ዕረፍተ ቅድስት ሐና

ኅዳር ፲ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ቅድስት ሐና የትውልድ ሐረጓ ከአብርሃም ዘር ነው፡፡ አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቅብን፣ ያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና ዐሥራ አንድ ወንድሞቹን ወለዱ፡፡ ከዚህም በኋላ ሌዊ ቀዓትን፣ ቀዓት እንበረምን፣እንበረም አሮን ካህኑን ወለዱ፡፡ ቅዱስ አሮን አልዓዛርን፣ አልዓዛር ፊንሐስን እንዲህም እያለ እስከ ቴክታና በጥርቃ ይወርዳል፡፡

ከዚህም በኋላ ቴክታ ሕልም አለመች፡፡ ለባሏም ነገረችው፤ «በራእይ ነጭ ዕንቦሳ ከበረታችን ስትወጣ፤ ያችም ዕንቦሳን እየወለደች እስከ ፮ ትውልድ ስትደርስ ፮ኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃ ደግሞ ፀሐይን ስትወልድ አየሁ» አለችው፡፡ (ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ) እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላት፤ «ራእዩስ ደግ ነው፤ የሚፈታልን የለም እንጂ» አላት፡፡ ስለዚህም ሕልሙን ለማስፈታት በማግሥቱ  ሕልም ፈቺ ጋር ሄዶ ሕልሙን ነገረው፡፡ ሕልም ፈቺውም «እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፤ በሣህሉ መግቧችኋል» ብሎ ደጋግ ልጆች እንደሚወልዱ፤ ፯ኛይቱ በጨረቃ መመሰሏ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት እንደሚወልዱ፤ የፀሐይ ነገር ግን እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አልተገለጸልኝም» ብሎ ፈታለት፡፡ (ነገረ ማርያም)

በጥሪቃም ለሚስቱ ሄዶ የሕልሙን ፍቺ ነገራት፡፡ በዚያም ወር የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ተፀነሰች፡፡ በ፰ኛው ቀን ስሟን  ሄኤሜን አሏት፤  በሥርዓት አሳደጓት፡፡ እርሷም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ባል አግብታ ሴት ልጅ ወለደች፤ ሄኤሜን ልጅም ዴርዴን ትባላለች፡፡ ዴርዴንም ቶና የምትባል ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ቶና ደግሞ ሲካርን ወለደች፤ሲካርም ሔርሜላን ወለደች፤  ሔርሜላንም በሥርዓት አሳድጓት፤ እርሷም ባል አግብታ ሐና የተባለች ልጅ ወለደች፤ የሐና ወላጆች ልጃቸውን በሥርዓት አሳደጓት፡፡ ለአካለ መጠን ስትደርስም ኢያቄም የተባለውን ጻድቅ ሰው አጋቧት፡፡ ሐና ግን ልጅ መውለድ አልቻለችም፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም ቅድስት ሐና ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክታ «ፈጣሪ ሆይ! የእንስሳትን ማኅፀን የምትከፍት ዕፅዋትንም ከባሕርያቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ እውነትም ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?» ስትል አለቀሰች። ቅዱስ ኢያቄምም ወደ ተራራ ወጥቶ ለዐርባ ቀናት አለቀሰ። ይህ ሲሆን ሁለቱም አርጅተው ነበር። ፈጣሪ ልጅ ከሰጣቸው ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን ለመስጠት ስእለት ተሳሉ፡፡

በሐምሌ ፴ ቀን ኢያቄም ለሐና ራእይ አየ፤ነጭ ርግብ ፯ቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ በራሷ ስታርፍ በቀኝ ጆሮዋ ገብታ በማኅፀኗ ስታድር አየ፤ሐናም ለኢያቄም ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አብባ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ ብላ» ነገረችው፡፡ ከዚህም በኋላ በነሐሴ ፯ በዕለተ እሑድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፀንሰቻት፤ይህም ለእነርሱም ለወገኖቻቸውም ታላቅ ተድላ ሆነ። ብፅዕት ሐና ግን ፈጣሪዋን ታከብረው ዘንድ በጐነትንና ንጽሕናን አበዛች። ፀንሳ ሳለም ዕውራንን አበራች፤ ድውያንን ፈወሰች። የጦሊቅ ልጅ በሞተ ጊዜም እያለቀሰች ስትዞረው ጥላዋ ቢያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ፦ «ሰላም ለኪ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ» ብሎ ድንግል ማርያምን «ወሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ» ብሎ ቅድስት ሐናን አመስግኗል። ትርጉሙም ድንግልን «የፀሐየ ጽድቅ እናቱ» ሐናን «ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አያቱ» ማለት ነው። ይህንን ያዩ አይሁድ ቅድስት ሐናን ሊገድሉ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ግን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አልፈቀደላቸውም።

ቅድስት ሐናም እመቤታችን ቅድስት ማርያምን በፀነሰች በ፱ኛው ወር ግንቦት ፩ ቀን ነቢያት የተናገሩ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመተ ዓለም በፈቃደ እግዚአብሔር ወለደቻት፡፡ ይህችም ቅድስት ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ማደሪያ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ለመረጣት ከፍጥረት ሁሉ የተለየችና የከበረች ቅድስት ድንግል ማርያምን ለመውለድ የተገባች ሆናለች፡፡

ቅድስት ሐናና ልጇ ሦስቱ ዓመታት እስኪሆናት ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር። አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች። ከዚህም ግን መልሰውላታል። ነገር ግን ስእለታቸውን የሚሰጡበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ ሳይሰስቱ ለእግዚአብሔር ቤት እንድታገለግል ሰጧት፤ ቅድስት ሐናም ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በኋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለአምስት ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት ትስማትም ነበር። እመቤታችን ስምንት ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ። ከክርስቶስ ልደት ስምንት ዓመታት አስቀድማ ብፅዕት እናት ቅድስት ሐና በኅዳር ፲፩ ቀን ዐረፈች።

 ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!