ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሁለተኛ ክፍል

የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፩.፪ አቡሊናርዮስ

አቡሊናርዮስ የሎዶቅያ ሊቀ ጳጳስ ነበረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ አቡርዮስ” በማለት ይጠራዋል፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ለየራስ ናቸው በማለት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ሊቁ ለዚህ መናፍቅ ሲመልስ በአመክንዮ ይጀምራል አስቀድመህ በራስ ፍረድ፤ የሥላሴ ሥርዓት (ሥርዓተ ሥላሴ) ሦስት ከሆነ ማን ፈጠረህ? ማንስ አበጀህ? አብ ራሴን ፈጠረው፤ ወልድም እጄን አበጀው፤ መንፈስ ቅዱስም እግሬን አጸናው ትላለህን? በማለት ይወቅሰዋል፡፡ እንዲህ ካልህ የሥላሴን አንድነት እንደበተንህ የራስህንም አንድነት በተንህ፤የሥላሴን አንድነት እንደ አሕዛብ አማልክት ከፈልኸው፤ ጣዖት ከሚያመልኩ ጋር በሥርዓት ተባበርክ በማለት ይዘልፈዋል፡፡ እኛ ግንአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ፈቃድእንላለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምህሮ ይነግረዋል፡፡

የአቡሊናርዮስ ክሕደት የመለኮትንና የሥጋን ተዋሕዶ ሁለት ጊዜ እንደተፈጸመ ያደርገዋል፡፡ ይኸውም በፅንሰት ጊዜ በማኅፀን እና በሞት ተለያይተው የነበሩ ሥጋና መለኮት ከመቃብር በተነሣበት ጊዜ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የአቡሊናርዮስ ክሕደት የነፍስ ድኅነትን ያልተፈጸመ የሚያስመስል ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ነፍስን ካልነሣ ያልነሣውን አላደነምና ነፍስ አልዳነችም ያሰኛል፡፡ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ነፍስን አልነሣም፣ ስለ ልብና ነፍስ ፋንታ መለኮቱ ሆነው ብሎ ያስተማረም ራሱ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም አንተ አቡሊናርዮስ ሆይ! ቀድሞ በጥርጥርህ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስም የተለያዩ ናቸው ብለህ ከአባቱ የተለየ ነው አልኸው፤ አሁን ደግሞ የክርስቶስ ሰውነት ነፍስና ልብ የለውም፣ መለኮቱም ስለ ነፍስና ልብ ሆነው አልህ፡፡ እንዴት እኮ እርሱ ራሱነፍሴን ፈጽሜ በፈቃዴ እሰጣለሁ› ያለ እንደዚህ ነፍስ የለውም ይባላል?ነፍስ ከሌለው መሞቱ እንደምን ይሆናል? ያለ ነፍስ ከሥጋ በመለየት ሞት የለምና በማለት አፉን ያስይዘዋል፡፡

፩.፫ ቢቱ

ከአባ ጊዮርጊስ ጋር በአንድ ዘመን የነበረ መናፍቅ ሲሆን ለኃጥአን ፍዳ፣ ለጻድቃን በጎ ዋጋ ለመክፈል ወልድ ከአባቱ ተለይቶ ይመጣልየሚል ኑፋቄ ያስተማረ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ቢቱን ሥጋን የለበሰ ሰይጣን፣ ሰው የሆነ ጋኔን ይለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይቀመጣሉ፤ ይመረምራሉ፤ ይፈርዳሉ እንዳለ፣ አባ ጊዮርጊስም ከብሉይና ከሐዲስ ማስረጃዎችን እየጠቀሰ ቢቱን መልስ አሳጥቶታል፡፡ እኛ ግንአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሙታንና በሕያዋን ይፈርዱ ዘንድ በአንድ ዐደባባይ፣ በአንዲትም መወቃቀሻ ቦታ ይመጣሉ› እንላለን በማለት ይመልስለታል፡፡

፩.፬ አርዮስ

አርዮስ ወልድ ፍጡር በባሕርየ መለኮቱ፣ ሀሎ ዘመን አመ ኢሀሎ ወልድ፤ ወልድ በባሕርዩ ፍጡር ነው (ሎቱ ስብሐት) … ያልነበረበት ጊዜ ነበር ብሎ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም አርዮስን ርእሰ መናፍቃን (የመናፍቃን አለቃ)” ትለዋለች፡፡ አባ ጊዮርጊስ አብ እና ወልድ በባሕርይ፣ በህልውና አንድ እንደሆኑ ከመጻሕፍት ከየወገኑ እየጠቀሰ አፉን ያስይዘዋል፡፡ የክሕደት ቡቃያ አርዮስ ሆይ!እኔና አብ አንድ ነን› ብሎ የተናገረውን የፍጥረታትን ፈጣሪ ፍጡር ትለዋለህን? ዳግመኛምእኔን ያየ አብን አይቷል፤ እኔን የሰማ የላከኝን ሰማው፤ እኔን የካደ የላከኝን ካደው፤ በእኔ ካልሆነ በቀር ወደ አብ መምጣት የሚቻለው የለም፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው›፤ በማለት የተናገረው ፍጡር ነውን? በማለት ፍጹም ሰው ሆኖ የተገለጠው ፍጹም አምላክ እንደሆነ ይመልስለታል፡፡

