ወርኃ ግንቦት

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በቀደምት ዘመናት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም ምእመናን ስለ ወርኃ ግንቦት (የግንቦት ወር) የነበራቸው አመለካከት የተሳሳት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ በዚያን ጊዜ ወቅቱ የተረገመ እንደሆነ በማሰብም ማንኛውንም ተግባር አይፈጽሙም ነበር። በዚህ ወቅት ነገሮች ሁሉ መጥፎ የመሆን ዕድል እንዳላቸው በማመን ምንም ዓይነት ምግባር አያከናውኑም፡፡ በርካቶችም የሚሠሩት ቤት ወይም የሚያስገነቡት ሕንፃ ፍጻሜው ጥሩ እንደማይሆንላቸው ያስቡ ነበር፡፡ ትዳር በግንቦት ወር የፈጸሙ ምእመናን ካሉ መጨረሻው እንደማያምር ያምኑም ነበር። ለዚህም አስተሳሰባቸው የሚያነሡት ሁለት ምክንያቶች የተሳሳቱ ናቸው፡፡

፩. በዘመነ ኖኅ ማየ አይኅ መዝነም የጀመረው በወርኃ ግንቦት ስለነበር ይህን ወቅት በእርሱ እንደተረገመች ትታሰባለች፤ አምላካችን እግዚአብሔር አሕዛብን ለማጥፋት ያዘነመው የጥፋት ውኃ ሳያቋርጥ ለዐርባ ቀናት ዘንሟል። በዚያን ጊዜ ኖኅ በታዘዘው መሠረት ወደ ገነባት መርከቡ አስገብቶ ካተረፋቸው ቤተበሶቹና እንስሳት ማለትም ከሚበሉት እንስሳት ውስጥ ከእያንዳንዳቸው ሰባት ሰባት፣ ከማይበሉት ደግሞ ሁለት ሁለት እስኪቀሩ ምድር ምድረ በዳ ሆናለች፡፡ ከዚህ የተነሣ በወርኃ ግንቦት እግዚአብሔር ፍርዱን ያስተላለፈበትና ምድርን ያጸዳበት በመሆኑ የተረገመ ወር ተደርጎ ይታሰብ ነበር።
ሆኖም ግን እውነታው ይህ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሕጉን በመተላለፍ በሚበድሉበት ወቅት ቁጣውን እንዲህ ባለ እና በመሳሰሉት ዓይነት መቅሠፍቶች ይቀጣ የነበረው በተለያዩ ወቅቶች ነው። ለምሳሌ እስራኤላውያን ሲበድሉ በእሳት ረመጥ በበሽታ እና በረኃብ የጨረሳቸው ጊዜ አለ። ነገር ግን እነዚህ ወቅቶች ይለያያሉ እንጂ አልተረጉሙም፡፡

፪. ጻድቁ ኢዮብ የተወለደው በወርኃ ግንቦት እንሆነና እንዲህ በማለት ረግሟት እንደነበር እንዲሁም በዚያ የተነሣ ወሩንም እንደረገመው ምእመናን ያምኑ ነበር። ‹‹ያች የተወለድሁባት ቀን ትጥፋ፤ ያችም ወንድ ልጅ ነው ያሉባት ሌሊት። ያች ቀን ጨለማ ትሁን፤ እግዚአብሔር ከላይ አይመልከታት፤ ብርሃንም አይብራባት። ጨለማና የሞት ጥላ ያግኙአት፤ ጭጋግም ይምጣባት። ያች ቀንም የተረገመች ትሁን፤ ያችም ሌሊት ጨለማ ይምጣባት፤ በዓመቱ ቀኖች መካከል አትኑር፤ በወሮች ቀኖች ውስጥም ገብታ አትቆጠር። ለዚያም ሌሊት ጭንቅ ይሁን፤ እልልታ ወይም ደስታ አይግባባት። ነገር ግን ሌዋታንን ለመግደል የተዘጋጀ ያችን ቀን የሚረግም ይርገማት። የዚያ ሌሊት ኮከቦች ይጨልሙ፤ ሌሊቱም በጨለማ ይኑር፤ ወደ ብርሃንም አይምጣ፤ የንጋት ኮከብም ሲወጣ አይይ፤ የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፤ መከራውንም ከአይኔ አልሠወረምና፡፡›› (ኢዮ.፫፥፫-፲)

በዚህም የተነሣ ሰዎች በዚህ ወር ቤት መሥራትም ሆነ ጋብቻም መፈጸምን አያምኑበትም ነበር። የዚህም ምክንያት የገነቡት ቤት እንደሚፈርስ እንዲሁም ጋብቻውም እንደማይጸና ያምኑ ስለነበር ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች በወርኃ ግንቦት የነበረ እርግማንን በመፍራት ይኖሩ እንደነበረ ሁሉ የሐዲስ ኪዳን ሰዎችም በተለይም በገጠርም ያለው ማኅበረሰብ በዚህ ወር ከላይ ቤት መሥራትንም ሆነ ጋብቻን መፈጸም አይደፍሩም።

በእርግጥ ጻድቁ ኢዮብ የተወለደበትን ዕለት እንደረገመ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል። ነገር ግን እዮብ ያረፈበት ቀን እንጂ ግንቦት ፪ የተወለደባት ቀን አይደለም፡፡ የግንቦት ወርንም ከወራት ሁሉ ተለይቶ ርጉም እንደሆነ ማሰብም ስሕተት ነው። ምክንያቱም እርሱ ወሩን መርገሙን በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ አልተመዘገበም፡፡ ይህ የተሳሳት አመለካከት መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል። ለዚህም የሚረዳን የቅዱሳት መጻሕፍትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ ወርኃ ግንቦትን በሐዲስ ኪዳን ከወሮች ሁሉ በላይ ምን ያህል እንዳከበረው እንመለከት፡-

፩.የወሩን መባቻ በእናቱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ባረከው።

፪.ወርኃ ግንቦትን በእናቱ ልደት ከባረከው በኋላ በስምንተኛው ቀን (ግንቦት ፰) በዕርገቱ ዳግም ባረከው፤ በዚህች ቀን ጥንተ ዕርገቱ ይታሰባልና፡፡

፫.በዐሥረኛው ቀን ማለትም ግንቦት ፲፰ ደግሞ በርደተ መንፈስ ቅዱስ ሆነ። ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ የወረደበት በዓለ ጵራቅሊጦስ ነው፡፡

ወርኃ ግንቦት የተረገመ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው የሚያመለክቱ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት ከላይ በተጠቀሱት መሠረት ማስረጃ ይሆናሉ፡፡ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት ሁለቱ በዚህ ወር የሚገኙ ናቸውና፡፡ በዚህም ወቅት እንደወትሮው ሁሉ ክብረ በዓላቱን በተገቢው መንገድ ለማክበር በንጽሕና ሆነን፣ በበጎ ምግባር ታንጸን፣ በሃይማኖት ጸንተን ለሥጋ ደሙ መብቃት እንጂ በትውፊት ሲነገር በነበረው ማስረጃ በሌለው መረጃ ተሰነካከልን እንደ ቀደሙት ወገኖቻችን ወርኃ ግንቦትን መፍራት ወይም መጥላት አይገባም፡፡