ከራድዮን

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ግንቦት ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

መጽሐፍ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር አልተወም፡፡ እግዚአብሔር የህልውናው፣ የቸርነቱ፣ የፍቅሩ፣ የኃይሉ፣ የማዳኑ ምስክሮች አድርጎ ካስቀመጣቸው ፍጥረታት መካከል አንደኞቹ እንስሳት ናቸው፡፡ ጻድቁ ኢዮብም “አሁንም እንስሳትን ጠይቅ ያስታውቁህማል፤ የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል” በማለት ተናግሯል፡፡ (ኢዮ.፯፥፯)

ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊትም በመዝሙሩ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ፍጥረት የእጁን ሥራ ያወራል” በማለት በመዘመሩ ይህን እውነት ያጠነክርልናል፡፡ (መዝ.፲፱፥፩) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሐዲስ ኪዳን ሰዎች ሆነን ተፈጥረን በአንዳች ነገር መጨነቅ እንደማይገባን ሲያስተምረን “የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤” እንዲሁም “የዱር አበቦችን ተመልከቱ” በማለት ፍጥረታትን ማስተማሪያዎችና የእግዚአብሔር ምስክሮች መሆናቸውን ነግሮናል፡፡ (ማቴ. ፮፥፳፮)

መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስም በጸሎትና ሥርዓተ አምልኮ በሚፈጸምበት ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ሊከተሉ ስለሚገባው የአለባበስ ሥርዓት በስፋት ካስተማረ በኋላ “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁምን? በማለት መናገሩ ሥተ ፍጥረት የሥርዓት ሰባክያን መሆናቸውን መስክሯል፡፡ (፩ ቆሮ.፲፩፥፲፬) ከዚህም ባሻገር አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር አንዳንድ እንስሳትና አዕዋፍ በተለየ መልኵ ተፈጥሯቸው የእርሱ ሥራንና የባሕርይ መገለጫው የሆኑትን ከሃሊነቱን፣ ሕያውነቱን፣ ኃያልነቱን ስለሚገልጡ የእርሱ ምሳሌዎች አድርጎ አቅርቧዋል፡፡ እንደ ምሳሌም፡-

እሳት፡- እሳት በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩ ፍጥረታት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ለእስራኤል ዘሥጋ ሲያስተምራቸው “አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት፣ ቀናተኛም አምላክ ነውና” በማለት ነግሮዋቸዋል፡፡ (ዘዳ.፬፥፳፬) ይህ ቃል አምላካችን እግዚአብሔር ራሱን በእሳት መስሎ እንደገለጠ ያስተምረናል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእሳት ተመስሏል፡፡ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ተብላ በምትጠራው ዕለተ ጰራቅሊጦስም መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ እሳት ተገልጧዋል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፩፣ የሐዋ.፪፥፩-፫) በብሉይ ኪዳን “የሚበላ እሳት” የተባለ አምላካችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለምን በእሳት ተመሰለ? ለሚለው ጥያቄ ሊቃውንቱ በትርጓሜያቸው ምክንያቶችን ገልጸውልናል፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለማንሣት፡-

 • እሳት ረቂቅ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነው፡፡
 • እሳት በብሉይ ኪዳን ያጠፉ ሰዎች ተቀጥተውበት ነበርና ሰዎች ያንን አይተው እሳት የተፈጠረው ለቁጣ ብቻ ነው እንዳይሉ ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለማስረዳት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ራሱን በአምሳለ እሳት ገለጠ፡፡
 • እሳት ዱር ይገልጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጣል፡፡
 • እሳት ከቡላድ ወይም ከክብሪት ሲወጣ በመጠን ይወጣል፤ ከዚያ በኋላ ግን በማገዶ ያስፋፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ጊዜ ጸጋውን የሚሰጠው በመጠን ነው፤ በኋላ ግን ምግባር እየሠሩ፣ ትሩፋት እያሰፉ ለሚሄዱ ሰዎች ጸጋውን እያበዛ ይሄዳልና፡፡
 • እሳት በመጠን ከሞቁት ሕይወት ጤና ይሆናል፤ መጠን አልፈው ከሞቁት ግን ጥፋትን ያመጣል፤ እግዚአብሔርም በእምነት ሆነው በአንክሮ ከመረመሩት ሕይወት ይሆናል፤ በድፍረት ከመረመሩት ግን ይቀጣልና፡፡ (፩ቆሮ.፪፥፲፪-፳፣ ኢዮ.፲፩፥፬-፰፣ ሮሜ ፲፩፥፴፫)
 • እሳት ውኃ ካልገደበው ያቀረቡለትን ሁሉ ያቃጥላል፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ቸርነቱ ምሕረቱ ካልከለከለው ሁሉን ሊያደርግ ሊያጠፋ ይችላልና፡፡

