ክረምት

ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ” መዝ.73÷17 “በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ” መዝ.71÷17

እግዚአብሔር የዓለምን ምግብ ሥጋዊውንም መንፈሳዊውንም በአራት ከፍሎታል ሥጋዊውን በአራቱ ክፍላተ ዘመን መንፈሳዊውን በአራቱ ወንጌላዊያን ትምህርት፡፡ የሰው ሥጋዊ ምግብና ከአራቱ ክፍላተ ዘመን እንዳይወጣ መንፈሳዊ ምግብናውም ከአራቱ ወንጌላውያን አይወጣም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካችን የሥጋም የነፍስም ፈጣሪ፣ መጋቢ ነውና፡፡ አሁን ያለንበት ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ የሆነው ክረምት ነው፡፡ከዚህም የምናገኘው ሥጋዊ ምግብ ብቻ ሳይሆን ከሥጋዊ ምግብ ያለፈ መንፈሳዊ ምግብም አለ፡፡

 

ክረምት ምንድነው?

ክረምት ማለት ከርመ ከረመ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መክረም የዓመት መፈጸም፣  ማለቅ መጠናቀቅ ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በፀሐይ አማካኝነት የደረቁ ኮረብቶች ተራሮች በዝናም አማካኝነት ውኃ የሚያገኙበት በዚህም ምክንያት በልምላሜ የሚሸፈኑበት፣ የደረቁ ወንዞች ጉድጓዶች ውኃ የሚሞሉበት፣ በፀሐይ የተቃጠለች ምድር ከሰማይ በሚወርድ ጠለል በረከት የምትረካበት፣ በውኃ ጥም የተሰነጣጠቁ የምድር ጉረሮዎች ውኃን የሚጠግቡበት፣ ሰማይ  በደመና የተራሮች ራስ በጉም  የሚጎናጸፉበት በሙቀት ፋንታ ቅዝቃዜ በድርቅ ፈንታም ልምላሜ የሚነግስበት ተሰባብሮ የወደቀ ሐረግ ቀና ብሎ ከየቦታው የሚሳብበት ወቅት  ነው፡፡

 

ክረምት

1.    ወርኃ ማይነው /የውኃ ወር፣ ወቅት ነው/ ውኃ ደግሞ እግዚአብሔር ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው ከሥጋዊ ምግብና ስንነሣ ያለ ውኃ ለምግብነት የሚውል ነገር በዓለማችን ውስጥ የለም ምድር የዘሩባትን እንድታበቅል የተከሉባትን እንድታጸድቅ ያጸደቀችውን ተክልም ለፍሬ እንድታበቃ ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህምበኋላ ያለ ውኃ ምግብ መሆን የሚችል የለም፡፡ እሚቦካው በውኃ የሚጋገረውም በውኃ ወጥ የሚሠራው የሚበላው የሚወራረደውም በውኃ ነው፡፡ የውኃን ጥቅም አበው በምሳሌ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፡-  ከ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ቁሳቁሱ በውኃ ይታጠባል፤ ከቆሻሻ ይለያል የሚሠራው ቤትም ቢሆን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ፣ ሲሚንቶው፣ ብረቱ፣ ቢኖር ያለውኃ ሊሠራ አይችልም፡፡ በባሕር ውስጥ ለሚኖሩ ዓሣ አንበሪ፣ አዞ፣ ጉማሬ፣ምግብ ለሚሆኑትም ለማይሆኑትም ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ ውኃ ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም ከፍጡራን በተለየ ውኃ ለሰው ልጅ ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ከሚጠቀምባቸው ፍጡራን ያለ ውኃ ምግብ ሊሰጥ የሚችል የለምና፡፡ እንስሳት ውኃ ይፈልጋሉ ምድርም ውኃ ትፈልጋለች አትክልት፣ እፅዋት ውኃ ይፈልጋሉና ጠቅላላውን የፍጡራን ሕይወት የውኃ ጥገኛ ነው፡፡

 

