ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጥር ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! አንድ ነገር ለማወቅ በጣም ጓጓን! ምን መሰላችሁ? ስለ ዘመናዊ ትምህርት ውጤታችሁ! በዚህ ጎበዞች እንደ ሆናችሁ ብናምንባችሁም እንደው የግማሽ ዓመት የፈተና ውጤታችሁ ምን እንደሚሆን እንገምታለን፤ ጥሩ ውጤት እንዳመጣችሁ አንጠራጠርም!

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ወላጆቻችን ብዙ የምንፈልጋቸውን ነገሮች እያደረጉልን ተምረን ትልቅ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ሲመኙ እኛ ደግሞ ጎበዞች ሆነን ልናስደስታቸውና የድካማቸውን ዋጋ የሆነውን መልካም ውጤት ልናሳያቸው ይገባል፡፡ አይደል ልጆች? መልካም!!!

ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርት መማር እንዲሁም በሰንበት ትምህርት ቤት ማገልገል ይገባናል፤ የምንማረው ትምህርት እንዲገለጽን ደግሞ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ መጸለይ በሥነ ምግባር ታንጸን ማደግ ይገባናል፡፡ መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ‹‹ልጅነቴ›› በሚል ርእስ የልጅነት ጸጋን እንዴት እንደምናገኝ ተምረን ነበር፤ አሁን ደግሞ የልጅነት ክብርን ካገኘን በኋላ በሃይማኖት እንዴት መጽናት እንዳለብን እንማራለን፡፡

ያለንበት ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ይባላል፤ አስተርእዮ ማለት “መገለጥ” ማለት ነው፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት እኛን ለማዳን መውረዱ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ እና በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንሰ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ ጌታችን እኛን ለማዳን መጥቶ ከጠላታችን ከዲያብሎስ ባርነት (አገዛዝ) ነጻ ስላደረገን ልጆቹ ሆንን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክርስቶስ ከሚለው ከጌታችን ስም ተወስዶ ክርስቲያን አሰኘን (ተብለን ተጠራን)፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ያዳነንን አምላካችንን የምናገኘው (የምናምነው) በሃይማኖት ነው፤ እኛ የምናምነው ሃይማኖታችን ስያሜው ደግሞ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ይባላል፤ “ለመሆኑ ይህ ስያሜ ከየት መጣ? ማን ሰየመን? ትርጉሙስ ምንድን ነው? የሚለውን እንማማራለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክርስቲያን የሚለው ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ‹‹…ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ…›› እንዲል፤ (የሐዋ.ሥራ ፲፩፥፳፮) ከዚያን በኋላም ተምረውና አምነው የሚጠመቁት ምእመናን “ክርስቲያን” የሚለውን ታላቅ ስም ይሰየማሉ፤ አያችሁ ልጆች የምንጠራበት ስም ታላቅ ነው! ታዲያ መልካም ሥራ በመሥራት እንደምንጠራበት ስም ልንሆን ያስፈልጋል፤ ክርስቲያን የሚለውን ስም ስንሰማ ጌታችን እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን በመስቀል ላይ እኛን ለማዳን መሰቀሉን እናስታውሳለን፤ ከዚያም መልካም እና በጎ ጥሩ ምግባር ያለው በሃይማኖቱ የጸናና በምግባር የታነጸ ልጅ እንድንሆን ይረዳናል፤ በስሙ ከተጠራን እንደ ስማችን መሆን አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክርስቲያን በሚለው ላይ ደግሞ ኦርቶዶክስ የሚልም ቃል አለበት፤ ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የጽርእ (የግሪክ) ቃል ሲሆን ትርጉሙ “ኦርቶ ማለት ርቱዕ (የተስተካከለ ቀጥ ያለ) ዶክስ- “ሐሳብ፣ ኅሊና” ማለት ነው፤ አንድ ላይ ደግሞ የቀና አስተሳሰብ “ርቱዕ ሃይማኖት” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፪፻፵፫)

