ዕረፍቱ ለአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ

ታኅሣሥ ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም  

የከበረ ገድለኛ አባት የዋልድባው አባ ሳሙኤል የአባቱ ስም እስጢፋኖስ የእናቱ ስም ደግሞ ዓመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጋግ ናቸው፤ እነርሱም በአክሱም ሀገር ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወለዱ። አንደኛው ስሙ ገብረ ክርስቶስ ሲሆን ይህ ሁለተኛው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው አባ ሳሙኤል ነው። እርሱንም ለመምህር ሰጥተውት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እየተማረ በትጋት ኖረ። ከዚህ በኋላም ያስተምረው የነበረ መምህሩ ስለ አባ ሳሙኤል ታላቅነት ትንቢት ተናገረና በመቶ ዓመቱ ዐረፈ።

አባ ሳሙኤልም አባትና እናቱ እንዳረፉ ተነሥቶ ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ (አባ አድኃኒ) በመሄድ በደብረ በንኰል መኖር ጀመረ። በዚያም ትጋቱን ያዩ የአባ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዛሙርት አባ ምንኲስና አስኬማ የሚገባው ደገ’ኛ ነውና እንዲያመነኩሱት ነገሩት። አባ አድኃኒም ትጋቱንና ተአዛዚነቱን ተመልክቶ አመነኰሰው። በዚያም ለሁላቸውም እየታዘዘ እንደመንኰራኲር በመፋጠን ያገለግል ነበር። የራሱን ሥራ ጨርሶ የደከማቸው ካለ ፈጥኖ መሄድ የነርሱንም ሥራ በመሥራት ያግዛቸው ነበር። በዚህም አፍቅሮ ቢጽን በግብር በግልጥ አሳያት። አባ መድኃኒነ እግዚእም በእጅጉ ወደደው። ነገር ግን በዚህ ገዳም ሲቆይ የሻገተ ጎመንና ጥቂት ውኃ ካልሆነ በቀር ምንም ምን ሌላ እህል አይቀምስም። እንዲህ ራሱን ሥጋውን በገድል እየቀጠቀጠ ቢኖርም ዘመዶቹ ግን እየመጡ ስላወኩት ለአባ መድኃኒነ እግዚእ አስፈቅዶ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ እግሮቹ እስኪያብጡ ድረስ እንደመንኰራኲር ይሰግድ፣ እጅግም ብዙ ጊዜ ይጸልይ ነበር። ከዚህም የተነሣ ሊቁ አባታችን ማር አባ ጊዮርጊስ ሲያመሰግነው ‹‹ሰአል ለነ ሳሙኤል አቡነ ሠረገላ ጸሎት፤ የፈጣን የጸሎት ሠረገላ የሆንክ ሳሙኤል ሆይ ለምንልን›› በማለት ተማጽኖታል።

ከዚያም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ በረኃ ወጥቶ ሲጋደል አናብርትና አናብስት ይሰግዱለትና ይገዙለትም ነበር። አንድ ዕለት አንዲት ለመውለድ የደረሰች አንበሳ ከበዓቱ መጣች። እርሱም ነገሩን አውቆ ቦታ ካስተካከለላት በኋላ መንታ የሆኑ ወንድና ሴት ደቦሎችን ወለደች። ወንዱም ሴቷን እየተጋፋ ሲጠባ አባ ሳሙኤል ግን ተራ በተራ እንዲጠቡ ያደርጋቸው ነበር። በሌላም ጊዜ አንድ አንበሳ እግሩ በእሾህ ተወግቶ አቂሞበት በጽኑዕ ታሞ ከውኃ ዳር ሁኖ ከደቀ መዝሙሩ ጋራ ሲጓዙ አዩት። ደቀ መዝሙሩም ውኃ ጠጥቶ ደክሞት የተኛ መስሎት ነበር። በኋላም ቀረቡና አባ ሳሙኤል ወስፌ አምጥቶ እሾሁን አወጣለት፤ ቂሙንም አፈረጠለት። ያም አንበሳ ከዚያ ልክ እንደእምቦሳ በአባ ሳሙኤል ፊት ይዘል ነበር።

አንድ ቀንም መጽሐፉን ሸክፎና የእሳት ማኅቶት ይዞ ሲጓዝ ታላቅ ወንዝ ውኃው እስከ አፉ መልቶ ገጠመው። አባታችንም በእምነት በውስጡ ገብቶ ተጓዘ። ሲገባበትም ውኃው ከራሱም በላይ ሞልቶበት ነበር። ተሻግሮ ሲወጣ ግን የእግዚአብሔር ድንቅ ቅዱስ ክብሩ እንዲገለጽ የቸሩ አምላክ ፈቃዱ ስለነበር እሳቱም አልጠፋ፣ ከመጻሕፍቱም አንዲቱ ቅጠን ስንኳ የውኃ ጠል አላገኛትም።

ጸላኤ ሠናያትም እጅግ ብዙ ጊዜ ይፈታተነው ነበር። አባ ሳሙኤል ግን በጸሎቱ ኃይል ድል ያደርገዋል። አንድ ዕለትም ጥልቅ ጉድጓድ አስቆፍሮ ለዐራት ወራት እህል ውኃ ሳይቀምስ ቆዳው ከአጥንቱ እስኪጣበቅ ሥጋውን አስጨንቆ ሲጋደል ከቆየ በኋላ ጌታችን ከአእላፍ መላእክት ከእመቤታችን እና ከቅዱሳን ጋር መጥቶ ባረከው፤ በምራቁም መላ ሰውነቱን ቀብቶ ኃይልን አሳደረበት። እንዲሁ ጣቱንም ሦስት ጊዜ ቢያጠባው ረኃብ የሚባል ነገር ሁሉ እልም ብሎ ጠፋለት። ከዚያችም ዕለት አንሥቶ እግሮቹን እያሠረ ማቅንም ለብሶ በየዕለቱ ከባሕር እየሰጠመ መዝሙረ ዳዊትን አምስት ጊዜ እየመላለሰ ቁጥር በሌለውም ግርፋት ራሱን ሥጋውን ይቀጣ ነበር። አናብስቱንም ልክ እንደፈረስ ለዕቃም ለመጓጓዝም ይገለገላቸው ነበር። እነርሱም እጅጉን ይታዘዙለታል።

ብዙ ደቀ መዛሙርትም ወደርሱ መጥተው የርሱ ልጆች ሆኖ። አንድ ዕለትም አባ ገብረ መስቀል ከሚባል ደገ’ኛ ጻድቅ አባት ጋር ተገናኝየው ሲጨዋወቱ አመሹ። ከዚያም በፊት ተያይተው አያውቁም ነበር። የእራትም ሰዓት ሲደርስ ተነሥተው በጸሎት ቢተጉ ከሰማይ የተዘጋጀ ማዕድ ወርዶላቸው አብረው ተመግበዋል። በሌላም ጊዜ ከአንድ ገዳማዊ አባት ሲነጋገሩ አባ ሳሙኤል ለዚያ ደግ ሰው ሲናገር ‹‹እነሆ እኔ በአርያም ቁሜ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የአምላክን መንበር ሳጥን ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነኝ›› አለው። ጻድቁ አባ ሳሙኤል አባታችን ለመቀደስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ የሚቀድስበት ጽዋዕ እና ኅብስት ከሰማይ የሚወርድለት ነበር።

ከዚህ ሁሉ ላይ ከዚህ ደገ’ኛ ጻድቅ የምናነሳለት ነገር ለንጽሕት የአምላክ እናት ለእመቤታችን ያለውን ጽኑዕ ፍቅር ነው። እርሱም ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ አስተባብሮ የሚደግም ነበር። በሚጸልይበትም ጊዜ ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ይል ነበር። እመቤታችንም በእጅጉ የምትወደው ንጹሕ ድንግል ተጋዳይ መነኰስ አባት ነው። ተያይዞም የሚነሣው አባታችን ምግብ ባሻቸው ጊዜ በውኃው ላይ ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ አድርጎ ቢጸልይ ኅብስት ሁኖላቸው ይመገቡት ነበር። ንጽሕት እመቤታችንም አንድ ዕለት ተገልጻለት በክብር ታየችውና ንጹሕ ዕጣንን ከሚያበራ ዕንቊ ጋራ ሰጥታዋለች።

ዕረፍቱ በደረሰ ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናውያን አክናሱ ተሸክሞ ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን አሳየውና ወደ ልዑል እግዚአብሔር አቀረበው። ቸሩ አምላካችንም በማይታበለው ቃሉ ጽኑዕ ቃልኪዳንን ሰጠው። ወደ ቀደመ አኗኗሩም በተመለሰ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፤ ከዚህም ሁሉ በኋላ በሰላም ዐረፈ።

እግዚአብሔር አምላካችን በዚህ ኃያል ገድለኛ ጻድቅ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ትደርብን፤ ለዘላለሙ አሜን።