ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር  

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

የካቲት ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? መቼም ከመጀመሪያው የዓመቱ አጋማሽ ትምህርት ውጤታችሁ በመነሣት የበለጠ ጎበዝ ለመሆን እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን! “ብልህ ልጅ ከስሕተቱ ይማራል” እንዲሉ አበው ከትናንት ድክመታችሁ በመማር የበለጠ ውጤታማ ተማሪ ለመሆን መሥራት ይገባል፡፡ ወላጆቻችን እኛን ለማስተማር ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍሉ አስተውሉ! ልጆች የእነርሱ ድካም እኛ መልካምና ጎበዝ እንድንሆን ነውና በርቱ! ለዛሬ የምንማማረው ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ነው፤ መልካም ቆይታ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ምግባር ማለት “ሥራ” ማለት ነው፤ “ሥነ ምግባር” ስንል ደግሞ “መልካም የሆነ፣ በሁሉ የተወደደ፣ በረከትን የሚያሰጥ፣ የሚፈቀድ ሥራ” ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ እኛ መልካም ሥነ ምግባር ያለው ልጆች ሆነን ማደግ አለብን፤ አምላካችን እግዚአብሔር እንድንፈጽማቸው ያዘዘን መልካም ምግባራት መተግበር ያስፈልጋል፤  አባትና እናትን እንዲሁም መምህራኖችና ታላላቆቻችንን ማክበር፣ መታዘዝ፣ ድሆችን ማብላት፣ ማጠጣት፣ ማልበስና  ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይገባል፤ ታዲያ እነዚህን ተግባራት ስንፈጽም ሕይወታችን መልካም ይሆናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በክርስትና እምነት ስንኖር ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን እኛም ለሰዎች ሁሉ መልካም ነገርን በማድረግ ክርስትናችንን መግለጥ አለብን፡፡ በሠፈር ውስጥም ሆነ በትምህርት ቤት ለሚመለከቱን ሁሉ የመልካም ምግባር አርአያ (ምሳሌ) መሆን ይገባናል፡፡ በዓላትን ማክበራችን ከበዓሉ በረከትን በማግኘት የተሰጠንን ሰላም በማሰብ የሰላም ሰዎች መሆን፣ የተደረገለንን ፍቅር በማሰብ ሰዎችን መውደድ፣ ለሰዎች መልካምን አድራጊ መሆን አለብን፡፡ ለሰዎች መልካምን አድራጊነት ምን ያህል ታላቅነት እንደሆነ ለዛሬ እንመልከት!

መልካም ማለት “በጎ፣ ጥሩ፣ ቅን” ማለት ነው፤ ቃሉ ብዙ ነገሮችን ያመለክተናል፡፡ ልጆች! እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ! እኛ መልካም ልጆች ነን? በቤት ውስጥ ከወንድማችን፣ ከእኅታችን ጋር ከዚያም ደግሞ በሠፈር ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር፣  ደግሞም በትምህርት ቤት ካሉ ጓደኞቻችንን ጋር ባለን ግንኙነት መልካሞች ነን? ለሰዎችስ ጥሩ ነገርን እናስባለን?

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! በነገሮች ሁሉ ለሰው ቅን ማሰብ መልካምነት ነው፤ ሰዎችን በምንችለው አቅም መርዳት መልካምነት ነው፤ ለምሳሌ ልጆች! እኛ ጎበዝ በሆንበት የትምህርት ዓይነት ቶሎ የማይረዳቸውን ሰዎች ዕውቀታችንን በማካፈል ማስረዳት፣ ፈተና ላይ ከምናስኮርጃቸው ዕውቀቱን እንዲይዙት፣ ራሳቸው እንዲሠሩት፣ ያወቅነውን ማሳወቅ ይህ መልካምነት ነው፤ በቤት ውስጥ ለወላጆችን አቅማችን የሚፈቅደውን ሥራ መሥራት (ማገዝ) መልካምነት ነው፤ ለምሳሌ ይህንን ጠቀስንላችሁ እንጂ የመልካምነት መገለጫው ብዙ ነው፡፡

ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሩት የምትባል መልካም ሴት ነበረች፤ ታሪኳ ሰፊና ብዙ ቁም ነገርን አስተማሪ ነው፤ እኛ ግን ስለ መልካምነቷ ጥቂቱን ብቻ እናውጋችሁ፤ ኑኃሚን የምትባል በጣም ያዘነች፣ ልጆቿ እና ባለቤቷ የሞቱባት ሴት ነበረች፤ ታዲያ በዚህ በጣም አዝና በነበረ ጊዜ ሩት ደግሞ ከአጠገቧ ሳትለያት ትረዳት ነበር፤ ምንም ምላሽ (ዋጋ) ሳትፈልግ እንዲሁ በመልካምነት ታገለግላት ነበር፤ ያዘነችውን ኑኃሚንን አጠገቧ በመሆን ስታገለግላት ደስተኛ አደረገቻት፤ ታማኝ በመሆን በችግሯ ጊዜ ከጎኗ በመሆን መልካምነቷን አስመሰከረች፤ በዚህም የተነሣ ግርማ ሞገስን አገኘች፤ እግዚአብሔርም ባረካት፤ በዚህ መልካምነቷ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ ..›› ብሎ ቡዔዝ የተባለ ሰው መረቃት፡፡ (መጽሐፈ ሩት ፪፥፲፪)

ልጆች! ለሰዎች መልካም ስናደርግ እገዚአብሔር ደግሞ ለእኛ መልካም የሚያደርገውን ሰው ያዝልናል፤ ሩት ለኑኃሚን መልካም ሰው ስለሆነች ለእርሷም መልካም የሆነውን ቡዔዝ ተባለውን ደግ ሰው አዘዘላት፤ እንግዲህ የመልካምነት መገለጫው ለሰዎች በምናደርገው እገዛ እንደሚገለጥ በዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ በጓደኞቻችን ላይ የማይገባ ነገር ባለማድረግ፣ ሰዎችን ሳንንቅ በአቅማችን፣ ባለን ነገር እያገዝናቸው፣ የደከሙትን ማበርታት፣ ተስፋ እንዲኖራቸው፣ ጎበዞች እንዲሆኑ በማበረታታት መርዳት መልካምነት ነው፡፡

ታዲያ ልጆች! ይህን ማድረግ የሚቻለን ቅድሚያ እኛ ጎበዞችና ታታሪዎች ስንሆን ነውና ራሳችንም መበርታት አለብን! መምህራን፣ ወላጆቻችንና ታላላቆቻችን የሚነግሩንን ምክር በመስማትና ተግባራዊ በማድረግ መልካም ልጆች እንሁን! ልጆች መልካምነት ከራስ ይጀምራል፤ እንደ አቅማችን በመጾም፣ በመጸለይ፣ እግዚአብሔር እንዲባርከን መልካም ልጆች እንሁን!  በቀጣይ የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን የቀሩትን ክርስቲያናዊ ምግባራትን እንማማራለን፡፡

ለዛሬ ይቆየን! ቸር ይግጠመን!

አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ማስተዋልን ያድለን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!