ስለ ህልውናቸውም የዐይን ጥቅሻ፣ የሽፋሽፍትንም መገለጥ ያህል እንኳ ቢሆን አብ ከወልድ በህልውና መቅደም የለውም በማለት የመለሰለት ሲሆን እኛ ግን ያልተሠራ፣ ያልተፈጠረ፣ ያልጎደለ፣ ያልተለየ እንደሆነ እንናገራለን ይላል፡፡ ፈጽሞ ያልተፈጠረ፣ ያልተሠራ፣ ከአባቱ አኗኗር ያልጎደለና ያልተለየ እንደሆነ እንናገራለን በማለት የወልድን አምላክነት ይመሰክራል፡፡ የአባ ጊዮርጊስ መልስ ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ነው” ለማለት “አማላጅ” በሚል ቅጽል ለሚጠሩት ሁሉ መልስ መሆኑን አንብቦ መረዳት የሊቃውንቱንም መልስ የመስጠት መንፈሳዊ ፈሊጥ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

፩.፭ አርጌንስ

አርጌንስ (ኦሪገን) መዓርገ ርቀትን (‹ቀ› ይጠብቃል) ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አብ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድም እንደዚሁ ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚበልጥ አድርጎ ይናገራል፡፡ ዛሬም በዚህ ኑፋቄ የወደቁና አብ ይበልጠኛል፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን ከአብ እንደሚያንስ አድርገው የሚናገሩ አሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ እነዚህን ኀይለ ቃላት እንዲህ ይተረጉማቸዋል፡፡ ከዕርገቱ በፊትወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁያለው ለሰውነት የሚገባ ትሕትናን እያሳየ ነው፤ ለእነርሱ በጸጋ አባታቸው ነው፣ ለእርሱ ግን በእውነት የባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ለእነርሱ በእውነት አምላካቸው ነው፤ ለእርሱ ግን ሰው ስለመሆኑ ነው፡፡ ለአርጌንስም እኛ ግን ‹በሥላሴ መዓርግ የመብለጥም ሆነ የማነስ ነገር የለም፤ በመለኮት አንድ ናቸው እንጂ› ብለን እናምናለን በማለት ይመልስለታል፡፡ አርጌንስ ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር እንዳይበሉ ከከለከላቸው ዛፍ በበሉ ቀን አዳምንና ሔዋንን ያለበሳቸው ለምድ በእኛ ላይ ያለው የቆዳ ልብስ ነው፤ የቁርበት ለምድ ልብስ አይደለም ማለቱን በመንቀፍ እኛ ግን ሥጋስ ቀድሞም በተፈጠሩ ጊዜ አላቸው፤ በኋላ እግዚአብሔር ያለበሳቸው ግን የቁርበት ልብስ ነው፤ ትእዛዙን ስላቃለሉ የነቀፋ ልብስ ነው እንላለን ብሎ ይመልስለታል፡፡

፪. ምሥጢረ ሥጋዌ (ነገረ ክርስቶስ)

፪.፩ ንስጥሮስ

ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረ ሲሆን የክርስቶስን አካልና ባሕርይ ለሁለት በመክፈል ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ኅድረትን ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወልድንከነቢያት አንዱ ነው፤ የዮሴፍ ልጅ ነው› ለማለት እንዴት ደፈርህ?” የሚለው ስለዚህ ነው፡፡ ንስጥሮስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሰው እናት (Anthropothokos) እንጂ የአምላክ እናት (Theotokos) መባል የለባትም ያለ መናፍቅ ነው፡፡ በእርግጥ ያሻሻለ መስሎ የክርስቶስ እናት (Christotokos) እላታለሁ” ብሏል፡፡ ይህን ቢልም ግን ለንስጥሮስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ያደረበት ደግ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ለዚህ ነው አባ ጊዮርጊስ ንስጥሮስን እመቤታችን ማርያምን መለኮት ያደረበትን ሰው የወለደች እንጂ የአምላክ እናት እንደማይሏት ስለ ልጆችህ ዜና ሰማን በማለት የሚዘልፈው፡፡

ሊቁ ለዚህ ኑፋቄው መልስ ሲሰጥ በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ዐመጽ የሌለበት አምላክ፤ ኃጢአት የሌለበት ሰው፤ እድፍ የሌለበት ንጹሕ በግ፤ ነውር የሌለበት ፍሪዳ፤ ርኵሰት የሌለበት የበሰለ ኅብስት፤ አተላ የሌለው የጠራ የወይን ጭማቂ፤ የተወደደ ዕጣን፤ የሚያንጸባርቅ ሽቱ፤ የሕዝብን ኃጢአት ይቅር የሚል ኃጢአት የሌለበት ካህን፤ ፊት አይቶ ለሀብታም፣ ለደሀ የማያዳላ ንጉሥ ነው በማለት አምላክ ወሰብእ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ስለ እመቤታችንም ቀድሞ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ እንደተወለደ፣ በኋለኛው ዘመን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ከብቻዋ ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በመጀመሪያ የማይታይ እርሱ ከማይታየው ተወለደ፤ በኋላም የማይያዝ የሕይወት እሳት፣ ከምትዳሰስ ሥጋ ተወለደ፡፡ በመጀመሪያ የሀልዎቱ መጀመሪያ ሳይታወቅ ተወለደ፤ በኋላም የዘመናት ፈጣሪ ዓመታትንም የሚወስን እርሱ ዕድሜዋ ዐሥራ አምስት ዓመት ከሆነ ከታናሽ ብላቴና ተወለደ፡፡ የመጀመሪያ ልደቱን ምሥጢር የኋለኛ ልደቱንም ድንቅ አደረገ በማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗን በማስረዳት ከብሉያትና ከሐዲሳት እየጠቀሰ ያሳፍረዋል፡፡ ከሥጋዌ በኋላ ምንታዌ እንደሌለም የአርዮስን ክሕደት በዘለፈበት ድርሳኑ ሰው ከሆነ በኋላ በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ በሰውነቱ የማርያም ልጅ አንለውምበማለት ይነግረናል፡፡

፪.፪ የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ልዮን

ርጕም ልዮን በሦስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ (ጉባኤ ኤፌሶን) ሁለት መቶ ሊቃነ ጳጳሳት ተሰብስበው ያወገዙትን የንስጥሮስን ክሕደት በማሻሻል አንድ አካል ሁለት ባሕርይ” የሚል ክሕደት የጀመረ መናፍቅ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን መከፈልም ተጠያቂ ነው፡፡ ልዮን ሥጋ ከመለኮት ያንሳል ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” የተባለ አባ ጊዮርጊስ እኔ እና አብ አንድ ነን፤ ከሰማይ የወረደ ኅብስት እኔ ነኝ፤ ባለመድኃኒት ከሰማይ መጣ …” የሚሉትን ንባባት በመተርጎም እኛ ግን ‹ከተዋሕዶ በኋላ የክርስቶስ ትስብእት ከመለኮቱ አያንስም (አይጎድልም)› እንላለን፡፡ ባለመድኃኒት በድውዮች ሴት ልጅ ዘንድ አደረ፤ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገው፡፡ ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨት በዳዊት ቤት ተገኘ፡፡ ያለመለኮት ከሥጋ ጋር መዋሐድ ፈውስ እንደማይገኝ ባለመድኃኒቱ ዐወቀ፤ ስለዚህም ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ፡፡ ታማሚስ ለራሱ ፈውስን ያደርግ ዘንድ አይቻለውም፤ ነገር ግን በሚድንበት ገንዘብ መድኃኒት እንዲያደርግለት ባለመድኃኒቱን ይማልደዋል በማለት አፉን ያስይዘዋል፡፡

፪.፫ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች

በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ጉባኤ ከለባት በመባል በሚጠራው በኬልቄዶን ጉባኤ የተሳተፉት ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ኤጲስቆጶሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ጉባኤተኞች መለኮትና ሥጋን በመለያየት ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ ናቸው” የሚል እንግዳ ትምህርት ያመጡ ናቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስም መለኮት በሰውነት ሥጋ እንደሆነ፤ ሰውነትም በመለኮት አምላክ ሆነ፡፡ በመለኮቱ መቀየርን ስለ ሰውነቱም መለወጥን አናስብ፤ ስለ አንድነቱ መቀላቀልን፣ ስለ ባሕርይውም መለያየትን አናስብ፡፡ እርሱ በመለያየት ያልተከፈለ፣ በወንድማማችነትም ሁለት ያልሆነ ነው፡፡ በመለኮቱም በሰውነቱም አንድ እግዚአብሔር ነው በማለት መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡ እኛ ግንከድንግል ማርያም ሰው የሆነ አንድ አካል አንድ ባሕርይ (ፈቃድ) ነውእንላለንበማለትም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ አስረድቷቸዋል፡፡

ይቆየን