ዐቢይ አገባብ

መምህር በትረማርያም አበባው
ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ‹‹ዘርና ቦዝ አንቀጽ›› በሚል ርእስ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስለ ዐቢይ አገባብ እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

የመልመጃ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ቃላት ዘራቸውን እየለያችሁ አውጡ! በቅንፍ ያለው መነሻ ግሡ ነው።
፩) ርደት (ወረደ)
፪) ተውኔት (ተዋነየ)
፫) ትውፊት (አወፈየ)
፬) ብኵርና (ተበኵረ)
፭) ኵፋሌ (ከፈለ)
፮) ተግሣፅ (ገሠፀ)
፯) ልሳን (ለሰነ)
፰) ላዕሉ (ተልዕለ)
፱) ቴሮጋ (ረግዐ)
፲) ሃይማኖት (ሃይመነ)

የጥያቄዎች መልሶች
፩) ርደት……………ሳቢዘር
፪) ተውኔት………..ምዕላድ
፫) ትውፊት……….ባዕድ ከምዕላድ
፬) ብኲርና…………ጥሬ ምዕላድ
፭) ኵፋሌ………….ጥሬ ዘር
፮) ተግሣፅ……….ባዕድ ዘር
፯) ልሳን………….ዘመድ ዘር
፰) ላዕሉ ………….ጉልት
፱) ቴሮጋ………..ባዕድ ጥሬ
፲) ሃይማኖት……ምዕላድ

ዐቢይ አገባብ

ዐቢይ አገባብ የሚባለው በቀዳማይ አንቀጽ፣ በካልዓይ አንቀጽ፣ በሣልሳይ አንቀጽ እና በነባር አንቀጽ እየገባ አናቅጽን ከማሰሪያነት የሚያስቀር ነው። በአገባብ፣ በአንቀጽ፣ በባለቤት እና በተሳቢ ሊወድቅ ይችላል። ለምሳሌ እስመ በሚለው አገባብ ብንመለከተው በአገባብ ሲወድቅ እስመ በወንጌል ይሜህር ሕገ ጴጥሮስ ይላል። በአንቀጽ ሲወድቅ እስመ ይሜህር ጴጥሮስ በወንጌል ሕገ ይላል። በተሳቢ ሲወድቅ እስመ ሕገ ይሜህር ጴጥሮስ ይላል። በባለቤት ሲወድቅ ደግሞ እስመ ጴጥሮስ ይሜህር ሕገ በወንጌል ይላል። ሁሉም ግን ትርጉሙ ተመሳሳይ ነው። መጨረሻ ፊደላቸው ግእዝ የሆኑ አገባቦች ይነዳሉ እንጂ አይነዱም (‹ነ› ይጥበቅ)።
ለምሳሌ እስመ፣ አምጣነ፣ እንዘ የሚሉ አገባቦች መጨረሻ ፊደሎቻቸው ‹መ፣ነ፣ዘ› ግእዝ ስለሆኑ ይነዳሉ እንጂ አይነዱም ማለት እስመ ሖረ፣ እንዘ የሐውር፣ አምጣነ ይበልዕ ይላል እንጂ ሖረ እስመ፣ የሐውር እንዘ፣ ይበልዕ አምጣነ አይባልም ማለት ነው። መድረሻ ፊደላቸው በካዕብ በሣልስ ያሉ አገባቦች ግን ይነዳሉም፣ ይነዳሉም። ለምሳሌ ባሕቱ፣ አኮኑ፣ ዓዲ የሚሉ አገባቦች መድረሻ ፊደላቸው ‹ቱ፣ኑ፣ዲ› ካዕብ እና ሣልስ ስለሆኑ ባሕቱ ይገብር፣ ይገብር ባሕቱ፣ አኮኑ ይገብር፣ ይገብር አኮኑ፣ ዓዲ ይገብር፣ ይገብር ዓዲ ይላል ማለት ነው። ከፊትም ከኋላም ይመጣሉ ማለት ነው። ከግእዝ ‹ሀ፣ሰ› ከካዕብ ‹ሁ፣ኑ› ከሣልስ ‹ሂ፣ኒ› በተለይ ተነጂ ናቸው። እኒህ ይነዳሉ (‹ነ› ይጥበቅ) እንጂ አይነዱም። ይህም ማለት ገብረኒ፣ ገብረሰ፣ ገብረሂ ይላል እንጂ ኒገብረ፣ሰገብረ፣ሂገብረ አይልም ማለት ነው።
አገባብ በአገባብ ላይ ሊደራረብ ይችላል።

ለምሳሌ ‹‹እስመ እንዘ ይበልዕ መጽአ ሲል እየበላ መጥቷልና›› ተብሎ ይተረጎማል። እስመ እና እንዘ ሁለቱም አገባቦች ስለሆኑ ተደራርበው በተከታታይ እንደመጡ አስተውሉ! ዐበይት አገባባት ሁሉ በምሥጢር አስረጂ ይሆናሉ። አስረጅ የሚሆኑ እስመ፣ አምጣነ እና አኮኑ ብቻ አይደሉም። ዐበይት አገባባት በዘንድ አንቀጽ ላይ አይወድቁም። ከወደቁም በአውታር በጣሽ አማካኝነት ይወድቃሉ። ይህም ማለት እስመ ይብላዕ አይልም። ነገር ግን እስመ እንበለ ይብላዕ መጽአ ቢል ይሆናል ምክንያቱም ‹‹እንበለ›› አውታር በጣሽ ሆኖ አገልግሎታልና ነው። እስመ ይብላዕ ሲል ቢገኝ ግን ጸያፍ ነው። ጸያፍነቱም አውታር ጸያፍ ይባላል። እስመ እንበለ ይብላዕ መጽአ ቢል ሳይበላ መጥቷልና ተብሎ ይተረጎማል። ይህ ጠቅላላ አዋጅ ነው። ከዚህ በኋላ ዐበይት አገባባት በዓረፍተ ነገር ውስጥ እንዴት እንደሚገቡ እንመለከታለን።
ስለ ተብለው የሚተረጎሙ አገባቦች

ስለ የሚሆኑ ዐበይት አገባቦች የሚከተሉት ናቸው። እነዚህም እስመ፣ አምጣነ፣ መጠነ፣ በዘ፣ በቀለ፣ በይነ፣ እንበይነ፣ በእንተ፣ ህየንተ፣ ፍዳ፣ ተውላጠ ናቸው። እያንዳንዳቸው በዓረፍተ ነገር እንዴት እንደሚገቡ ቀጥለን እንመልከት።

፩) በቀለ፦ስለ ተብሎ የሚተረጎም በቀልነትን ሳይለቅ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ወለተ ባቢሎን ኅስርት ብፁዕ ዘይትቤቀለኪ በቀለ ተበቀልክነ›› ይባላል። ትርጉሙም ‹‹አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ ስለተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው›› ማለት ነው። (መዝ.፻፴፮፥፰) ስለዚህ ‹‹በቀለ›› ስለ ሆኖ ለማገልገል በቀልነትን ሳይለቅ ነው ያለው ለዚህ ነው። ‹ዘ› ን በር ከፋች አድርጎም ሳያደርግም ይገባል። ይህም ማለት ለምሳሌ በቀለ ተበቀልክነ ባለው በቀለ ዘተበቀልክነ ይላል ማለት ነው። ትርጉሙ ያው ነው። ሙያ ሲሰጥ ግን ‹ዘ› በር ከፋች ይባላል። በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራል።

፪) በእንተ፣ ህየንተ፣ እንበይነ፣ በይነ ‹ስለ› ተብለው ሲተረጎሙ ፈንታነትን ሳይለቁ ነው። በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራሉ። ሲነገሩም ‹ዘ›ን በር ከፋች ይዘው ነው። ለምሳሌ ‹‹ፈጠረነ አምላክ በይነ ዘአፍቀረነ/ እንበይነ ዘአፍቀረነ›› ይባላል። ትርጉሙም ‹‹አምላክ ስለወደደን ፈጠረን›› ማለት ነው። በእንተ ሲገባ ‹‹በእንተ ዘተወልደ እምኔሃ›› ይባላል። ትርጉሙም ‹‹ከእርሷ ስለተወለደ›› ማለት ነው። ህየንተ ሲገባ ደግሞ ‹‹ህየንተ ዘበላዕነ ሥጋከ›› ይባላል። ትርጉሙም ‹‹ሥጋህን ስለበላን›› ማለት ነው።

