ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እና እስልምና በኢትዮጵያ

ታኅሣሥ ፳፮፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል እየተዘጋጀ የሚቀርበው የጥናትና ምርምር ጉባኤ ታኅሣሥ 22/2015 ዓ.ም በማኅበሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ 3ኛ ፎቅ በርካታ ምእመናን በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን በዕለቱ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ከእነዚህም “ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እና እስልምና በኢትዮጵያ ዕቅበተ እምነታዊ ጉዳዮች” በሚል የቀረበው አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን በ6ኛ መ/ክ የነበራት ግዛትና ተጽእኖ እስከ ዓረቢያን ምድር የሰፋ እንደነበረ የተለያዩ ድርሳናት እንደሚመሰክሩ በጥናቱ መግቢያ ተጠቁሟል። ይህን የግዛት ወሰን ተከትሎ በአቅራቢያ ከሚገኙ የዓረብ ሀገራት ጋር በተለያዩ መንገዶች ለመገናኘት በር ከፍቷል።

የኢትዮጵያ ክርስትና እና የእስልምና አነሣሥ ዕቅበተ እምነታዊ እይታ

“ኢትዮጵያ በነበራት የግዛት ወሰን ምክንያት ከዓረቡ ዓለም ጋር በቅርብ የመገናኘት በር ከፍቶላት ቆይቷል። በንግድ፣ በባህል፣ መንግሥት ከመንግሥት ወዘተ በነበረ ቀደምት ግንኙነት የሚሸጋገሩና የሚወራረሱ መገለጫዎች ሊከሠቱ እንደሚችሉ በጥናቱ ተጠቁሟል። ለምሳሌ ያህል ቋንቋ፣ ባህል፣ ጋብቻ፣ ሃይማኖታዊ እሳቤዎችና ሥርዓቶች የመሳሰሉት በሚፈጠሩ መልካም ማኅበራዊ ግንኙነት ሊወራረሱ ይችላሉ፡፡” ሲሉ አጥኚው ገልጸዋል። እንዲህ ያለው ማኅበራዊ መስተጋብር መተሳሰብን የመፍጠር አቅሙ ከፍ ያለ በመሆኑ መደጋገፍን፣ መተዛዘንን፣ መተሳሰብን ያጎለብታል። (Haggai Enrich, Ethiopia and the Middle East, London: Lynne Rienner Publihers, 1994)

ሐበሻን አትንኩ ለምን?

“ቀደምት ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሰጠቻቸው የማይነጥፍ ዕውቀት መንፈሳዊና ዕውቀት ሥጋዊ ራሳቸውን በሥነ ምግባር ጠብቀው እንዲኖሩና በሂደትም ከባህላቸው ጋር አዋሕደው የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንዲሆን ማገዙ እሙን ነው። እንግዳ መቀበላቸው፣ አዛኝነታቸው፣ ለጋስነታቸው፣ ቸርነታቸው፣ ርኅራኄያቸው ይጠቀሳል። ይህም በእንግድነት የመጡ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችን ተቀብለው በእንግድነት ማስተናገዳቸው ዋቢ ምስክር ነው። ይህን ተከትሎ ነቢዩ መሐመድ ‘ሐበሾችን አትንኩ’ ሲሉ መመሪያ መስጠታቸው በጎነትን የተላበሱ እሳቤዎችን ለዕቅበተ እምነት መጠቀም እንደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡ በዚህም የኦርቶዶክስ ክርስትና እና የእስልምና ተከታዮች ምእመናን ይዘዋቸው የኖሩትን የተወራረሱ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት አግዞአል” ሲሉ አጥኚው አበክረው ተናግረዋል፡፡

ክርስቲያን ነገሥታት፣ አሕመድ ኢብን-ኢብራሂም (ግራኝ አሕመድ) እና የኢትዮጵያ  ታሪክ (Apologetic Re-interpretation)

