ኪዳነ ምሕረት!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
የካቲት ፲፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የዕረፍት ጊዜ እንዴት ነበር? መቼም ቁም ነገር ሠርታችሁበት እንዳሳለፋችሁ ተስፋችን ነው፡፡ ለእናንተ ለተማሪዎች የዓመቱ አጋማሽ የምዘና ፈተና ነበር! የፈተናስ ውጤታችሁ እንዴት ነበር? እንግዲህ የዓመቱ አጋማሽ የትምህርት ወቅት አልቆ ፈተናም ተፈትናችሁ ውጤት የተመለከታችሁና በርትታችሁ በማጥናት ጥሩ ውጤት አግኝታችሁ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ልጆች! በተለያየ ምክንያት ውጤታችሁ ዝቅ ያለባችሁ “ከትናንት ብንዘገይም ከነገ እንቀድማለን” እንደሚባለው ትላንት አልፏል፡፡ ነገን ግን በርትታችሁ በመማርና በማጥናት ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ መቅደም ትችላላችሁ! በርቱ! ለዛሬ የምንማማረው ስለ እመቤታችን ኪዳነ ምሕረትና ከአምላካችን ስለተሰጣት ቃል ኪዳን ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወር በገባ በ፲፮ኛው (ዐሥራ ስድስት) ቀን “ኪዳነ ምሕረት” ብለን የምናከብረውና የምንዘክረው ታላቅ በዓል አለ፡፡ ታዲያ ይህ በዓል ለምን የሚከበር ይመስላችኋል? ጌታችን አምላከችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የምሕረት ቃል ኪዳን የገባበት መታሰቢያ ነው፡፡ ኪዳን ማለት “ውል፣ ስምምነት” ማለት ነው፡፡

ልጆች! ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከብዙ ከቅዱሳን አባቶቻችን እና ከቅዱሳት እናቶቻችን ጋር ቃል ኪዳንን አድርጓል፡፡ ይሄ ቃል ኪዳን በእነርሱ ስም ተማጽኖ ለሚለምነው የወደዱትን ሁሉ እንደሚያደርግ ነው፡፡ ታዲያ ልጆች! ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነች እመቤታችንም ከልጇ ጋር ቃል ኪዳንን አድርጋለች፡፡ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ላይ ፷፬ (ስድሳ ዐራት) ዓመት ከኖረች በኋላ ከማረፏ በፊት ጌታችን ብዙ ቃል ኪዳን ገባላት፡፡ በስሟ ተማጽኖ የሚለምነውን፣ በስሟ ለተራበ የሚያበላውን፣ በስሟ ዝክር የሚዘክረውን፣ በስሟ የሚማጸነውን…. ከመከራ እንደ ሚጠብቀው በኋላም ሲሞት ነፍሱን በክብር በገነት እንደሚያስገባ ቃል ኪዳን ገባላት፡፡

አያችሁ ልጆች! የእመቤታችንን ስም ሁልጊዜ በውዳሴ ማርያም፣ በቅዳሴ፣ በሰዓታት ጸሎት የሚጠራት እንዲሁም በእርሷ ስም የሚዘክሩ በምድር ሲኖሩ ቤታቸው ይባረካል፡፡ በችግራቸው ጊዜ ሲጠሯት ፈጥና ትመጣና ችግራቸውን ታቃልላለች፡፡ ዕውቀትን ማስተዋልን ትሰጠዋለች፤ በኋላም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ደግሞ ወደ ገነት ይገባሉ፡፡ ይህንን ቃል ኪዳን የሰጣት ልጇ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ነው፤ ይህም በየካቲት ፲፮ ቀን ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት እመቤታችን ከፍርድ ያዳነችውን ስምዖን (በላዔ ሰብ) ስለ ተባለው ታሪክ ከተአምረ ማርያም ላይ ካገኘነው በአጭሩ እንንገራችሁ፡፡ ስምዖን የሚባል እመቤታችንን በጣም የሚወድ በእርሷ ስም የተራበ የሚያበላ፣ እንግዶችን የሚቀበል፣ ዘወትር በጸሎት የሚማጸናት ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይገርማችኋል ልጆች! ሰዎች መልካም ሲሠሩ የማይወድ ሰይጣን አንድ ቀን እንግዳ መስሎ መጣና አታለለው፡፡ ብዙ ኃጢአትም እንዲሠራ አደረገው፡፡ ከዚያም ለሰዎች መልካም ያደረግ የነበረውን ሰው ሰዎችን የሚገድል ጨካኝ ሆነ!

