‹‹ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ ድምጼንም ይሰማሉ፥ አንድ መንጋም ይሆናሉ እረኛውም አንድ ነው›› (ዮሐ. ፲፥ ፲፮)

በጎች የተባሉ ምእመናንን በለመለመች መስክ በቤተ ክርስቲያን በማሰማራት የሕይወት ውኃ የተባለ ቃሉን የሚመግባቸው እረኛቸው ነው። ወተት የሆነ ቃሉን በመመገብ በክርስቲያናዊ ሕይወት በማጽናት ለሥጋ ወደሙ በማብቃት ለሰማያዊው ርስት ያዘጋጃቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እያንዳንዱን በግ (ምእመን) በስም ማወቅና መለየት፣ ሊቀርባቸውና ሊከታተላቸው፣ የሚመገቡትም ቃለ እግዚአብሔር ያዘጋችላቸዋል፡፡ ምእመናን ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል፡፡›› (መዝ ፳፪፥ ፩-፪) ማለት የሚችሉትና የእግዚአብሔርን ቸርነት ሊረዱ የሚችሉት አዕይንተ እግዚአብሔር በተባሉ ካህናት በሚገባ ሲጠበቁና ቃሉን በአግባቡ ሲመገቡ ነው።

ሆኖም በጎች ምእመናን ሕገ እግዚአብሔርን ሊዘነጉና ብሎም ኃጢአት በመሥራት ከእረኛቸው እየራቁም ይሄዳሉ፡፡ እረኛቸው ግን መመለሻ መንገዱን እስኪያገኙ ድረስ በትዕግሥት ይጠብቃቸዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ አባግዕ ሲያስተምር ‹‹ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ ድምጼንም ይሰማሉ፥ አንድ መንጋም ይሆናሉ እረኛውም አንድ›› ብሏል። (ዮሐ. ፲፥ ፲፮) ሕዝብና አሕዛብን አንድ ያደረገ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራውን የሠራው ዓለም ሁሉ በእርሱ እንዲያምንና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው። (ዮሐ. ፫፥ ፲፮) አምላካችን ሁሌም ወደ እርሱ እንድንመለስ ይፈልጋል፤ ‹‹የመዳን ቀን አሁን ነው›› (፪ ቆሮንቶስ ፮፥፪) ይላልና ቃሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ሲያስተምር ‹‹መቶ በጎች ያሉት ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ላይ ይሸከመዋል፤ ወደ ቤት በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እላችኋለሁ÷ እንዲሁ ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል›› በማለት ተናግሯል። (ሉቃ. ፲፭፥፬-፯)

በዚያን ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ንስሓ ስለ መግባት መናገሩ ፈሪሳውያኑን አስገርሟቸው ነበር። እነርሱ ራሳቸውን እንደ ጻድቅ አድርገው የሚቆጥሩ ስለነበሩ ንስሓ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው አላመኑም። አንዳንዶቹ ጌታችን ኢየሱስን ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር በመብላቱ በነቀፉት ጊዜ ‹‹ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስልጋቸውም፤ ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም›› ብሏቸዋል። (ማር. ፪፥፲፭-፲፯) ራሳቸውን የሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን ግን ንስሓ መግባት እንዳለባቸው አያስተውሉም፡፡

ስለ ጠፋው በግ ምሳሌ አድርጎ ጌታችን ኢየሱስ ያስተማረው ኃጢአተኞች ንስሓ ገብተው መዳን እንደሚችሉ ለማስረዳት ነው፤‹‹እላችኋለሁ÷ እንዲሁ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል›› አለ። (ሉቃ.፲፭፥፲) ስለዚህ በኃጢአት ውስጥ ያሉ ሰዎችም ይህን ቃል በመረዳት በንስሓ ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ተጠርተዋል፤ በጎች ወደ በረታቸው ተመልሰው እረኛቸውን ማግኘት አለባቸውና፡፡

ምእመናንን እንዲጠብቁ ሰማያዊ ሥልጣንን የተቀበሉ ካህናትም ከግል ሕይወታቸው በተጨማሪ በተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ምን እንደሰሩበት በሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠየቃሉ። ስለሆነም ካህናት ለልጅነት ተጠርተው ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ያልተነገራቸውን የጠፉ የተባሉትን በማስተማርና በማጥመቅ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የመመለስ መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው።

ምእመናንም ቸሩ እረኛ መድኃኔዓለም በዳግም ምጽኣቱ በቀኙ ከሚያቆማቸው በበጎች ከተመሰሉ ማኅበረ ጻድቃን ለመደመር በሕገ እግዚአብሔር በመኖር ሊጸኑ ይገባል። ሁላችንም ኃላፊነታችንን በአግባቡ ተወጥተን የሰማያዊ ክብር ተካፋዮች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