እሳት ምግብን ያጣፍጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችንን በጸጋው ያጣፍጣልና፡፡ ሸክላ ሠሪ የሠራችው ሸክላ የነቃባት እንደሆነ እንደገና አፍርሳ በውኃ ለውሳ፣ በእሳት ተኩሳ ትሠራዋለች፤ የነፍስ መታደስም በመንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ (ወንጌል ትርጓሜ፣ ገጽ ፺፮)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም መንፈሳዊ ድርሰቱ የሙሴን ቃል ይዞ “ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚባላ እሳት ነው፡፡ እሳታውያን የሚሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል ሊነኩት የማይቻላቸው በእውነት እሳት ነው” በማለት በአንክሮ ይዘምራል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ገጽ ፻፷፪)

አንበሳ ፡- አንበሳ እግዚአብሔር ግርማንና መፈራትን አላብሶ ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንዱ ነው፡፡ በመጻሕፍትም አንበሳ እንደየአገባቡ በልዩ ልዩ መንገድ ለተለያዩ ነገሮች ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር በአንበሳ እንደሚመሰል ነቢዩ ሲናገር “አንበሳው አገሣ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?” በማለት አስተምሮሯል፡፡ (አሞ. ፫፥፰)

አንበሳ ሲያገሣ ከግርማው የተነሣ እንስሳት በሙሉ እንደሚፈሩና እንደሚደነግጡ እግዚአብሔርም ሲናገር በኃያልነቱና በግርማው የማይፈራና የማይደነግጥ የለም፡፡ መጻሕፍት የአንበሳን ተፈጥሯዊ ባሕርይ ከጌታቸን ትንሣኤ ጋር በማሰናሰል ይገልጡታል፡፡ አንበሳ ሲተኛ ዓይኑን ያፈጣል፤ ሲነቃ ዓይኑን ይከድናል፤ ይህንም ከሚያደርግበት ደመ ነፍሳዊ ምክንያት ሊቃውንቱ ሲገልጡ አንበሳ ምንም ጊዜ ክብሩን አስጠብቆ መኖርን የሚፈልግ፣ ለክብሩ ኗሪ ነውና ዕረፍት በሚያደርግበት (በሚተኛበት) ጊዜ ጠላት እንዳያጠቃው ዓይኑን ያፈጣል፡፡ እንዲህ በማድረጉም በቁሙ ይፈሩት የነበሩት ሁሉ በተኛም ጊዜ ይፈሩታል፡፡ ምክንያቱም አንበሳ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው በእንቅልፍ ነውና፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ጥበበኛ ነበርና ይህ የአንበሳ ጥበብ ተገልጦለት ሲተኛ ዓይኑን ይገልጥ፣ ሲነቃ ደግሞ ዓይኑን ያፈጥ ነበር፡፡ በመሆኑም ጠቢቡ “እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል” በማለት ዘመረ፡፡ (መኃ.፭፥፪)

የዚህ የአንበሳ ነገር ምሳሌነቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ነው፡፡ አንበሳው ነቅቶ ሳለ አራዊትን ለማደን የተኛ እንደመሰለ ጌታችንም በሞቱ ሞትን ለመግደል በሥጋው በሞተ ጊዜ በመለኮቱ ሕያው ነውና፡፡ ሞት ዲያብሎስም በመስቀል ላይ የተደረገ ሞቱን አይቶ እንደ ዕሩቅ ብእሲ የመድኃኔዓለምን ነፍስ በሲኦል ሊቆራኝ በቀረበ ጊዜ በኃይሉ ሰቅዞ ይዞ በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶት በእጁ የነበሩትን ነፍሳትን ነጻ አውጥቷልና፡፡ (ምዕላደ ጥበብ ፡- መ/ር በጽሐ ዓለሙ፣ ገጽ ፪፻፹፩፣ ቆላ.፪፥፲፬፣ ፩ጴጥ. ፫፥፲፱ መዝ.፷፯፥፲፰) በመጽሐፍ ጌታችን “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” ተብሎዋል፡፡ (ራእ.፭፥፭)

ከራድዮን

ከራድዮን ነጭ ወፍ ሲሆን በሊቃውንቱም ዘንድ የታወቀ ነው። ጠቢባን በድካም ፈልገው አድነው ይይዙታል፤ የታመመ ሰው ቢኖር ያቀርቡታል፤ እርሱም በሽተኛውን ትኩር ብሎ ያየዋል፤ የማይድን ለሞት የቀረበ ከሆነ ፊቱን አዙሮ ይመለሳል፤ ቀኑ ገና ከሆነ ግን አፉን ከፍቶ ከበሽተኛው አፍ እስትንፋሱን ይወስዳል፤ በልዑል እግዚአብሔር ኃይል የሰውየው ደዌ ሙሉ ለሙሉ ወደ ወፉ በእስትንፋሱ ይተላለፋል። ሰውየው ይድናል፤ ወፉ ይታመማል። ፊት ነጭ የነበረው እንደ ከሰል ይጠቁራል፤ ሕመም ሲሰማው ወደ አየር ይነጠቃል፤ ሲብስበት ወደ ባሕር ራሱን ይወረወራል። በባሕር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ቆይቶ ጠጉሩን መልጦ በዐዲስ ተክቶ፣ ድኖ፣ታድሶ፣ ኃያል ሆኖ ይወጣል። ይህ ፍጥረት በዕለተ ሐሙስ የተፈጠረ ፍጥረታት ነው፡፡ ስለምን ፈጠረው? ቢሉ የወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማያምኑ ትምህርት ምሳሌ አብነት ይሆን ዘንድ ይህን ወፍ የማዳን ኃይል ሰጥቶ ፈጥሮታል። ምሳሌነቱ እንደምንድነው? ቢሉ

 • ከራድዮን ወፍ ፡-  የክርስቶስ ምሳሌ
 • የታመመው ሰው ፡- የአዳም ዘር ምሳሌ ሲሆን
 • ወፉ በዐይኑ መመልከቱ ፡- ክርስቶስ የሰው ልጆችን በሙሉ ለማዳን በምሕረትና በቸርነት ዓይኑ ለመመልከቱ ምሳሌ
 • ወፉ መታመሙ ፡- ክርስቶስ ስለ እኛ በደል መታመሙ ምሳሌ
 • መጥቆሩ ፡- ጌታችን ለእኛ ቤዛ ሊሆነን ከኃጢአተኞች ጋር ለመቆጠሩ ምሳሌ
 • ወፉ ወደ ላይ መውጣቱ ፡- ክርስቶስ ከፍ ብሎ በመስቀል የመሰቀሉ ምሳሌ
 • ወፉ በባሕር ሦሰት ቀን ሦስት ሌሊት መኖሩ ፡- ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ሦሰት ቀንና ሦሰት ሌሊት ለማደሩ ምሳሌ
 • ከራድዮን ወፍ ታድሶ ኃያል ሆኖ ከባሕር መውጣቱ ፡- ክርስቶስ በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን አድሶ፣ አንጽቶ ገነት አስገብቶ፤ እርሱም ወደ ቀደመ ክብሩ ለማረጉ ምሳሌ ነው፡፡                                                                                                                                                                                                          ይቆየን!