፫) ፍዳ፦ ብድራትን ሳይለቅ ‹ዘ›ን በር ከፋች ይዞ በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራል። ለምሳሌ ‹‹ፍዳ ዘብዕለ ነዌ ብዕለ ሥጋ ውስተ ምድር ነድየ ውስተ ሰማይ እምብዕለ ነፍስ›› ይባላል። ‹‹ፍዳ ዘብ ዕለ›› ያለው ‹‹ባዕለ ጸጋ›› ስለሆነ ተብሎ ይተረጎማል።

፬) ተውላጠ፦ ለውጥነትን ሳይለቅ ‹ዘ›ን በር ከፋች ይዞ በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራል። ለምሳሌ ‹‹ተውላጠ ዘገፍዖ ዳዊት ለኦርዮ ተገፍዐ በእደ ወልዱ አቤሴሎም›› ይባላል። ትርጉሙም ‹‹ዳዊት ኦርዮን ስለገፋው በልጁ በአቤሴሎም እጅ ተገፋ›› ማለት ነው። ‹‹ተውላጠ ዘገፍዖ›› ያለው ‹‹ስለ ገፋው›› ተብሎ እንደተተረጎመ አስተውሉ።

፭) እስመ፣ በዘ፣ መጠነ፣ አምጣነ ሲገቡ ‹ዘ›ን በር ከፋች ሳይዙ ይገባሉ። ለምሳሌ ‹‹እስመ በልዐ አዳም በለሰ ተሰቅለ አምላክ›› ይባላል። ትርጉሙ ‹‹አዳም በለስን ስለበላ አምላክ ተሰቀለ›› ማለት ነው። ‹‹ተቀነወ ቴዎድሮስ በ፻ ወ፶ ወ፫ ቅንዋት መጠነ/አምጣነ ተዘከረ ተቀንዎቶ ለእግዚእነ በ፭ቱ ቅንዋት›› ማለት ደግሞ ‹‹ቴዎድሮስ ጌታችን በአምስቱ ችንካር መቸንከሩን ስላሰበ በ፻፶፫ ችንካሮች ተቸነከረ›› ማለት ነው። በዘ ሲገባ ‹‹በዘተሰብአ ተቀብዐ›› ይባላል። በዘተሰብአ ሰው ስለሆነ ተብሎ ይተረጎማል።
የስለ አገባቦች ‹አ› ባለበት አማርኛ ‹ስላ› ይሆናሉ። ይህም ማለት ለምሳሌ ‹ገብረ፤ አደረገ› ማለት ነው። ፍዳ ዘገብረ ሲል ‹ስላደረገ› ተብሎ ይተረጎማል። ‹አእመረ፤ አወቀ› ነው። ፍዳ ዘአእመረ ስንል ‹ስላወቀ› ተብሎ ይተረጎማል ማለታችን ነው።

ና የሚሆኑ አገባቦች
‹ና› የሚሆኑ አገባቦች ‹እስመ፣አምጣነ፣አኮኑ፣ሰ› ናቸው። እነዚህ ሦስቱም በዋዌ እስከ ሦስት ያወርዳሉ። ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ጊዮርጊስ ርኁብ በልዐ ኅብስተ ሃይማኖት እስመ ያፈቅር ግብረ ወንጌል ወይኤዝዝዎ ሥላሴ አጋእዝቲሁ ወይትቀነይ ወይደክም፡፡›› ይህም ሲተረጎም ‹‹የተራበ ጊዮርጊስ ወንጌል ሥራን ይወዳልና፤ ሥላሴ ጌቶቹም ያዝዙታልና፤ ይገዛልምና ይደክማልምና ሃይማኖት እንጀራን በላ›› ማለት ነው።

፩) እስመ፣አምጣነ፦ በዘማች አንቀጽ በነባር አንቀጽ ይዘረዘራሉ። ዘማች አንቀጽ የሚባሉት ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽ፣ ሣልሳይ (ዘንድ) አንቀጽ፣ ትእዛዝ አንቀጽ እና ንዑስ አንቀጽ ያላቸው ከዚያም በላይ ሊዘረዘሩ የሚችሉ ናቸው። ነባር አንቀጽ የሚባሉ ግን በራሳቸው ብቻ የሚገኙ ናቸው። ለምሳሌ ውእቱ፣ ቦ እና የመሳሰሉት ናቸው። እስመ እና አምጣነ በቀዳማይ አንቀጽ፣ በካልዓይ አንቀጽ ይገባሉ። በዘንድ አንቀጽ ሲገቡ ግን አውታር በጣሽ ይዘው ነው። ይህንን ባለፈው ክፍል አይተናል። ይህም ‹‹እስመ እንበለ ይብላዕ መጽአ›› ነው፤ ትርጉሙ ‹‹ሳይበላ መጥቷልና›› ማለት ነው። ‹‹እስመ ሖረ አምጣነ ሖረ ሄዷልና፣ እስመ የሐውር አምጣነ የሐውር ይሄዳልና›› ማለት ነው። ለምሳሌ ‹‹ሐዋርያት መሀሩ ወንጌለ እስመ ይኤዝዞሙ ወልድ፤ ወልድ ያዝዛቸዋልና(አዝዟቸዋልና) ሐዋርያት ወንጌልን አስተማሩ።››

፪) አኮኑ ‹ና› ሲሆን ከግሡ ፊትም ከግሡ በ ኋላም ይመጣል። ለምሳሌ ‹‹አኮኑ መጽአ መጥቷልና፤ መጽአ አኮኑ መጥቷልና›› ይባላል። ‹‹ይመጽእ አኮኑ፣ አኮኑ ይመጽእ ቢልም ይመጣልና›› ማለት ነው።

፫) ሰ ‹ና› ሲሆን በአምስት ግሦች በሣልሳይ አንቀጽ ይነገራል። እነዚህም ግሦች ጸንሐ-ቆየ፣ ተርፈ-ቀረ፣ ተኀድገ-ተተወ፣ ተዘንግዐ-ተዘነጋ፣ ተረሥዐ-ተረሣ ናቸው። በአሉታ ኢተኀለየ፣ ኢተጽሕቀ፣ ኢተዘከረ፣ ኢተሐሰበ፣ ኢያስተሐመመ ናቸው። ከእነዚህ በተረፈ ኮነ-ሆነ፣ ረሰየ-አደረገ የሚሉ ግሦች ይስማሙታል። የኮነ እና የረሰየ ተሳቢዎች ሐሰት፣ ሕሳዌ፣ ሕብል፣ ዛውዕ፣ ተውኔት፣ ሠሐቅ፣ ስላቅ ናቸው። ወ፣ ሂ፣ ኒ፣ ጥቀ ስንኳን ሲሆኑ ለሁለተኛው ማሰሪያ ሰ፣ ስ፣ ና ሲሆን ይቀድምላቸዋል። ማሰሪያዎቻቸው ኢ፣ አልቦ፣ አኮ ናቸው።

ምሳሌ ፩፦ ‹‹ገብረ ሕይወት ኢበልዐ እክለ አምጣነ መልአክ ውእቱ። ይጽናሕሰ/ ይትርፍሰ/ ይትኀደግሰ/ ይዘንጋዕሰ/ ይትረሣዕሰ/ ነገረ ዝንቱ ጥቀ ጥበ እሙ ኢጠበወ/ ጥበ እሙኒ ኢጠበወ/ ጥበ እሙሂ ኢጠበወ/ ወጥበ እሙ ኢጠበወ›› ይባላል፤ ትርጉሙ ‹‹ገብረ ሕይወት መልአክ ነውና እህልን አልበላም። ይህ ነገርስ ይቅርና የእናቱን ጡት እንኳ አልጠባም›› ማለት ነው።

