ዕረፍተ ሕፃን ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ

ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል ሀገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ኢየሉጣ የተባለች ደግ ሴት ነበርች፡፡ እርሷም ቂርቆስ የተባለ በሥርዓት ያሳደገችው ሕፃን ልጅ ነበራት፡፡ በዚያን ዘመን እለእስክንድሮስን የተበላ አረማዊ መኰንን  ነበር፤ ይህችም ቅደስት ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ ተሰደደች፡፡

ነገር ግን በዚያ የሸሸችውን መኰንኑን አገኘችው። እርሷን የሚያውቋት ሰዎችም ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ መኰንኑ ጋር በመሄድ ነገሩት። መኰንኑም ቅድስት እየሉጣን አስጠርቶ ጠየቃት። ቅድስት ኢየሉጣም ‹‹መኮንን ሆይ፥ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ›› አለችው።

ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው፤ ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና ‹‹አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ?›› አለው። ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስም መለሰለት እንዲህም አለው።‹‹አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ደስታዬም ተጠብቆልኛል። ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና›› አለው። እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ብዙ ተናገረ። ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ።

በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

መኰንኑም በአፈረ ጊዜ በየዓይነቱ በሆነ ታላላቆች እንኳ የማይችሉትን ታላቅ አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሰቃየው። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም ከእርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሠቃያት። እግዚአብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሣቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ፤ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማኃትነት ሞቱ፤ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።

በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር። ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር። ይህንን ያየ መኮንን በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ። የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር። ይህን ያየችና የሰማች እናት ቅድስት ኢየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ። ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት። ቅድስት ኢየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው። ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም ‹‹ልጄ ሆይ፥ አንተ ከእንግዲህ አባቴ ነህኃ እኔም ልጅህ ነኝ›› አለችው።

ቅድስት እየሉጣም ለልጇ ‹‹ያች የተወለድክባት ዕለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት›› አለችው። የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውኃው ፍላት ወደያውኑን ቀዘቀዘ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።

ይህን ያየ መኰንን ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው። መኰንኑም በታላቅ ሥቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው፤ አጽናናው ስሙን ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም በረከትን እንደሚያገኝና ሌላ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። ሲነጋ መኰንኑ ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ካለበት አስጠርቶ ‹‹የተመለስከው መመለስ አለን?›› አለው:: ቅዱስ ቂርቆስም ‹‹አይሆንም አልመለስም››  አለው:: ሰይፍ ጃግሬውን ጠርቶ ‹‹ንሳ ውደቅበት›› አለው:: በሰይፍ መታው፤ ጌታም ነፍሱን ከመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮለታል:: ይህም ጥር ፲፭ ቀን ነው፤ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም በማግሥቱ (ጥር ፲፮) በሰይፍ አንገቷ በሰይፍ ተቆርጦ በሰማዕትነት ዐርፋለች::

የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅድስት ኢየሉጣ እና የቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸውና ምልጃቸው አይለየን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ መጽሐፍ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር ወሐምሌ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!