ክርስቲያን በሚለው ስያሜ ላይ ኦርቶዶክስ የሚለውን በ፫፻፳፭ (ሦስት መቶ ሃያ አምስት) ዓ.ም ኒቂያ በሚባል ቦታ በሃይማኖት ጉዳይ የተሰበሰቡ ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት) ሊቃውንት አባቶቻችን ናቸው፤ ለምን ጨመሩበት መሰላችሁ? አርዮስ የተባለ ሰው እኛ በምናምናት እውነተኛ ሃይማኖት ላይ የስሕተት ትምህርት ይዞ ተነሣ፤ በዚህን ጊዜ ልጆች አባቶች ጉባኤ ሠርተው አስተማሩት፤ መከሩት፤ እርሱ ግን አልመለስም በማለት ዓመፀ፤ በዚህን ጊዜ አባቶቻችን አርዮስን ሌሎችን በስሕተት ትምህርቱ እንዳያሳስት አውግዘው ለዩት፤ እርሱም “ክርስቲያን ነኝ” እያለ ክህደትን ስላስተማረ አባቶቻችን እውነተኛዋን እምነት ክርስትናን ተጨማሪ ስያሜ አደረጉላትና ‹‹ኦርቶዶክስ ክርስቲያን›› ብለው ሰየሙ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚህ ስም መጠራት ጀመርን፤ አያችሁ ልጆች የእምነታችን መጠሪያ ስያሜ እንዲሁ አልተሰየመም፤ ምክንያት አለው፤ እኛም እንደስያሜው በእምነት የጸናን ከሐሰተኞች የተለየን መሆን አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ደግሞ ተዋሕዶ የሚል ስያሜም አለ፤ ይህም ስያሜ የተሰየመው በአባቶቻችንን ነው፤ በ፬፻፴፩ ዓ.ም ንስጥሮስ የተባለ ሰው በትክክለኛ እምነት ላይ የሐሰት ትምህርት በማስተማሩ ኤፌሶን በሚባል ከተማ አባቶቻችን ተሰብስበው (ጉባኤ) ሠርተው ንስጥሮስ ላነሣው ጥያቄ ምላሽ ከሰጡት በኋላ እርሱ ግን በያዘው የስሕተት ትምህርት ስለ ጸና አባቶቻችን ሌሎች በእርሱ የስሕተት ትምህርት እንዳይሳሳቱ “ኦርቶዶክስ ክርስቲያን” በሚለው ላይ “ተዋሕዶ” የሚል ጨመሩበት፤ ምክንያቱም ንስጥሮስም “ኦርዶቶክስ ክርስቲያን ነኝ” ስላለ የእርሱን የሐሰት ትምህርት ሌሎች ባለማወቅ እንዳይከተሉ በማለት ‹‹ተዋሕዶ›› የሚል ቅጽል በመጨመር የሃይማኖችን ስያሜ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን” ተብሎ መጠራት ጀመረ፡፡ ከዚህም የተነሣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ እንባላለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የሃይማኖት ስያሜ ያገኘንባቸውን ጉባኤያት እነ ማን እንደ ሆኑ የበለጠ ለመረዳት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ገጽ ፪፻፺፮) የሚለውን መጽሐፍ አንብቡ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ የሃይማኖታችን ስያሜ የመጣው ከዚህ ነው፤ በቀጣይ ጊዜ ደግሞ “ሃይማኖት፣ ከዚያም ነገረ እግዚአብሔር፣ ትምህርተ ሃይማኖት” በሚሉ ርእሶች እንማራለን፡፡ ስም መጠሪያ ብቻ አይደለም፤ መታሰቢያም ጭምር ነውና፤ የእምነታችንን መጠሪያ ስያሜንና ታሪኩን በደንብ በማጥናት እንወቀው! ቸር ያገናኘን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!