ምሳሌ ፪፦ ‹‹አልቦ ንጹሕ እምኃጢአት እስመ ጌገይዎ መላእክት ለአምላክ ሶበ ለብሰ ሥጋ። ይኩንሰ ይትረሰይሰ ሐሰተ/ ሕሳዌ/ ሕብለ/ ዛውዐ/ ተውኔተ/ ሠሐቀ/ ሥላ ቀ/ ስላተ/ ነገረ ዝንቱ ዮሐንስኒ ተዘከረ ኃጢአቶ›› ይባላል። ትርጉሙ ‹‹ይኩንሰ ሐሰተ ሲል ሐሰት ይሁንና›› ማለት ነው።

ዘንድ የሚሆኑ አገባቦች

ኀበ፣ መንገለ፣ ወእደ፣ ውእደ ዘንድ አጠገብ፣ በኵል ይሆናሉ። በትርፍ አማርኛ ከ፣ ካ ይሆናል። ትርፍ አማርኛ ሲል ለምሳሌ ካፈራ ዘንድ ለማለት መንገለ ፈረየ እንላለን ‹ካ›ን ስላመጣ ነው። በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራሉ።

ምሳሌ፦ ‹‹ኀበ ወረደ ማይ ይቀድሕዎ›› ይባላል። ትርጉሙ ‹‹ውኃ ከወረደ ዘንድ ይቀዱታል›› ማለት ነው። ‹‹ወእደ ገብረ›› ስንል ‹‹ከሠራ ዘንድ›› ማለት ነው። ‹‹መንገለ ፈረየ›› ከተባለ ‹‹ካፈራ ዘንድ›› ይባላል ማለት ነው።
ኀበ፣መንገለ፣ወእደ፣ውእደ ‹ዘንድ› ተብለው ሲተረጎሙ በቀዳማይ አንቀጽ ይነገራሉ። ‹የ› ተብለው ሲተረጎሙ ግን በቀዳማይ እና በካልዓይ አንቀጽ ይነገራሉ። ለምሳሌ ‹‹ወኀበሂ አመሥጥ አልብየ ይባላል። (መዝ.፻፵፩፥፬) ትርጉሙ ‹‹የማመልጥበትም የለም›› ማለት ነው። ‹‹ወእደ ይከውን ከብካብ ይትጋብኡ ሰብእ›› ስንል ደግሞ ‹‹ሠርግ ሲሆን ሰዎች ይሰበሰባሉ›› ማለታችን ነው። በካልዓይም በቀዳማይም አንቀጽ እንደተነገረ አስተውሉ!

የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ!
፩) ጻመወ በእንተ ዘገብረ
[ጻመወ-ደከመ፥ ገብረ-ሠራ]
፪) ሞተ እስመ ወድቀ
[ሞተ-ሞተ፥ ወድቀ-ወደቀ)
፫) ኢተረክበ ኤልያስ በይነ ዘዐርገ
[ ዐርገ-ዐረገ፥ ኢተረክበ-አልተገኘም]

የሚከተሉትን የአማርኛ ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ!
፩) ስላነገሠው ተጸጸተ
[ነስሐ-ተጸጸተ፥ ነግሠ-ነገሠ]
፪) ከእርሷ ስለተወለደ ይወዳታል።
[እምኔሃ-ከእርሷ፥ ተወለደ-ተወልደ፥ አፍቀረ-ወደደ]

የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ!
፩) ኀበ አፍቀረነ ናፍቅሮ
፪) መንገለ ጸለየ ተባረከ
፫) ወእደ ተናገረ ተሰምዐ

የሚከተሉትን የአማርኛ ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ!
፩) እስመ ወለድኪ ለነ ንጉሠ
፪) አኮኑ አጽባዕት እምነ አጽባዕት የዐቢ

ረደኤተ እግዚአብሔር አይለየን!