በዚህ ጥናት ውስጥ የክርስቲያን ነገሥታት በንግሥና ዘመናቸው የነበራቸው ሥርዓተ መንግሥት፣ የአመራር ጥበብ፣ ከሚመሩት ሕዝብ ጋር ያላቸው መስተጋብር መነሻ ምክንያታቸው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያለው ቢሆንም እንደሰው የሚሠሯቸው መልካምም ሆነ መልካም ያልሆኑ ጎኖች እንደሚኖሯቸው አጥኚው በስፋት አብራርተዋል። ሆኖም ግን በንግሥና ዘመናቸው የሚነሡ ተገዳዳሪ ኃይላትን ሲፋለሙና ሲዋጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ የጦር ታሪካቸው የሃይማኖታቸው አስተምህሮ ተደርጎ መቆጠሩ ትክክል አለመሆኑን ተገልጿል። ሃይማኖታቸው ጠላትህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ትምህርት የሚሰጥ እንጂ ለጦርነት የሚጋብዝ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በማስቀመጥ አስረድተዋል። በተለይ አሕመድ ኢብን ኢብራሂም በተለምዶ አጠራሩ ግራኝ አሕመድ እስላማዊ ሥርዓተ መንግሥት ለመፍጠር በከፈተው ጦርነት በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ያወደመ፣ ቅዱሳት መካናትን ያቃጠለ፣ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ደብዛቸው እንዲጠፋ ያደረገ መነሻው ምክንያት ‘ሐበሾችን አትንኩ’ የሚለውን የነቢዩ መሐመድን መመሪያ በተለያዩ አረዳዶች በመተርጐም ለጦርነት መነሣቱ ተጠቅሷል።

ዕቅበተ እምነታዊ መንገዶች

የጥንት ቤተ ክርስቲያን ዕቅበተ እምነታዊ መንገዶች የውጪና የውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም ረገድ ዓይነተኛ ድርሻ እንደነበረቻው እንዲሁም አማንያኑን በማኅበራዊ ኑሯቸው የሚታመኑለት በልባቸው የሚያኖሩት ህግ እንዲኖራቸው አግዟል። በተጨማሪም የቤዛንታይን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የያዙት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ዕቅበተ እምነታዊ መመሳሰል እንዳለው ተገልጿል። ለምሳሌ እስልምና ነገረ መለኮት፣ ማኅበራዊ፣ አስተዳደራዊ መሰል ጉዳዮችን የያዘ መሆኑ በምእመናኖቻቸው ዘንድ ለሚኖረው ማኅበራዊ ግንኙነት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚችል Bavinck, J. H. Introduction to the Science of Missions. Grand Rapids, (MI: Baker Book House, 1960), 149 በመጥቀስ አስረድተዋል።

ከዚህ አኳያ የተለያዩ የማሳሳት እና የማጭበርበር (Deception) መንገዶች ሊከሠቱ ስለሚችሉ በሚገባ በመመርመር ማጤን ያስፈልጋል። የሚፈልጉትን ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቁርዓን በመጥቀስ፣ አመክንዮ ተቃርኖዎችን በማቅረብ፣ ግራ ዘመም ጸሓፊዎችን በመጥቀስ የማሳሳትና የማጭበርበር ሥራ የሚሠሩትን አጥብቆ መመርመር እንደሚገባ ብሎም ከእስልምና ተከታይ ወንድሞቻችን ጋር የሚኖረን ተግባቦት የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ፍጥረታት እንዲሁም እነርሱ ውስጥ ስለሚገኙ እውነታዎችን በመግለጽ፣ በማክበርና በመውደድ ሊሆን እንደሚገባ በስፋት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ይህም ምእምናንን ከመጠበቅ አኳያና ትምህርተ ወንጌልን ለማዳረስ ከሚፈጥረው ዕድል አንጻር አስፈላጊነቱ ከፍተኛ እንደሆነ አጥኚው ገልጸዋል።

ተግዳሮቶችና ዕድሎች

ዕቅበተ እምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉ በጥናቱ የተዳሰሱ ሲሆን ከእነዚህም ጥቂቶቹ በምዕራቡ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጥንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሠሩ ጥናቶች ክርስትናን ለመተቸት ማዋል፣ ሃይማኖታዊ ትችት፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳችን መቀላቀል ለአብነት ተጠቅሰዋል። ተግዳሮቶች ያሉትን ያህል ዕድሎችም እንዳሉት አጥኚው ጠቁመዋል። ከእነዚህም ሃይማኖታዊና ባህላዊ ውርርሶች እንዲሁም የጋራ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተጠቅሰዋል። በአጠቃላይ ