ዕረፍተ አባ ኪሮስ

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በሀገረ ሮም ከአባቱ ንጉሥ አብያ ከእናቱ አንሰራ ተወለደ፡፡ ደጋግና ቅዱሳን ወላጆቹም እግዚአብሔርን በመፍራት እየኖሩባት በነበረበት ወቅት ይህን የተመረጠ አባት ሰጣቸው፤ አባ ኪሮስ የተወለደው በታኅሣሥ ፰ ቀን ነበር፡፡ ጻድቁ አባት በቅድስና ሕይወትና ትጋት ማዕረግ አባ ኪሮስ ከመባሉ በፊት ‹ዲላሶር› ተብሎ ይጠራ እንደነበር ታሪኩ ይገልጻል፡፡

ቅዱሱ ከታላቅ ወንድሙ ቴዎድሮስ ጋር በሚኖርበት ጊዜ አባቱ ስለሞተ ሀብቱን ከወንድሙ ጋር በመካፈል ለድሆች መጸወተ፤ መንፈስ ቅዱስ ኪሮስ ብሎ ጠራውና “ለብዙዎች አባት ትሆናለህ፤ በቃልህም ክርዳድ ይነቀላል፤ የአንድ ቀን መንገድ ሂድና ገዳማዊ መነኰስ ታገኛለህ፤ ከእርሱም ልብሰ ምንኲስና ትለብሳለህ” አለው፡፡ እንደ ታዘዘው በሄደ ጊዜ ከአንዲት በዓት የራስ ፀጉሩ እስከ እግሩ የሚደርስ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ወጥቶ “ኪሮስ መነኲሴ ለመሆን ወደዚህ መጣህን? አለው፡፡ ኪሮስም ግርማውን እያደነቀ ቀርቦ ተባረከና ሦስት ቀን ከቆየ በኋላ “ኪሮስ ሆይ፥ እንደ እኔ መሆን ትፈልጋለህን?” አለው፡፡ እርሱም “አዎ፥ በጣም እፈልጋለሁ” ባለው ጊዜ አባ በብኑዳ ትንሽ ደመናን ጠርቶ በዚያ ላይ በመሆን ከአስቄጥስ ገዳም በመሄድ የምንኲስናን ልብስ ተቀብሎ በዚያችው ደመና ኪሮስ ካለበት ቦታ ተመለሰ፡፡ ያመጣውን አልባሰ ምንኲስናም ለኪሮስ አለበሰው፡፡

ለአባ በብኑዳ ሁልጊዜ በሠርክ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋዐ ወይን ቅዱስ ሚካኤል ያመጣለት ነበር፡፡ አባ ኪሮስ በዚያ ለአባ በብኑዳ እየታዘዘ ሲኖር አንድ ገዳማዊ ሰው ወደ አባ በብኑዳ መጥቶ ሳለ ምንም ነገር እንደሌለው ዐይቶ “ምን ትበላለህ?” ቢለው “አምላካችን ይሰጠናል” አለው፡፡ ያ እንግዳ መነኲሴም በልቡ “እንደ እኛ ሰው አይደለምን?” እያለ ሲያስብ አባ በብኑዳ በመንፈስ ዐውቆ “ለምን እንዲህ ታስባለህ?” “እኔም እንዳንተ በደለኛና ኀጥእ የሆንኩ መነኲሴ ነኝ” አለው፡፡ ይህን እየተነጋገሩ ሳለ የሠርክ ጸሎት ደርሶ በኅብረት ሲጸልዩ ፈጽሞ ደስ የሚል መዓዛ መጣ፤ ወዲያውም የተዘጋጀ ኅብስትና ጽዋዐ ወይን ይዞ ቅዱስ ሚካኤልን ሲመጣ አየውና ተቀበለው፤ ያ እንግዳ መነኲሴ ግን አላየውም፤ አሁንም “አስቀድሞ ያልነበረ ይህን ጽዋና ኅብስት ከየት አገኘው? ይህ ባሕታዊ መሠሪ ነው” እያለ አሰበ፤ አባ በብኑዳም “ለምን እንዲህ ክፉ ታስባለህ?” አለው፤ መነኲሴውም አድንቆ ተቀምጠው መመገብ ጀመሩ፡፡

ያ እንግዳ መነኲሴ ግን ከዚያ ኅብስተ ሰማይ ቆርሶ በልብሱ ደብቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደ፡፡ በዚያ ያሉ መነኰሳትንም ሰብስቦ ያን በረድ የሚመስል ኅብስተ ሰማይ አሳያቸው፡፡ “የት አገኘኸው?” ቢሉት “በዮርዳኖስ ገዳም ውስጥ በብኑዳ የሚባል መሠሪ ሰው አለ፤ ኑ ተከተሉኝና ታመጡት ዘንድ ወደዚያ ልውሰዳችሁ” አላቸው፡፡ ይህን ሲነጋገሩ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ያችን የኅብስት ቁራሽ ወደ ሰማይ ወሰዳትና በልዑል ፊት ሰገደ፤ እግዚአብሔርም “መልካም አገልጋዬ ሆይ፥ የተቀደሰውን ለውሻ የሰጠ በብኑዳ ክፉ አደረገ፤ ስለዚህም በአንበሳ ተሰብሮ እንዲሞት አደረግኹ፤ ይህም በረከት ይከለከላል፤ ይህንንም ኅብስት በበረሃ ላለ ፊልሞና ለሚባል መነኲሴ እስከ ዕለተ ሞቱ ሲሳይ እንዲሆነው ስጠው” አለው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም እንደ ታዘዘው አደረገ፡፡ የአስቄጥስ ገዳም ቅዱሳንም ያን መነኲሴ “እኛን ማን መምህርና ፈራጅ አድርጐ ሾመን” አሉት፤ በዚህ ጊዜ አዘነና ወደ ማደርያው ሂዶ ታንቆ ሞተ፡፡

አባ በብኑዳም ይመጣለት የነበረው መና ተከለከለ፤ ሦስት ቀን ምንም ሳይቀምስ ከቆየ በኋላ እያለቀሰ አባ ኪሮስን “ልጄ ሆይ፥ ሰይጣን ወደ ማደርያችን ገብቶአል፤ ያገኘን ይህ ነገር ምንድን ነው?” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “ያ መነኲሴ መጥቶ ከሄደ በኋላ እግዚአብሔር ተቆጥቷል” አለው፡፡ አባ በብኑዳም “የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን” አለ፡፡ ከዚያም አባ ኪሮስ ፍሬን እየሰበሰበ ይመለስ ነበር፤ አባ በብኑዳ ግን በቀንም ሆነ በማታ ከበዓቱ ሳይወጣ ይጸልይ እንደ መንኰራኲርም ይሰግድ ነበር፡፡