ልጆች! አንዳንድ ጊዜ መልካም የሚመስሉ ግን ኃጢአት የሆኑ ብዙ ነገርች አሉ፡፡ እነዚህን ከማድረጋችን በፊት አባቶችንና ታላላቆችን ማማከርና ዘወትር በጸሎት ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያም መልካም ነገር በሠራን ቁጥር ጠላታችን ሰይጣን ያንን ሊያስተወን ይተጋል፤ ይጥራል፡፡ ታዲያ ይህንን ድል የምናደርገው ሁሌ በጸሎትና መልካም ምግባር በመያዝ ነው፡፡ ልጆች! ስምዖን በጣም ደግ ሰውና የዋህ ነበር፡፡ ሰይጣን ቤቱ እንግዳ መስሎ መጣና “እኔ የምበላው የሰው ሥጋ ነው፡፡ ከፈለክ ልጅህን ሰዋልኝ” ብሎ የዋህነቱን ተጠቅሞ አታለለው፡፡ ልጁንም እንዲሰዋለት አደረገው፤አ ያችሁ ጌታችን ቅዱሳን ሐዋርያትን ሲነግራቸው እንደ ርግብ የዋህ ብቻ ሁኑ አላለም፡፡ እንደ እባብም ልባም ሁኑ ብሏል፡፡ ስለዚህ አንድን ነገር ቸኩለን ከማድረጋችን በፊት አስተዋይና ብልህ መሆን ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህ ሰው ሳያውቀው ሰዎችን መግደል ጀመረ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በመንገድ ሲሄድ በጣም የቆሰለ በዚያ ላይ በረሃብ አንጀቱ የተጣበቀ እና በውኃ ጥም የተጎዳ ሰው አገኘ፡። ሊገድለው ሲልም መከራው ራሱ አድክሞታል፡፡ ታዲያ አልፎት ሲሄድ ይሄ ምስኪን የተጠማ ሰው “ስለ እግዝእትነ ማርያም፣ ስለ ቤዛዊት ዓለም ውኃ አተጣኝ” አለው፡፡ የዚህን ጊዜ ስምዖን ( በላዔ ሰብ) ቆም አለና አዳመጠው፡፡ የእመቤታችንን ስም ሲጠራ ልቡ ድንግጥ ድንግጥ አለበት፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት ይህንን ስም አውቀዋለሁ አለ ! ከዚያም ከያዘው የውሃ ኮዳ ጥቂት ጠብታ ብቻ በጉሮሮው ላይ ጠብ አደረገለት፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ያ የተጠማ ሰው በጣም ሰውነቱ ተጎድቶ ስለ ነበር ውኃውን ከአፉ ጠብ ቢያደርግለትም ከሞት ሊታደገው አልቻለም፤ ከዚያም ሞተ፡፡ ስምዖን የተባለው (በላዔ ሰብ) ሽፍታም ከብዙ ጊዜ በኋላ ሞተ፡፡ ከዚያም እርኩሳን መናፍስት ሰይጣናት ያችን ነፍስ “የእኛ ናት፤ ኃጢአት ስትሠራ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ሲዖል እንውሰዳት” አሉ፡፡ እመቤታችንም “ይህች ነፍስ መሄድ ያለባት ወደ ገነት ነው’ አለች”” ልጇን ጌታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስምሽን የጠራ፣ በስምሽ ለተጠማ ያጠጣ እምርልሻለው ብለህ ቃል ኪዳን ገብተህልኛል፡፡ ይህ ሰው ቀድሞ በእኔ ስም ይዘክር፣ የተራቡትን ያበላ ነበር፡፡ በኋላም ሰይጣን አሳስቶት ብዙ ኃጢአት ሠርቷል፡፡ አሁን ደግሞ ተመልሶ በእኔ ስም የተጠማን ሰው አጠጥቷል፤ በጎ ምግባርን ሠርቷል፡፡ ስለዚህ ማርልኝ” አለችው፡፡ ጌታችንም በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ያንን ሰው ማረላት፡፡

አያችሁ! ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት ቃል ኪዳን ነው ያልናችሁ ለዚህ ነው፡፡ እመቤታችንን በተሰጣት ቃል ኪዳን በስሟ አምኖ ለሚማጸን፣ ለተራበው የሚያበላና ለተጠማው የሚያጠጣ ከልጇ ምሕረትን ታሰጠዋለች፡፡ ይህ ስምዖን (በላዔ ሰብ) የተባለውን በአማልጅነቷ አስማረችው፤ ይቅርታ እንዲያገኝ አደረገችው፡፡ እንግዲህ ቅዱሳን አባቶች በሠሩልን ሥርዓት መሠረት ወር በገባ በ፲፮ኛው (ዐሥራ ስድስት) ቀን ኪዳነ ምሕረት ብለን እናከብራለን፡፡ የካቲት ፲፮ ደግሞ ዓመታዊ ክብረ በዓሏ ነው፡፡ ለግንዛቤ ያህል ከብዙ ተአምሯቷ፣ አማልጅነቷ አንዱን ብቻ ጠቀስንላችሁ፡፡

ልጆች! በእመቤታችን ስም ካለን ላይ ቀንሰን ለተራበ ስናበላ፣ ስንመጸውት፣ ስሟን ጠርተን በጸሎት ስንማጸን ትባርከናለች፡፡ ስለዚህም ለሰዎች በጎ ነገርን ለማድረግ እንትጋ!

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷና ረድኤቷ ይደርብን፤ አሜን!!!

ምንጭ፡- ተአምረ ማርያም፣ የካቲት ፲፮

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!