ከዚህ አንፃር ከዓለማችን ብዙውን ቦታ የሚሸፍነው ውኃ መሆኑን ሥነፍጥረትም ሳይንስም ይስማሙበታል፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ካለፍጡር የማያስፈልገው የለምና ከዚህም በተጨማሪ እቤታችን ውስጥ የሚሠሩ እቃዎች የሸክላም ይሁኑ የብረት በውኃ የተሠሩ ናቸው ከዚህ አለፍ ብለን ስንመለከት በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረ የሰው ልጅ ከተፈጠረባቸው አራት ባሕርያት አንዱ ውኃ ነው፡፡ በመሬትነት ባሕርዩ እየፈረሰና እየተቆረሰ ዓለምን እንዳያጠፋ በውኃነት ባሕርዩ አንድነቱ ጸንቶለት ይኖራል በእሳትነት ባሕርዩ ዓለምን እንዳያቃጥል በውኃነት ባሕርዩ እየቀዘቀዘ ይኖራል፡፡ ሰው ከእናቱ ተወልዶ  የእናቱን ጡት ጠብቶ እንዲያድግ ሰውም ከውኃ፣ ከእሳት፣ ከነፋስና ከመሬት ተፈጥሮ እነዚሁ የተገኘባቸውን ተመግቦ የሚኖር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአራቱ ባሕርያት አስታራቂ ሽማግሌ ውኃ ነው፡፡ጠበኞች የሆኑ ነፋስና መሬት በውኃ ይታረቃሉ ነፋስ መሬትን ይጠርገዋል፡፡ መሬትም ነፋስን ይገድበዋል፡፡ዝናም በዘነመ ጊዜ ትቢያው የመሬት ላይኛው ክፍል በውኃ አማካኝነት ከታችኛው ክፍል ጋር አንድ ይሆናል በነፋስ መጠረጉም ይቀርለታል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ስለ ውኃ የእግዚአብሔር መሣሪያነት እናያለን፡፡

በኃጢአት የተበላሸው የቆሸሸው ዓለም የተቀጣው በውኃ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሠክረው እውነት ነው፡፡ ዘፍ.6÷1፣ 7÷1፣ 8÷1 እስከ ፍጻሜያቸው ማንበብ ለዚህ በቂ መልስ እናገኝበታለን፡፡ ኤልያስ አምልኮ እግዚአብሔር በአምልኮተ ጣዖት ተክተው ሃይማኖተ ኦሪትንት ተው የጣዖት ውሽማ አበጅተው ያስቸገሩትን አክአብና ኤልዛቤልን እንዲሁም መሰሎቻቸውን የቀጣው ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር እንዳይሰጥ ሰማይ ለጉሞ ዝናም አቁሞ ነው፡፡ በአንጻሩ በረድና እሳት አዝንሞ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡

 

“ኤልያስ ዘከማነ ሰብዕ ውእቱ ወጸሎ ተጸለየ ከመ ኢይዝንም ዝናም ወኢዘንመ ዝናም ሠለስተ ዓመተ ወስድስተ አውርሀ ወካዕበ ጸለየ ከመይዝንም ዝናም ወወሀበ ሰማይ ዝናሞ ወምድርኒ አብቆለት ፍሬሃ” ያዕ.5÷17 ኤልያስ እንደኛ የሆነ ሰው ነበር ዝናም እንዳይዘንም አጥብቆ ጸለየ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም አልዘነበም ሁለተኛም ጸለየ ሠማዩም ዝናብን ሰጠ ምድር ፍሬዋን አበቀለች፡፡ በማለት የሰው ልጆች ሕገ እግዚአብሔርን ሲጥሉ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ሲያፈርሱ ከሕጉ ሲወጡ ከአምልኮቱ ሲያፈነግጡ ውሃ መቅጫ መሳሪያ በመሆኑም ይታወቃል ውኃ እስከ አሁን የተመለከትነው በሥጋዊ ምግብነቱ ያለውን ነው፡፡

 

ከዚህ ውጪ መንፈሳዊ ምግብናውስ ብንል፡፡ አሁን ካየነው የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡”

ደገኛዋ የሰው ልጆች ጥምቀት በውኃ መሆኑ የውኃን ጥቅም የጎላ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ይኸውም እንደምናውቀው የጥምቀታችን መሥራች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ ተጠምቆ የአባቶቻችንና በኛ ላይ የነበረው የእዳ ደብዳቤ ያጠፋልን በውኃ በመጠመቁ ነበር ማቴ.3÷13 ከዚህ በኋላ “ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ዮሐ.3÷5 ብሎ ውኃ ከሥጋዊ ምግብናው ያለፈ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ምሥጢር መፈጸሚያ መሆኑን ይነግረናል፡፡ በሌላ መልኩ ጌታችንን የእኛን ሥጋ ለብሶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ ባስተማረበት ጊዜ እንጀራ ለመነ ሳይሆን ውኃ ለመነ የሚል ነው የተጻፈለት፡፡ “ኢየሱስም ውኃ አጠጭኝ አላት” ዮሐ. 4÷7 አሁን ከዚህ የምንመለከተው እስራኤል 40 ዓመት ውኃ ከጭንጫ ያጠጣ አምላክ ውኃ አጥቶ ይመስላችኋል ውኃ ትልቅ ምሥጢር የሚፈጸምበት መሆኑ ለመግለጽ ነው እንጂ ይኸውም ሊታወቅ “የእግዚአብሔር ስጦታ ውኃ አጠጭኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበር እንጂ የሕይወት ውኃም ይሰጥሽ ነበር” ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም ብሎ አስተምሮአል፡፡” ያውም ውኃ የተባለው ትምህርት ልጅነት በሌላ መልኩ እራሱ መሆኑንም ነው የሚያስረዳን በመስቀል ላይ እያለም ከተናገራቸው 7ቱ የመስቀል ንግግሮች አንዱ “ተጠማሁ የሚል ነበር፡፡ ዮሐ.19÷29 ይኸ ከሥጋ መጠማት ያለፈ የእኛን የነፍሳችን ጥማት እንደአጠፋልን የምንማርበት ነው፡፡ እኛን የሕይወት ውኃ ያጠጣን ዘንድ ተጠማሁ አለም፤ ከዚህም የተነሣ ቀደም ሲል በነቢዩ ኢሳኢያስ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ” ኢሳ.55÷1 ብሎ በዓለም ላሉ ፍጡራን ውኃ አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ በተለይ ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል፡፡

 

የተጠማ ይምጣ ይጠጣ የሚለው ብዙ ምሥጢር ያለው ነው ጌታችን የአይሁድ በአል በሚከበርበት ቦታ ተገኝቶ ቀደም ሲል በኢሳይያስ የተነገረውን ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረ መሆኑን ገልጾአል፡፡ “ኢየሱስም ቆሞ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ” ይኸን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስለአላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፡፡  ዮሐ.7÷37-39 ስለዚህ ውኃ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆኖአል ውኃ ከቆሻሻ ከእድፍ እንዲያነጻ መንፈስ ቅዱስም ከኀጢአት ከርኲሰት ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከበደል ሰውን ያነጻልና፡፡ ከክረምት አንደኛው ክፍል ወርኃ ማይ የውኃ ወቅት ይባላል፡፡

 

2.    ክረምት ወርኃ ዘር ነው፡፡ የዘር ወቅት ወይም ጊዜ ነው፡፡ ገበሬው በበጋ ያረሰውን የከሰከሰውን ደረቅ መሬት በዝናብ ወቅት አለስልሶ አዘጋጅቶ ከጎታው ወይም ከጎተራው ያስቀመጠውን ዘር ባዘጋጀው መሬት ላይ አውጥቶ የሚዘራበት መሬቱ ያብቅል አያብቅል ፍሬ ይስጥ አይስጥ ሳያውቅ እግዚአብሔር በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ይመግበኛል ብሎ በማመን ያለምንም ጥርጥር የጎታውን እህል ለመሬት አደራ የሚሰጥበት ከላይ ዝናሙን ከታች ጭቃውን ታግሶ በሬዎችን እየነዳ በትከሻው ላይ ዘርና ቀምበር ተሸክሞ ዘር ለመዝራት ይሰማራል፡፡

 

የገበሬውን ሁኔታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡ “ናሁ ወጽአ ዘራኢ ከመ ይዝራዕ ዘርዖ” ዘሪ ሊዘራ ወጣ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር ከመንገድ ዳር ወደቀ በጭንጫ ላይ የወደቀ ዘር አለ በሾህ መካከል የወደቀ ዘርም አለ በመልካም መሬት ላይም የወደቀ ዘር አለ፡፡ መቶ ስልሳ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ” ማቴ.13÷1 ብሎ ራሱን በገበሬ ቃሉን በዘር የሰማዕያን ልቡና በመንገድ፣ በዐለት፣ በእሾህ፣ በለሰለሰ መሬት መስሎ አስተምሯል፡፡ በመንገድ የተመሰለው ሰምተው የማያስተውሉ ሰዎች ልቡና ነው የሰማይ ወፎች የተባሉ ደግሞ አጋንንት ናቸው፡፡ “ኢትህሚ ሰብአ በቤትከ እስመ ዖፈ ሰማይ ያወጽዖ ለነገርከ” መክ.10÷20

 

በቤትህ ውስጥ ንጉሥ አትስደብ የሰማይ ወፍ/ዲያብሎስ/ ቃሉን ነገሩን ይወስደዋልና” እንዲል በዐለት የተመሰሉት ፈጥነው የሚሰሙ ግን ተግባር ላይ የሌሉ በእሾህ የተመሰሉትም የዚህ ዓለም ሀሳብ ምድራዊ ብልጽግና ፍቅረ ዓለም አስሮ የያዛቸው ሰዎች ሲሆኑ በመልካም መሬት የተመሰሉት ቃሉን ሰምተው የጽድቅ ሥራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በወርኃ ዘር የምንማረው ትልቁ ትምህርት ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ነው፡፡ በወርኃ ማይ ምሥጢረ ጥምቀትን እንደተማርን ገበሬው በጎታው ያከማቸውን እህል ከአፈር ጋር አንድ እንደሚያደርገው ማለት በአፈር ላይ እንደሚዘራው የሰው ዘርም እንዲሁ ውሎ ውሎ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንዲሉ ሲሞት በመቃብር ከአፈር ጋር አንድ ይሆናል ይፈርሳል ይበሰብሳል ወደ አፈርነቱ ይመለሳል፡፡ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና ወደ አፈርነትህም ትመለሳለህና” እንዳለ ዘፍ.3÷19 የተዘራው ዘር በዝናቡና በተዘራበት አፈር አማካኝነት ይፈርሳል ይበቅላል ይለመልማል፣ ያብባል ፣ ፍሬ ይሰጣል ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል ይሞታል፡፡

 

ወደ መሬት ይመለሳል ይፈርሳል፡፡ ትንሣኤ ዘጉባኤን ጠብቆ ይነሣል፡፡ ይህን በተመለከተ ጌታችን ሲያስተምር “ለዕመ ኢወድቀት ህጠተ ስርናይ ውስተ ምድር ወኢሞተት ባህቲታ ትነብር ወእመሰ ሞተት ብዙኀ ፍሬ ትፈሪ” ዮሐ.12÷24 የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” ሰውም ካልሞተ አይነሣም ካልተነሣም መንግሥተ ሰማያት ሊገባ አይችልምና፡፡ ምክንያቱም ግብር እምግብር ሳይለወጡ መንግሥተ ሰማያት አይገባምና ስለዚህ ሰው ትንሣኤ እንዳለው ገበሬ ከሚዘራው ዘር መማርና ብዙ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅበታል ቅዱስ ጳውሎስም ትንሣኤ ሙታንን ባስተማረበት መልእክቱ ይህንኑ ያጎላልናል፡፡ “ኦ አብድ አንተ ዘትዘርዕ ኢየሀዩ ለዕመ ኢሞተ” 1ቆሮ.15÷35 ነገር ግን ሰው ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ አይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል አንተ ሞኝ የቆሮንቶስ ገበሬ አንተ የዘራኸው ካልሞተ ሕያው አይሆንም የምትዘራውም ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት /በቆሎ ኑግ/ የአንዱ ቢሆን ቅንጣት /ፍሬ/ ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል፡፡

 

ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል፣ ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው የእንስሳ ሥጋ ሌላ ነው የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው ደግሞ ሠማያዊ አካል አለ ምድራዊም አካል አለ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፡፡ የምድራዊ አካል ክብርም ልዩ ነው የፀሐይ ክብር አንድ ነው፡፡ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና፡፡ የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው በመበስበስ ይዘራል፣ በአለመበስበስ ይነሣል በውርደት /አራት አምስት ሰው ተሸክሞት/ ይዘራል/ይቀበራል፡፡ በክብር ይነሣል በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል ፍጥረታዊ አካል ይዘራል/ ሟች ፈራሽ በስባሽ አካል ይቀበራል/ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ማለት የማይሞት የማይታመም የማይደክም ሆኖ ይነሣል” በማለት ወርኃ ዘር የትንሣኤ ሙታን መማሪያ መሆኑን ጽፎአል ከዚህ ላይ አንድ ገበሬ ስንዴ ከዘራ ስንዴ ጤፍ ከዘራ ደግሞ ጤፍ በቆሎም ከዘራ በቆሎ ኑግ ቢዘራ ኑግ እንደሚሆን አካሉን ለውጦ እንደማይበቅል ሰውም የራሱን ማንነት ይዞ የሚነሳ መሆኑንም ጭምር ነው ያስተማረን ሰው ክፉ የሠራም ሥራው ጽድቅ የሠራም የራሱን ሥራ ይዞ ይነሣል እንጂ ጻድቁ ኀጥዕ ኀጥዑ ጻድቅ ሆኖ  አይነሣም፡፡ እንደ ሥራው ዋጋውን የሚቀበልበት ነውና፡፡ “ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንዲል ገላ.6÷7 በሌላም አንቀጽ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡፡ “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ያጭዳል በበረከትም የሚዘራ ደግሞ በበረከት ያጭዳል” 2ቆሮ.9÷6 ይህንም ስለመስጠትና መቀበል አስተምሮታል የዘራ እንደሚሰበስብ የሰጠም ዋጋውን አያጣምና የተዘራባት ምድር የዘሩባት አብዝታ እንደምትሰጥ በምጽዋት መልክ የተቀበሉ ነዳነያንም ትልቅ ዋጋ ያሰጣሉና በሚያልፍ የማያልፍ በሚያልቅ የማያልቅ ዋጋ ያስገኛሉና ምጽዋት በዘር መስሎታል “ዘርን ለዘሪ ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል” 2ቆሮ.9÷10 ጠቅለል አድርገን ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ ባጭሩ ስናስቀምጠው ወርኃ ዘር በዚህ መልኩ ተገልጿል፡፡ “ብዙ ጊዜ በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅመን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት ለመርገምም ትቀርባለች መጨረሻዋ መቃጠል ነው” ዕብ.6÷7 ከዚህም መሬት የተባለ የሰው ልጅ ዘር የተባለ ቃል እግዚአብሔር ዝናም የተባለ ትምህርት እሾህ የተባለ ኀጢአት ክፋት ነው ምድር የዘሩባት ባታበቅል መጨረሻዋ መቃጠል እንደሆነና የሰው ልጅም አደራውን ባይጠብቅ የንስሓ ፍሬ ባያፈራ ፍጻሜው መከራ ነውና፡፡ ሰው እንደ ዘር ወደ መሬት እንደሚመለስ ዘሩ ፈርሶ በስብሶ ከበቀለ በኋላ ፍሬ እንደሚሰጥ ሰውም ከሞተ በኋላ ትንሣኤ ያለው መሆኑን በማሰብ መልካም ሥራን መሥራት እንደሚገባው እንማራለን፡፡ ከዚህ አለፍ ብለን ዘር የሚለውን ስንመለከተው ድንቅ ምሥጢር ያዘለ መሆኑንም ጭምር  እንገነዘባለን፡፡

 

“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር” ኢሳ.1÷9 ይህ ዘር ነቢያት፣ ደቂቀ ነቢያት፣ በተለይም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእርሷ እኛ ለማዳን የተወለደውን ክርስቶስ ያሳየናል፡፡” የነሣውን ሥጋ ከመላእክት የነሣው አይደለም ከአብርሃም ዘር ነው እንጂ” እንዲል ዕብ.2÷16 ቅዱስ ጴጥሮስ ይህ ዘር ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ሲያስረዳ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም በሕያውና ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” 1ጴጥ.1÷23 ስለዚህ የማይጠፋ ዘር የተባለው ክርስቶስ ነው፡፡ ከእርሱ ተወልደናልና እርሱንም በመከራው መስለነው በትንሣኤውም ልንመስለው ያስፈልጋል፡፡

 

3.    ክረምት ወርኃ ልምላሜ ነው፡- በክረምት ወቅት ከዘር ተከትሎ ምድር በቅጠል በልዩ ልዩ የልምላሜ ዓይነቶች አሸብርቃ ደምቃ በዋዕየ ፀሐይ የተራቆተ ማንነቷ በቅጠል የሚሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ወርኃ ልምላሜ ነው፡፡ ፍሬ ግን የለም ይህን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ሰማይን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃል ሳርን በተራሮች ላይ ያበቅላል ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ለሚጠሩት ለቁራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል” መዝ.146÷8-10 በማለት ወቅቱ የልምላሜ የሣርና የቅጠል እንስሳት ሣሩ ቅጠሉን ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ የሚያገኙበት እንደሆነ ገልጿል፡፡

 

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በቢታንያ መንገድ ላይ በተራበ ጊዜ ያያት በለስ ቅጠል ብቻ እንደነበረች በወንጌል ተጽፏል፡፡ “በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርሷ መጣ ከቅጠል በቀር ምንም ፍሬ አላገኘባትምና ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት በለሲቱም ያን ጊዜውን ደረቀች” ማቴ.21÷18 ይላል፡፡ ይኸውም ጊዜው ክረምት ነበር፡፡ ወርኃ ቅጠል የነቢያትን ዘመን ይመስላል በነቢያት በዘመነ ነቢያት ሁሉም በተስፋ ብቻ ይኖሩ እንደነበር እንዲህ ተገልጿአል፡፡ “ብዙ ነቢያትና ጻድቃን ሊያዩ ተመኙ አላዩም የምትሰሙትን ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም” ማቴ.13÷16 ገበሬውም የዘራውን ዘር ቅጠሉን በተስፋ እየተመለከተ አረሙን እየነቀለ ዙሪያውን እያጠረ እየተንከባከበ ይጠብቃል ደግሞም ፈጣሪውን ከበረድ እንዲጠብቅለት እየተማጸነ የራት ሰዓት እስኪደርስ መቆያ እንዲቀምስ ይህ ቅጠል ፍሬ እስኪሰጥ በተስፋ አለኝ እያለ ቅጠሉን የዐይን ምግብ አድርጎ ይጠባበቃል፡፡ በሌላ መልኩ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘሪ በእርሻው ላይ የዘራውን ዘር እንደምትመስል ተጽፏል፡፡

 

“በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲህ ናት ሌሊት ይተኛል ቀን ይነሣል እርሱም /ገበሬውም/ እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ በዘለላው ፍጹም ፍሬ ታፈራለች ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷልና ወዲያው ማጭድ ይልካል፡፡ ማር.4÷26-29 ፍሬ እስከምታፈራ ግን ገበሬው እንደሚጠብቅ ነው የሚያስተምረን በገበሬው የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስም እኛ በዓለም ላይ ያለን የሰው ዘሮች በሙሉ በመከር ያፈራውም ያላፈራውም እንዲሰበሰብ ያሳየናል፡፡ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ እነሆ ገበሬው የፊተኛውን የኋለኛውን ዝናም እርሱን የታገሰ የከበረውን የምድር ፍሬ ይጠብቃል እናንተም ደግሞ ታገሡ” የዕ.5÷7-9 ገበሬ ቅጠሉ ፍሬ እስከሚሰጥ ምን ያህል መከራን እንደሚታገስ እኛም መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ቅጠል ብቻ የሆነ ማንነታችን የንስሐ ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ መከራውን መታገስ እንደሚገባን ያስተምራል፡፡ ምድራዊ ፍሬ ለማግኘት ይህን ያህል መጠበቅ መታገስ ካስፈለገ ሰማያዊ ዋጋ ለመቀበል ምን ያህል መታገስ ያስፈልግ ይሆን? ከወርኃ ቅጠል የምንማረው ያለፍሬ ብንገኝ መርገምን እንደምናተርፍ ብናፈራ ግን ገበሬ ደስ ብሎት ምርቱን ደስ ብሎት እንዲሰበስብ ፈጣሪያችንም በእኛ የሚደሰት መሆኑን እናውቃለን እኛም ዋጋችንን እንደምናገኝ እንማራለን፡፡ ክረምት ጥልቅ ትምህርት የምንማርበት እግዚአብሔር በሰፊው የሚገለጽበት ነው፡፡

 

ይቆየን