አባ ኪሮስም እንዲህ እያለ ሲኖር አንድ ቀን የዕለት ሲሳይ ፍለጋ ወደ አንድ ሀገር ሄዶ ሳለ የኬልቄዶን ንጉሥ ሞቶ፣ ሕዝቡ ሁሉ እየጮኹና እያለቀሱ፣ ምድር እየረገጡ፣ ብዙ የፈረሰኛ ሰልፍ ተሰልፎ፣ በአስከሬኑ ላይ ድባብ እየዘረጉ ካህናት በማዕጠንት በፊቱና በኋላው እየዘመሩ ባየ ጊዜ አንዱን ሰው “ይህ የማየው ምንድን ነው?” ብሎ ቢጠይቀው “የኬልቄዶን ንጉሥ ስለ ሞተ ነው” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “ለሞተ ሰው ይህን ያህል ይደረጋልን?እኔስ ንጉሥ ለልጁ ሠርግ ያደረገ መስሎኝ ነበር” አለ፡፡ ይህን ብሎ አልፎ ፍሬ ሰብስቦ ወደ ማደርያው ወደ አባ በብኑዳ በደረሰ ጊዜ አጽሙ በየቦታው ተበታትኖ አንበሳ ሲበላው ባገኘ ጊዜ በጣም አምርሮ እያለቀሰ “ጌታ ሆይ፥ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? ፍርድህ መልካም አይደለም፤ በመንግሥት፥ በመብልና በመጠጥ በደስታ የኖሩትን በክብር እንዲቀበሩ ታደርጋለህ፤ ስለ አንተ ሲሉ አባትና እናትን፣ ሚስትንና ልጆችን ደስታን ሁሉ ትተው በተራራና በዋሻ በጾምና በጸሎት የኖሩትን ደግሞ ሥጋቸውን ለዱር አራዊት ትሰጣለህ፤ የአንተን ፍርድ ነገር ላልሰማ እንዳልነሣ ሕያው ስምህን” ብሎ መሬት ላይ ተኛ፡፡ አርባ ዓመት ሲሆነው ግማሽ ሥጋው አለቀ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልአክ አምሳል ተገልጾ “ተጋዳይ የሆንክ አርበኛ ኪሮስ ሆይ፥ ሰላም ላንተ ይሁን፤ ተነሥ” አለው፡፡

ኪሮስም “አንተ ማነህ? መልአከ እግዚአብሔር ከሆንክ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ በል” አለው፡፡ ጌታችንም “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” አለ፡፡ ኪሮስ መነሣት ባቃተው ጊዜ ምድርን “ሥጋውን አትያዥ” ባላት ጊዜ ፈጥኖ ተነሣ፤ ኪሮስም ጌታችን እንደ ሆነ ዐወቀው፤ መላ ሰውነቱን ዳበሰው፤ ሰውነቱ እንደ ሕፃን ሆነ፤ በምድር ላይ ሰግዶ ጌታችን እንደ መብረቅ ሲለወጥና እልፍ አእላፋት መላእክት ሲያመሰግኑት አያቸው፡፡ ጌታችንም “ኪሮስ ሆይ፥ አንተ ሚስትህን፣ ልጆችህን፣ መንግሥትህን የተውህልኝ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ነኝ፤ ስለ ሁሉ ብዙ የብዙ ብዙ ታገኛለህ፤ በምድር ላይ እንዳንተ ትዕግሥትን የለበሰ አላገኘሁም፤ ለዚያ እንግዳ መነኲሴ ቅድሳቴን ለምን ሰጣችሁት? ስለዚህ ነው የበብኑዳን ሥጋ ለአራዊት የሰጠሁት፤ በዚህ ምክንያት በፊቴ እንዳይወቀስ ነው፡፡ ለሁሉ ሥራ ፍዳ አለውና፤ አምላኩ በምድር ላይ የገሠጸው ሰው ብፁዕ ነው፤ ያለውን አልሰማህምን?” ኪሮስም “ጌታዬ ሆይ፥ ፍርድህ ቅን ነው” አለ፡፡ ጌታችንም “ከዚህ በኋላ የነፍስን ከሥጋ መለየት ታይ ዘንድ በገዳማት ሂድ፤ ከዚያም ወደ ማደሪያህ ተመለስ” ብሎት ተሠወረ፡፡

አባ ኪሮስ በጌታችን ታዝዞ ደብረ ባሳት በደረሰ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ተሳልሞ፣ የእመቤታችንን ሥዕል ዐይቶ ከዐይኖቹ እንባ እያፈሰሰ “እመቤቴ ሆይ፥ አስቢኝ” አላት፡፡ ሥዕሊቱም “ኪሮስ ሆይ፥ መምጣትህ መልካም ነው፤ የአባትህን ዐፅም ትጠብቅ ዘንድ ወደ ማደርያህ ተመለስ” አለችው፡፡ ይህን ሰምቶ ከሥዕሏ ፊት ሰባት መቶ ስግደት ሰገደ፤ በዕብራይስጥ ቋንቋም “እንግዳ ነህና በቃህ፥ በምሕረት መዝገብም ተመዝግቦልሃል” የሚለውን ቃል ሰማ፡፡ ከዚያም መስፈርስ የሚባል ሕማም ለብዙ ጊዜ የታመመና በምድር ላይ የወደቀ ሰውን አገኘ፡፡ በራስጌው ቅዱስ ሚካኤልን፣ በግርጌው ገብርኤልን፣ በቀኙም ሩፋኤልን፣ በግራውም ሰዳክኤልን በክንፋቸው ጋርደውት ዐየ፡፡ እነርሱም “በገዳዮች ፊት ሞትን የማይፈራ ሆይ፥ እንዴት ነህ?” ብለው ሰላምታ ሰጡት፡፡ እርሱም አድንቆ “በልዕልና ነዋሪዎች ሆይ፥ በዚህ ለምን ተቀመጣችሁ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “ይህን ድሀ እንድንጠብቀው ከእግዚአብሔር ታዝዘናል” አሉት፡፡ “እስከ

መቼ?” ቢላቸው “አምላካችን እስከሚያሳርፈው ድረስ” ብለውታል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ታመመው ተመልሶ “በዚህ ቦታ ከኖርህና ከታመምህ ምን ያህል ዘመን ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ በሽተኛውም “በዚህ ቦታ ስኖር ፷፭ ዓመት ነው፤ ከታመምኩ ሃያ ዓመት ነው” አለው፡፡ መልሶም “አበ ምኔቱና የገዳሙ መነኰሳት ይጐበኙሃል” አለው፡፡ በሽተኛውም “አባቴ ሆይ፥ የለም፤ ፊታቸውን ከዐየሁ ዐሥራ አምስት ዓመት ነው” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “አባትህ ማነው? እናትህስ ማናት?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “አባቴ የኬልቄዶን ንጉሥ ነው፤ እናቴም ንግሥት ናት፤ በአባቴ ቤት ያሉ ሰዎች ወርቁንና ብሩን ቀጭኑንም ልብስ ከብዛቱ የተነሣ በእግሮቻቸው ይረግጡታል” አለው፡፡ ጥያቄውን በመቀጠል “ወደዚያች ገዳም ማን አደረሰህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም “እንደ አንተ ያሉ ሁለት ሰዎች ወደ አባቴ ቤት መጥተው ከዚያ አደሩ፡፡ እኩለ ሌሊትም ሲሆን ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰው ወደ እኔ መጥቶ “ሚሳኤል” ብሎ ጠርቶ “ሲነጋ ተነሥተህ ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር ሂድ” አለኝ፡፡ እኔም ወጥቼ ወደዚህ ገዳም ደረስኩ” አለው፡፡ አባ ኪሮስም የአባቱን የበብኑዳንና የሌሎችንም ቤተ መንግሥትን እየተው የመነኑ ቅዱሳንን ሁኔታ እያነሣ አጽናናው፡፡ “እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻልና አታድንቅ” አለው፡፡ ያ በሽተኛ /ሚሳኤልም/ “እውነት ነው ለእኔ ይገባኛል። ስለ ኃጢአቴም ይህን ተቀበልኩ” ብሎ መለሶ ዝም አለ፡፡

ያን ጊዜ በሞት ያሰናብተው ዘንድ አባ ኪሮስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ጌታችንም በክብር መጣ፡፡ ጌታችንም አባ ኪሮስን “ምን ያህል እንደምወድህ የመላእክት ሠራዊት ያዩና ያውቁ ዘንድ ይህችን የገነት ተክል አበባ ከእጄ ወስደህ በፊቱ ላይ ጣል” አለው፡፡ ኪሮስም እንዲሁ አደረገ፡፡ ያን ጊዜ የበሽተኛው የሚሳኤል ነፍስ ያለ ጻዕር በፍጥነት ወጣች፡፡ መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት፡፡ ከእርሱ ጋርም በብርሃን ሠረገላ ውስጥ አስቀመጣት፤ አውጥቶም በሰማያዊ ክብር አኖራት፤ አባ ኪሮስም አለቀሰ፡፡ አባ ኪሮስም የገዳሙን መነኰሳት “ያን በሽተኛ ቅበሩት” ሲላቸው ፈቃደኞች ባለመሆን እያንጐራጐሩ ነበር፡፡ አራቱ የመላእክት አለቆች ሥጋውን በከርቤና በሚዓ አጠኑ፡፡ የገዳሙ መነኰሳትም “የሚሸተን ምንድን ነው? ይህ መነኰስ ሥራይን ያውቅ ይሆንን?” ተባባሉ፡፡ ሥጋውንም በገዳሙ በእንግዳ መቃብር ቀበሩት፤ ከመቃብሩም ጥሩ ውኃ ፈለቀ፤ ለበሽተኖችም ፈውስ ሆነ፡፡ አባ ኪሮስም እነዚያን መነኰሳት “በክፉ ሥራቸው ገሠጻቸው፤ መከራም ይመጣባችኋል” አላቸው፡፡ ሊወግሩትም ድንጋይ በአነሡ ጊዜ ሠረገላ መጥቶ ወደ ማደርያው አደረሰው፡፡ በማግሥቱም ሽፍቶች መጥተው የዚያን ገዳም መነኰሳት በሙሉ ፈጁአቸው፤ ገዳሙንም አቃጠሉት፡፡

አባ ኪሮስ በበዓቱ ሆኖ ሠራዊተ ጽልመት የእነዚህን ክፉዎች መነኰሳት ነፍሳት እያቻኰሉ ወደ ሲኦል ሲወስዷቸው ዐይቶ “ይገባቸዋል” አለ፡፡ በኋላ ግን “እነዚህን ስሑታን አሳቱኝ” ብሎ እግዚአብሔር ይምራቸው ዘንድ ፵ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ “አልምራቸውምና አትድከም” የሚል ቃልን ሰማ፡፡ ከዚያም ከጋለ ድንጋይ ላይ ተኝቶ ሥጋው በእሳት እንደ ተጠበሰ እስኪሆን ቆየ፤ ቃልም “አልምራቸውምና አትድከም” አለው፡፡ እንደ ገና በሆዱ ተኝቶ ዐይኑ ወልቆ ታወረ፡፡ ሰይጣንም ከሩቅ ሆኖ “ብዙዎችን በኪዳንህ ያሳትክና ገንዘቤን ልትወስድ የተነሣህ ኪሮስ አንተ ነህን?አሁን ዐይንህ ጠፋ ማን ይረዳሃል? ማንስ ይመራሃል?” አለው፡፡ ይህን ሲሰማ አባ ኪሮስ ወደ ጌታችን ፈጽሞ እያለቀሰ ጸለየ፤ ጌታችንም ወደርሱ መጥቶ “ኪሮስ ሆይ፥ ሰላም ላንተ ይሁን፤ በእውነት አንተ ሰውን ወዳጅ ነህ፤ ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተመዝግቧል፡፡ ልጁን በስምህ ለሚጠራ፣ በእምነት ሆኖ የገድልህን መጽሐፍ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ መባዕና ዕጣን ለቤተ ክርስቲያንህ የሰጠውን ላንተ ዓሥራት ይሆን ዘንድ ሰጠሁህ፤ ካንተም ጋራ ባሕረ እሳትን ይለፍ፤ ደስም ይሰኝ” አለው፡፡ ይህንኑ ብሎ ራሱን በእጆቹ ይዞ ፈወሰው፡፡ ቅዱስ ኪሮስም “በፊትህ ሞገስ ካገኘሁ እነዚያን መነኲሳት ማርልኝ” አለው፡፡ ጌታችንም ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፤ ነፍሳቸውንም ከሥጋቸው ጋር አዋሕዶ አሥነሳቸው፤ አባ ኪሮስንም በዐዩ ጊዜ አፈሩ፡፡ በአባ ኪሮስ ልመና አልባሰ ምንኲስና ለበሱ፤ ወደ ገዳማቸው የሚወስድ መንገድንም አሳይቶአቸው እንዲሄዱ አዘዛቸው፡፡ ከገዳማቸውም ደርሰው ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በጾም በጸሎትና እንግዳ በመቀበል ኖሩ፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ “ቅዱስ ኪሮስ የእነዚያን መነኰሳት ሕይወታቸውን ያይ ዘንድ መልአኩን ላክ” ብሎ በጸለየ ጊዜ ጌታችን “አንተው ሄደህ ጐብኛቸው” ብሎ ደመናን ጠርቶና በዚያች ላይ አውጥቶ “በሰላም ሂድ” ብሎ አሰናበተው፡፡ ኪሮስም ወዲያው ደርሶ ወደ ሚሳኤል መቃብር ሄደ፤ መነኰሳትም ባዩት ጊዜ ከአበምኔቱ ጋር ሮጠው ሄደው አቅፈው እየሳሙት “ደኅና ነህን?” አሉት። እርሱም “ውሻና ነዳይ ለምሆን ለእኔ ይህ ክብር ለምኔ ነው?” አላቸው፡፡ እነርሱም “ባለማወቃችን ያሳዘንህን ይቅር በለን” ባሉት ጊዜ “እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም የእግዚአብሔር አገልጋይ ሚሳኤል ሆይ፥ ይቅር በለን በሉ” አላቸው፡፡ እነርሱም “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሚሳኤል ሆይ፥ ይቅር በለን” አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ “እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ፤ በእናንተ ምክንያት ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብቻለሁና” የሚል ቃል ሰሙ፡፡ እነርሱም “ይህ የናቅነውና የጣልነው ሚሳኤል አይደለምን?” ብለው እያደነቁ አጽሙን ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያስገቡት በፈለጉ ጊዜ “ባለበት ተውት፤ ነገር ግን በጸሎቱ ትጠቀሙ ዘንድ ተዝካሩን አድርጉ” አላቸው፡፡ እርሱም እየመከራቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ አባ ኪሮስም “የክርስቶስ ማደረያው ሆይ፥ ሰላም” ብሎ በተሳለመ ጊዜ “በሐከ ፈላሲ ክቡር፤ ክቡር መጻተኛ ሆይ ሰላም” ስላለው አደነቀ፡፡ አበ ምኔቱም “በቤቴ እደር” ቢለውም “አይሆንም” ብሎ በሚሳኤል ማደርያ በነበረው አንጻር ሄዶ አደረ፡፡ በማግሥቱም “ከእንግዲህ ወዲህ በመንግሥተ ሰማያት እንጂ በዚህ ምድር አንተያይምና በጸሎታችሁ አስቡኝ” ብሎ ተሰናብቷቸው ወደ ማደሪያው ተመልሶ አጋንንትን ‘ኑ’ ሲላቸው እየመጡ ‘ሂዱ’ ሲላቸው እየሄዱ ሲገዛቸው ኖረ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኪሮስ በገድልና በትሩፋት እየተቀጠቀጠ ለብዙ ዘመናት ከኖረ በኋላ በ፪፻፸ ዓመቱ ሐምሌ ፰ ቀን ቅዱስ ዳዊት እየዘመረለት እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት በተገኙበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ አሳርጓታል፡፡ ጌታችንም የአስቄጥስ ገዳም አባ ባውማ ሥጋውን ገንዞ እንዲቀብረው አደረገ። እርሱም የንጉሥ ዘይኑን ልጅ ቅድስት ኢላርያን ሥጋዋን የገነዘ ነው። ደግሞም አባ ባውማ ጌታችን እንዳዘዘው በመንፈስ ቅዱስ የቅዱስ ኪሮስን ገድሉን የጻፈ ነው። “እኔ አባ ባውማም የቅዱስ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ” ተብሎ ተጽፏል። (ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ)