ውኃ የሌለባቸው ምንጮች

(፪ጴጥ.፪፥፲፯)

ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውኃ ከምንጭ ተገኝቶ እየፈሰሰ የፍጥረትን ጥማት ያረካል፡፡ በውኃ ሰው ሕይወቱን ያለመልማል፤ እንስሳትና አራዊትም እንዲሁ፡፡ ዕፅዋትና አዝርዕትም ያለ ውኃ አይለመልሙም፤ አይበቅሉምም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ የአገባቡ መምህራን በውኃ ምንጭ ተመስለዋል፡፡ ከምንጭ ንጹሕ ውኃ ተገኝቶ ፍጥረትን እንደሚያረሰርስ ከመምህራንም አንደበት በውኃ የሚመስል ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰ የሰው ልጆችን በጽድቅ እንዲኖኑ ያደርጋል፡፡ ምእመናን ውኃ ቃለ እግዚአብሔር ከሚገኝባቸው እውነተኞች መምህራን እግር ሥር ተገኝቶ በመማር ከድርቀት ኃጢአት ወደ ልምላሜ ጽድቅ ይመጣሉ፤የመንፈስ ፍሬንም ያፈራሉ፡፡(ዮሐ.፬፥፲፬፣ኢሳ.፶፭፥፩፣ ዘዳ.፴፪፥፩‐፪፣ሉቃ.፪፥፵፮፣ማቴ.፱፥፴፮-፴፰)

ሐሰተኛ መምህራን ግን ‹‹እግዚአብሔር ልኮናል፤ የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ ዘንድ አለ›› ይላሉ እንጂ ሐዋርያው እንዳስተማረን በቃሉ የሚሸቃቀጡ ናቸው፡፡ የደረቀ ምንጭ ውኃ እንደሚያስገኝ እነዚህም ‹‹መምህራን ነን›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ መልካም ፍሬ አይገኝባቸውም፡፡ (ማቴ.፯፥፲፭-፲፰)

በዐውሎ ነፋስ የተነዱ ደመናዎች

በሊቃውንቱ ትርጓሜ መሠረት በደመና የሚመሰሉት መምህራን ናቸው፡፡ ደመና ከውቅያኖስ ዝናብ ቋጥሮ ወጥቶ እየዞረ፣ እያዘነበ አዝርዕትና ዕፅዋትን ይጠቅማል፡፡ እውነተኞቹ መምህራን ዙረው አስተምረው ያልተመሰለውን መስለው፣ የተሰመሰለውን ተርጉመው ምእመናንን ይጠቅማሉና፡፡ እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያትና መምህራንም (ቢጽ ሐሳውያን መናፈቃንም) ‹‹መምህራን ነን›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ናቸው፡፡ በዐውሎ ነፋስ የተመሰለው ውዳሴ ከንቱ ፍቅረ ነዋይ እንዲሁም የዚህ ዓለም ፍቅር ነው፡፡ ሐሰተኞች መምህራን ለምን በደመና ተመሰሉ? ቢሉ ደመና ዝናብ እየቋጠረ ወጥቶ ካዘነበ በኋላ እንደማይቆም ወዲያው እንዲበተን፥ እነዚህም መንፈሳዊያን ሊሆኑ ሲገባቸው ሥጋውያን፣ ሰማውያን መሆን ሲገባቸው ምድራዊያን ሆነዋልና፡፡ እውነተኞች መምህራን መንፈስ እግዚአብሔር ሲነዳቸው (ሲመራቸው)፥ እነዚህ ደግሞ የሚነዱት በክፋ መንፈስ በዲያብሎስ ነው፡፡

ምንጭ፡- ‹‹ፍኖተ አርሲሳን›› በመምህር ቢትወደድ ወርቁ፤ ሁለተኛ ዕትም፤ ታኅሣሥ ፳፻፲፫ ዓ.ም