‹‹ወአንትሙሰ ተዐቀቡ፤ ወግበሩ ተዝከረ ሕማማቲሁ፤ እናንተስ ተጠበቁ፤ የሕማሙን መታሰቢያ አድርጉ››፤/ትእዛዝ ፴፩/

   በወልደ አማኑኤል

ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችን የምሥጢረ ሕማማቱን ነገር መንፈስ ቅዱስ ሲገልጽለት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማታችንንም ተሸከመ››ማቴ. ፰፥፲፯/ኢሳ ፶፫፥፬/ ሲል ተናገረ፤ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፍቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግስት በመሸከም መከራ መስቀሉ ስለተፈጸመበት፤ እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ተባለ፤ ኢሳ. ፶፫፥፬፡፡

 ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም የነበረው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንዑስ፤ በማዕከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትንና በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ታዲያ ሰሙነ ሕማማትን ጌታችን ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገው ትድግና ቅዱሳን መጻሕፍት በየበኩላቸው ቢዘረዝሩትም ቸርነቱ፤ ርህራሄውና በጠቅላላው በአምላካዊ ጥበቡ የሰራቸው ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ሥራዎች ጸሐፊ፣ አንባቢና ሰሚ ሊደርስባቸውና ዝርዝራቸውን ሊከተላቸው ሲፈልግ፤ ገና በሀሳቡ ውጥን ላይ ድካም እንዲሰማውና ፍጡርነቱ ፈጣሪን እንዳይመረምር ያስገድደዋል፡፡

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በቃሉ ብቻ ዳን በማለት ሊያድነው ሲቻለው የሰውን ባሕርይ ባሕሪዩ አድርጎ በፈቃዱ ሰው የሆነበትን፤ ሰውም ከሆነ በኋላ የተቀበላቸው ልዩ ልዩ መከራ የተቀበለበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሰሙነ ሕማማት በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረጉ ሥርዓቶች በጥቂቱ እንመልከት፡-

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት

ሰሙነ ሕማማትን የምናከብረው አባቶች ሐዋርያት የጌታን ጾም ለብቻው እንድናስበው እንዳደረጉን ሁሉ የጌታ ሕማማትም እንዲሁ በተለየ ለብቻው እንድናስበው የሰሩልን ሥርዓት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሳምንት ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተ ኩነኔ (፶፻፭፻ ዘመን) እና የጌታችን ሕማም መከራ እንግልት የሚታሰቡበት ነው ብለው ያስቡታል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሁለት ነገሮች ምክንያት በማድረግ በሰሙነ ሕማማት  የሚተገበሩ ሥርዓቶች አሉ፤ እነርሱም፡-

ጥቁር ልብስ መልበስ 

በሰሙነ ሕማማት ወቅት በተለይ በዕለተ ዐርብ ካህናቱ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ የኃዘንና የመከራ መገለጫ በመሆኑ በዚህ ወቅትም የጌታን ኃዘን መከራ ለማሰብና ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ባይገኝ ደግሞ የተገኘውን ልብስ ገልብጠው ይለብሱታል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቃጭሉ ተቀይሮ ጸናጽል ይሆናል

በጸሎተ ሐሙስ በቅዳሴው ወቅት ቃጭሉ ተለውጦ ጸናጽል ይሆናል፤ ምክንያቱም በዘመነ ኦሪት የነበሩ አበው ጸሎታቸው ፍጽም ሥርዓት እንዳላሰጣቸው ለማጠይቅ ነው፡፡ ከቃጭል የጸናጽሉ ድምጽ ከርቀት እንደማይሰማ ሁሉ የአበው ጩኸት አናሳ መሆኑን ለማጠየቅ፤ የይሁዳን ግብር ለመግለጥና ይሁዳ ጌታን ለማስያዝ በድብቅ ያደባ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡

እርስ በእርሳችን አንሳሳምም፤ መስቀል አንሳለምም

እርስ በእርሳችን አለመሳሳማችን ይሁዳ በመሳም አሳልፎ መስጠቱን ለማሰብና ለማስረዳት ሲሆን መስቀልን ያለመሳለማችን ምክንያቱ ደግሞ፤ መስቀል በዘመነ ኦሪት የኃጥአን መቅጫ እንጂ የሰላም ምልክት እንዳልነበረ ለማጠየቅ ነው፡፡ መጽሐፍትም በመስቀሉ ስለምን አደረገ እንዲሉ መስቀል አዳኝ የሆነ ጌታ ከተሰቀለ በኋላ መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡

አብዝተን መጾም አለብን

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አብዝተን እንድንጾምና እንድንፀልይ ያዙናል፤ ለምሳሌ በሰሙነ ሕማማት የሚችል በሁለት ቀን ውኃና ጨው ያለበት ምግብ እየተመገበ እንዲጾም ሲያዙን ያልቻለ ግን ፲፫ ሰዓት እየጾመ እየጸለየ ውኃንና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲመገብ አዘዋል፡፡

ለሙታን ፍትሐት አይደረግም

በሰሙነ ሕማማት ወቅት ለሞቱ ሰዎች ፍትሐት አይደረግላቸውም፤ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔን የምናስብበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ የነበሩ ሰዎች ፍትሐት እንደማይደረግላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ተስፋ ላለውና ለአማኝ እንጂ ለማያምን ትንሣኤ ዘለክብር፤ ለማይነሣ ቢሆን ፍትሐት አይደረግለትም፡፡

በወይራ ቅጠል ጥብጠባ ይደረጋል

በዕለተ ዐርብ ሥርዓቱን ከፈጸምን በኋላ ወደ ካህናት አባቶቻችን እየሔድን በወይራ ዝንጣፊ ጥብጠባ ተደርጎልን ቀኖና እንቀበላለን፤ በዚህ ወቅት የምንቀበለው ቀኖና የሰሙነ ሕማማትን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ወይራ ጽኑ በመሆኑ የጌታ መከራ ጽኑ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ሕጽበተ እግር ይደረጋል

በጸሎተ ሐሙስ በካህናት አባቶችን የሚፈጸም እግር የማጠብ ሥርዓት ይፈጸማል፤ በዚህም መነሻ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር እንዳጠበና እርሱን አብነት ስላደረግን ነው፡፡

በዚህ ወቅት በዋነኝነት ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ይነበባል

የሰሙነ ሕማማት ሥርዓተ ጸሎትና አገልግሎት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮት ጋር የተያያዘ ቢሆንም አሁን ያለውን ሥርዓት የያዘ ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጻሕፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ የዋለው ከጌታ ልደት በኋላ በ፲፬ተኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፬፻፹ ዓ.ም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ ዐዜብ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት፤ ቀደም ሲል በግዕዝ ብቻ ታትሞ በነበረው የግብረ ሕማማት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡

የመጽሐፉ ስያሜም ከጥንት ስሙ ጀምሮ ግብረ ሕማማት እንደሚባል በመጽሐፍ ውስጥ በብዙ ክፍል ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከጥንት ፍጥረት ከባሕርይ አባቱ አብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ በረቂቅ ጥበቡ ዓለማትንና ፍጥረታትን ሁሉ በየወገኑ ፈጥሮ እንደባሕርያቸው በቸርነቱ እየመገበና እየጠበቀ ሲገዛ ይኖራል፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ በተለየ አካሉ ዓለምን ከፈጠረበት በሚበልጥ ጥበብ ሰው ሆኖ፤ ሥጋን ለብሶ፤ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፤ አዳምን ከነዘሩ እንደገና በአዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ክብሩና ቦታው እንደመለሰው ያመለክታል፤ ፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፯/ ዕራ.፳፩፥፭/ ኢሳ. ፵፫፥፲፱/፡፡