በአጠገቡ ሲያልፉ በእስትንፋሱ (በትንፋሹ) እየሳበ ይመገባቸዋል፡፡ እስከ ፵ ቀን ድረስ እንደዚህ እያደረገ ከቆየ በኋላ ፀጕር ያበቅላል፤ በዚህ ጊዜ በመልክ እነርሱን ስለሚመስል እናት አባቱ ተመልሰው ይከባከቡታል፡፡ ይህ የቍራ ዕድገትና ለውጥም እግዚአብሔር ፍጡራኑን የማይረሳ አምላክ እንደ ኾነና ፍጥረቱንም በጥበቡ እየመገበ እንደሚያኖራቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ይህንን የቍራ የዕድገት ደረጃና የእግዚአብሔርን መግቦት በተናገረበት መዝሙሩ ‹‹ወሐመልማለ ለቅኔ ዕጓለ እመሕያው ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ ለሰው ልጆች ጥቅም ለምለሙን የሚያበቅል፤ ለእንስሳትና ለሚለምኑት የቍራ ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው›› ሲል ይዘምራል /መዝ.፻፵፮፥፱/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደ ገለጹት ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ለእርሱ ለሚገዛው ለሰው ልጅ እኽህሉን፣ ተክሉን የሚያበቅልላቸው፤ ለእንስሳቱና ለአዕዋፍ (በቍራ አምሳል አዕዋፍን በመጥቀስ) ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ እንደ ኾነ ያስረዳል፡፡ ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ … ለሚለምኑት ለቍራ ጫጩቶች›› የሚለው ሐረግም አዕዋፍ እግዚአብሔርን ምግብ እንዲያዘጋጅላቸው እንደሚለምኑትና እርሱም ልመናቸውን እንደሚቀበላቸው ያስገነዝበናል፡፡ በአንድምታው ትርጓሜ እንደ ተጠቀሰው ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ›› የሚለው ሐረግ ‹‹… እለ ኢይጼውእዎ›› ተብሎ ከተገለጸ የቍራ ጫጩቶች አፍ አውጥተው ባይነግሩት እንኳን እርሱ ፍላጎታቸውን ዐውቆ ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው የሚያመለክት ምሥጢር አለው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

ምሥጢሩን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣውም እግዚአብሔር አምላክ ስሙን የሚጠሩትንም የማይጠሩትንም፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› እያሉ የሚማጸኑትንም የማይጸልዩትንም በዝናም አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ኹሉንም ሳያደላ በቸርነቱ እንደሚመግባቸው ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰው ልጅ ለሚበላው፣ ለሚጠጣው መጨነቅ እንደማይገባው ሲናገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ትምህርት ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፡፡ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከወፎች ትበልጡ የለምን? … አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ኹሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም:: … ዛሬ ያለውን፣ ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የኾነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከኾነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ ይልቁን እንዴት? … የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም:: ይህንስ ኹሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፡፡ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል:: ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ኹሉ ይጨመርላችኋል፤›› /ሉቃ.፲፪፥፳፪-፴፩/፡፡

ስለዚህም አምላካችን እንዳስተማረን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ሳይኾን ስለ በጎ ምግባርና ስለ ዘለዓለማዊው መንግሥት መጨነቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ለገነት፣ ለመንግሥተ ሰማያት በሚያበቃ የጽድቅ ሥራ ካስገዛን የሚቀርብን ነገር አይኖርምና፡፡ ‹‹ዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ፤ ሳንለምነው ልባችን የተመኘውን የሚሰጠን እርሱ ነው›› እንዲል /መጽሐፈ ኪዳን/፡፡ የየልባችንን መሻት ዐውቆ በረድኤቱ እየጠበቀ፤ በቸርነቱ እየመገበ የሚያኖረን አምላካችን እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

ደሰያት

በውሃ የተከበበ የብስ መሬት ‹‹ደሴት›› ይባላል፤ ‹‹ደሰያት›› ደግሞ ብዙ ቍጥርን አመላካች ነው፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ደሴቶች ይነገራል፡፡ ምክንያቱም በዝናም አማካይነት በሚጨምረው የውሃ መጠን በድርቅ ብዛት የተጎዱ በደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ እንስሳትም አዕዋፍም በሚበቅለው እኽልና በሚያገኙት ምግብ የሚደሰቱበት ጊዜ በመኾኑ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ የተከበቡ መሬት እንደ መኾናቸው በዚህ ወቅት በልምላሜ ያጌጣሉ ቢባልም ዳሩ ግን በማዕበልና በሞገድ መቸገራቸውም አይቀርም፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) እና የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ መከበባቸው ቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፤ በቃለ እግዚአብሔር የታነጸች ለመኾኗ፤ ደሴቶች በማዕበልና በሞገድ እንደ መናወጣቸው ደግሞ በዓለም ውስጥ የሚከሠቱ ረሃብ፣ ጥላቻ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች፤ በተለይ ሰይጣን የሚያመጣው ልዩ ልዩ ኅብረ ኀጢአት የቤተ ክርስቲያንን (የምእመናንን) ህልውና የሚፈታተኑ መኾናቸውን ያጠይቃል፡፡

ዓለም ሞገድ የበዛባት የውሃ ክፍል ናት፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ በውሃ የተከበበች መሬት፡፡ በውሃ የተከበበ መሬት ሞገድ፣ ማዕበልና ስጥመት እንደሚያጋጥመው ኹሉ የክርስትና ሕይወትም በምድር ላይ ልዩ ልዩ መከራና ፈተና ሊያጋጥመው ይችላልና ሃይማኖታችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ፈተና ይጠብቅልን ዘንድ ኹላችንም በፍጹም ሃይማኖት ኾነን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከስጥመት አድነን?›› እያልን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እርሱ በባሕር፣ በሞገድ፣ በማዕበልና በነፋስ የሚመሰሉ የዓለምን ውጣ ውረድና መከራ መገሠፅ፤ ሑከቱንም ጸጥ ማድረግ የሚቻለው አምላክ ነውና /ማቴ.፰፥፳፫-፳፯/፡፡

ዓይነ ኵሉ

‹‹ዓይነ ኵሉ›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹የኹሉም ዓይን›› ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጥረታት ኹሉ ወደ ፈጠራቸው ወደ እግዚአብሔር በማንጋጠጥ የዕለት ጕርስ፣ የዓመት ልብስ እንዳይከለክላቸው እንደሚማጸኑትና ዘወትር የእርሱን መግቦት ተስፋ በማድረግ እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡ ይህ ወቅትም ያለፈው እኽል ያለቀበት፤ የተዘራውም ያላፈራበት ገና የተክል ጊዜ በመኾኑ ፍጥረታት በሙሉ የፍሬውን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቁበት ስለ ኾነ ‹‹ዓይነ ኵሉ›› ተብሏል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ›› ሲል የዘመረው /መዝ.፻፵፬፥፲፮/፡፡ ይኸውም የሰው ኹሉ ዓይን (ዓይን የተባለ ሰውነት ነው) እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ እንደሚኖር፤ እርሱም በዘር ጊዜ ዘሩን፣ በመከር ጊዜ መከሩን፣ በበልግ ጊዜ በልጉን እያዘጋጀ በየጊዜው ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን በሰፊው እጁ (በማያልቅ ቸርነቱ) በሥርዓቱ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ጭምር ምግባቸውን እየሰጠ ደስ እንደሚያሰኛቸው የሚያስረዳ ነው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እንደሚያትቱት ከሰው ልጅ በቀር ከእግዚአብሔር ሥርዓት የወጣ እንስሳ የለም፤ ማለትም ሰው እንጂ እንስሳት ሕገ እግዚአብሔርን አልተላለፉም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አምላክነትን ተመኝቶ ‹‹አትብላ›› የተባለውን ዕፅ በመብላት ሕጉን፣ ትእዛዙን ተላልፏል፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ባይ አምላክ ነውና የሰውን ልጅ (የአዳምን) ንስሐ ተመልክቶ፣ ኀጢአቱን ይቅር ብሎ ሞቱን በሞቱ ሽሮ አድኖታል፡፡ እናም እግዚአብሔር በፍጡራኑ የማይጨክን፤ የለመኑትን የማይነሳ፤ የነገሩትንም የማይረሳ አምላክ መኾኑን በማስተዋልና ቸርነቱን ተስፋ በማድረግ በምድር በረከቱን እንዲሰጠን፤ ቅዱስ ሥጋውን ለመብላት፣ ክቡር ደሙን ለመጠጣ እንዲያበቃን፤ በሰማይም ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን በንጹሕ ልብ ኾነን ዘወትር ልንማጸነው ይገባናል፡፡ ‹‹አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፳፬፥፫/ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ አያሳፍርምና፡፡ ደግሞም በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣልና፡፡

ይቆየን፡፡