‹‹ክርስቶስን የምታስመስለን የከበረች ጥምቀት›› ቅዳሴ አትናቴዎስ

እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሰን!

 ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ጥር፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በአዳምና በሔዋን በደል ምክንያት ልጅነታችንን በማጣታችን፣ ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልሰው እግዚአብሔር ወልድ ከሰማያት ወርዶ፣ ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ድኅነትን ሊፈጽም ከጀመረባቸው አንዱ እና ዋነኛው የክርስትናችን መግቢያ በር ጥምቀት ነው፡፡

ጥምቀት ክርስቲያን የሚለውን ታላቅና ክቡር ስም እንዲሰጠን፣ ከእግዚአብሔር ልጅ የመባልን ክብር በማግኘት፣ መንሳፈዊ ተግባራትን በመፈጸም ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት የመንግሥቱን ክብር ለመውረስ ጉዞ የምንጀምርበት ነው፤ ልጅነት እንዲሁ የሚገኝ ሳይሆን በስሙ ስናምንና ስንጠመቅ የሚሰጠን ክቡር ታላቅ፣ ሥልጣን ነው፡፡ ‹‹በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፩፥፲፪)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኦሪቱ ምሁር ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› በማለት በአማናዊ ቃሉ እንደነገረው የልጅነትን ክብር ዳግመኛ አግኝተን ልጆች ተብለን መንግሥቱን ለመውረስ መጠመቅ ግድ ይለናል፤ (ዮሐ. ፫፥፭) አለበለዚያ ግን ‹‹ባሪያም ለዘለዓለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘለዓለም ይኖራል›› እንደተባለው ነው፡፡      (ዮሐ.፰፥፴፭) ልጆች ሳንሆን መንግሥትን መውረስ አይቻልምና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግመኛ ከቅድስት ሥላሴ ልንወለድ ይገባናል፡፡

ሥርዓተ ጥምቀትን የሠራልን፣ እንፈጽመውም ዘንድ ያዘዘን እርሱ አምላካችን ነው፡፡ በምድራዊ ሕይወታችን በአምልኮ ሥርዓት ያሉ በጎ ምግባራትን (መንፈሳዊ አገልግሎትን) እንፈጽማቸው ዘንድ ሲያዘን አብነት ይሆነን ዘንድ ከአንደበቱ ትምህርት በተጓዳኝ በተግባር ከውኖ አሳይቶናል፡፡ ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ›› ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፮)

ጥምቀት መንፈሳዊ ልደትን እና የልጅነት ሥልጣን የምናገኝበት ነው፡፡ ጥምቀት ወደ መንግሥተ ሰማያት መግቢያ በራችን ነው፤ ጌታችን ግን መጠመቁ እንደ እኛ ልጅነትን አልያም ክብርን ሽቶ ሳይሆን ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው የጉባኤ ኒቅያ አፈ ጉባኤ አባ እለ እስክንድሮስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ባስተማረበት ትምህርቱ ጌታችን የመጠመቁን ምክንያት እንዲህ ገልጦልናል፤ ‹‹እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምን አተጋው፤ በጨርቅ ይጠቀለል ዘንድ በበረት ይጣል ዘንድ ከድንግል ጡትን ይጠባ ዘንድ በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው…፤ በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን ያድነን ዘንድ ለእኛ ብሎ አይደለምን፤›› የጌታችን መጠመቁ ለእኛ አብነት ነውና፡፡ (ሃይማኖተ አበው ፲፮፥፪)

የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው አባ ሳዊሮስም ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ባስተማረበት ትምህርት ስለ ጌታችን የመጠመቅ ምሥጢር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹በዮርዳኖስ ውኃም በተጠመቀ ጊዜ ይህ ምሥጢር ዳግመኛ ተገለጠ፤ ጥምቀትንም ሽቶ አይደለም፤ ሽቶ አልተጠመቀም፤ አምላክ በሥጋ ተገልጦ ዳግም ልደትን ይሰጠን ዘንድ ነው እንጂ፤ እርሱስ ከእኛ ከሰዎች ዘንድ የሚሻው ነገር የለም፡፡›› (ሃይማኖተ አበው ቅዱስ ሳዊሮስ ፹፯፥፲፭)

የጌታችን በመጠመቁ በበደላችን ምክንያት በትእዛዝ ተጽፎብን ጠላት ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ደብቆት የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ደምስሶልናል፤ ‹‹በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡›› (ቆላ.፪፥፲፬)

ቅዳሴ አትናቴዎስ እንደተናገረው ‹‹ክርስቶስን የምታስመስለን የከበረች ጥምቀት›› ጌታችን ለእኛ አብነት ሆኖ የተጠመቀበትን በመሆኑ ይህችን ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ ይህ ዕለት የጠላት ዲያብሎስ ሴራ የከሸፈበት፣ የዕዳ ጽሕፈት የተደመሰሰበት፣ የአንድነት ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ነው፡፡ ውለታውን እንዘክርበታለን፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በመነሣት፣ ጌታችንን አብነት በማድረግ እና ወደ ጥምቀተ ባሕር በመሄድ ይባርካሉ፤ ምድሪቷም በዚህ ዕለት ተቀድሳ ትውላለች፤ ታድራለች፡፡ በዚህች ዕለት ጠላት ዲያብሎስ ይንቀጠቀጣል፤ የግብር ልጆቹ ይሸበራሉ፡፡ በዚህች ዕለት ክርስቲያኖች ደስታን ለብሰው፣ ደስታን ተጫምተው፣ የደስታን  ዘውድ ደፍተው የደስታ ምስጋናን ያቀርቡባታል፡፡

ምሥጢረ ጥምቀት ለእኛ አምነን ለተጠመቅን ክርስቲያኖች አዲስ ሕይወትን የሚያጎናጽፈን፣ ድኅነትን የምናገኝበት ነው፤ መጠመቃችን ዳግመኛ ልጆች እንሆን ዘንድ ነው፤ መጠመቃችን የቤተ ክርስቲያን አባል ሆነን በውስጧ ካለው ጸጋ ተካፋይ ለመሆን ነው፤ መጠመቃችን በልተን ከማንራበው፣ ጠጥተን ከማንጠማው፣ የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጠንን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ ክቡር ደም እንቀበል ዘንድ የሚያስችለንን ክብር የሚያጎናጽፈን ነው፡፡ ካልተጠመቅንና ልጆች ካልተባልን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም አይቻለንምና፡፡

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀትን ሥርዓት በአዲስ ኪዳን ሳይመሠርትልን በፊት በብሉይ ኪዳን በብዙ ምሳሌ ሲመስል ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ልጆች መለያ ምልክታችን ጥምቀት እንደ ሆነ፣ በብሉይ ኪዳን ሕዝበ እግዚአብሔር ለመሰኘት መለያው ግዝረት ነበር፤ ይህ ሥርዓተ ግዝረት በእግዚአብሔርና በወዳጁ በአብርሃም መካከል የነበረ ቃል ኪዳን ከእርሱ የሚወለዱት ሁሉ እንዲፈጽሙት ታዞ ነበር፤ ‹‹በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከአንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡›› እንዲል፤ (ዘፍ.፲፯፥፲)

በብሉይ ኪዳን ትንቢት እያናገረና በምሳሌ ሲናገር የነበረውን በአዲስ ኪዳን መሥርቶ፣ ፈጽሞና አማናዊ አድርጎ ሰጠን፤ አዳምና ሔዋን ሕግ አፍርሰው፣ በለሰ ቆርጠው ፍሬዋን በበሉ ጊዜ በዕዳ ተያዝን፣ ከሕይወት ወደ ሞት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ፣ ከልጅነት ወደ ባርነት ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ ፈለስን፤ (ተሰደድን) ‹‹በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበርሁ፡፡›› (ኤፌ.፪፥፩) ከመጣብን ከቀደመ በደላችን በጌታችን መወለድ፣ መጠመቅ፣ በቅዱስ መስቀል ላይ መሰቀል ነጻ ሆነናል፤ የክብሩን መንግሥት እንወርስ ዘንድ ግን በዕለተ ዓርብ ሌንጊኖስ በጦር ከወጋው ጎኑ ከፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ልጆች ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ጌታችን ከማረጉ በፊት ለቅዱሳን ሐዋርያት ካዘዛቸው ዐቢይ ተልእኮ መካከል ሰዎችን አስተምረው፣ የምሥራቹን ወንጌል ሰብከው፣ ከጣዖት አምልኮ ከለዩ በኋላ የልጅነት ጸጋን አማንያን ያገኙ ዘንድ እንዲያጠምቋቸው ነው፤ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንዲህ በማለት አዝዟቸዋልና፤ ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡›› (ማቴ.፳፰፥፲፱)

አበው ቅዱሳን ሐዋርያት በተሰጣቸው ሥልጣን፣ በተቀበሉት አደራ እያስተማሩ የምሥራቹን ሰምተው ያመኑትን እያጠመቁ ልጅነትን አሰጥተዋል፤ ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ›› እንዲል፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፪፥፵፩) ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን በተወለዱ በአርባ እና በሰማንያ ቀናቸው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደው የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የመንግሥተ ሰማያት ዜጋ አድርጋ ክርስቲያን የሚለውን ክቡርና ታላቅ ስምን ትሰጣቸዋለች፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!