ወርኃ ክረምት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሰኔ ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የዓመቱ ትምህርት ጊዜ ተጠናቆ ፈተና ተፈትናችሁ ጨረሳችሁ አይደል? ውጤት እንዴት ነው? በጥሩ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል እንደተዘዋወራችሁ ተስፋ እናደርጋለን፤ አሁን ደግሞ የክረምት ጊዜ መጥቷል፤ በዚህ የዕረፍት ጊዜያችሁ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርት ልትማሩ ይገባል፤ ቤተ እግዚአብሔር (ቤተ ክርስቲያን) በመምጣት የሃይማኖት እና የሥነ ምግባር ትምህርት በመማር አስተዋይ እና ጥበበኛ ልጆች በመሆን ማደግ ያስፈልጋል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልጅነቱ ለእኛ ምሳሌ ሊሆነን ቤተ መቅደስ በመሄድ ከመምህራን ዘንድ ቀርቦ ይማርና ይጠይቅ ነበር፤ ስለዚህ እኛም ቤተ ክርስቲያን ልንሄድና ልንማር አባቶችንም ልንጠይቅ ይገባል፤ ይህን ካደረግን ከክፉ ተግባር እንለያን፤ ቅንና ታዛዥ ልጆችም ሆነን እናድጋለን! መልካም! ልጆች! ለዛሬ ልናስተምራችሁ የወደድነው ስለ ክረምት ወቅት ነው፡፡

በዓመት ውስጥ ያሉት ዐሥራ ሁለቱ ወራት በአራት ወቅታት ይከፈላሉ፤ ከመስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) እስከ ታኅሣሥ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ያለው ወቅት አንዱ ሲሆን መጸው በመባል ይታወቃል፤ ሁለተኛው ደግሞ ከታኅሣሥ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ጀምሮ እስከ መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት) ያለው ነው፤ ይህ ደግሞ ሐገይ ( በጋ) ይባላል፤ ሦስተኛው ደግሞ ከመጋቢት ፳፮ (ሃያ ስድስት) እስከ ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ያለው ወቅት ነው፤ ይህ ጊዜ ፀደይ ይባላል፤ አራተኛውና ዛሬ በጥቂቱ ልንነግራችሁ ያሰብነው ወቅት ደግሞ ከሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት)  ጀምሮ እስከ መስከረም (ሃያ አምስት) ድረስ የሚቆየውና ‘ክረምት’ በመባል ስለ ሚታወቀው ወቅት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  ከሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ጀምሮ እስከ መስከረም (ሃያ አምስት) ቀን ድረስ  ያለው ወቅት ክረምት ይባላል ፤ ክረምት ማለት ‘ከርመ (ክራማት)’ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ‘ዝናም፣ የዝናም ወራት፣ በጸደይና በመጸው መካከል ያለ ክፍል’ ማለት ነው፡፡ ( አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፭፻፵፰) በዚህም በክረምት ወቅት በበጋው ሠልጥኖ  የነበረ ዋዕይ (ሙቀት) ፈጽሞ ሲጠፋ ተቀብሮ የነበረው ቁር (ቅዝቃዜ ) ወደ ፊት ሲወጣ ከውኃው ብዛትና ከምንጩ ጽናት የተነሣ ምድር ‘እፈርስ እፈርስ፣  እናድ  እናድ’ ትላለች፡፡

ከዚህም በኋላ አምላካችን ደመና ገልጦ ፀሐይ አውጥቶ ምድርን ያረጋታል፤ ያጸናታል፤ ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት በዝማሬው ‹‹…አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም  ክረምትንም አንተ አደረግህ …›› በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር ወቅታትን ያፈራርቃል፤ (መዝ.፸፫፥፲፯)፡፡ በክረምት ወቅት አንዳንዴም ከደመናው ጽናት የተነሣ ቀኑ ጨፍገግ (ጨለም) ብሎም የሚውልበት ጊዜ አለ፤ እንደ በጋው (የፀሐይ) ጊዜ እንደ ልብ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም የሚያዳግትበት ወቅት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…ምድርን ጎበኘኻት፤ አጠጣኻትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ…›› በማለት እንደገለጸው በዚህ ወቅት ገበሬው ምድርን አርሶ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ በምድር ላይ ለዘራው ዘር ፈጣሪያችን ዝናመ ምሕረቱን የሚሰጥበት ወቅት ነው፤ (መዝ.፷፬፥፱) የተዘራው ዘር የሰማይን ጠል (ዝናም) ሲያገኝ በጊዜ ሂደት በእግዚአብሔር ቸርነት ያቆጠቁጣል፤ በመቀጠልም ቅጠል ከዚያም ደግሞ አበባ ያወጣል፤ በመጨረሻም ፍሬን ይሰጣል፡፡

ልጆች! ለምድር ዝናምን የሚሰጥ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ዝናምን  ካልሰጠን ምድር በሰማይ ጠል (ዝናም) ካልረሰረሰች የዘሩባትን አታበቅልም፤ በመሆኑም ዝናም እንዲዘንም ግን በጸሎት ፈጣሪን መለመን ያስፈልጋል፤ ‹‹…እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፤ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር፤ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቆጠረውን ተአምራት ያደርጋል፤ በምድር ላይም ዝናብን ይሰጣል፤ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል..›› እንዲል፤(ኢዮ.፭፥፰-፲) አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር በእርሻ ውኃን ይልካል፤ ያሳድጋቸውማል፡፡ አትክልትና አዝርዕት ውኃን ካላገኙ ይጠወልጋሉ፤ ይረግፋሉ፤ ልምላሜም አይታይባቸውም፤ ይህ እንዳይሆን አምላካችን እግዚአብሔር ዝናቡን ይሰጠናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በክረምት ወቅት እንደ በጋው ጊዜ ፀሐይን አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በሰማይ ላይ አናያትም፤ ሰማዩ በደመና ይሸፈናል፤‹‹…ሰማዩን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም….›› በማለት ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ (መዝ.፻፵፯፥፰)

በዚህ ወቅት ዝናም በብዛት ስለሚዘንብ ምድር ከመረስረስም አልፋ መልሳ ውኃን ታመነጫለች፤ ከዚህም የተነሣ ቁር (ቅዝቃዜ) ይሆናል፤ በምድራችን ያሉ ዕፅዋቱ ለምልመው ይታያሉ፤ይህ ሁሉ የፈጣሪ ችሮታ (ስጦታ) ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ክረምት ወቅት ለተማሪዎችም የዕረፍት ጊዜ እንደመሆኑ ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ልንማር ይገባናል፤ ይህን ጊዜ በከንቱ በጨዋታ ብቻ ማሳለፍ የለብንም፤ በዘመናዊ ትምህርታችን ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን መዘጋጀትም ያስፈልጋል፤ ልጆች! ስለ ክረምት በጥቂቱ ነገርናችሁ፤ ወቅትን ጠብቆ ዝናብን የሚሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን! ዝናቡን ዝናመ ምሕረት ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን አሜን! ቸር ይግጠመን! መልካም የክረምት ወቅት ይሁንላችሁ!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!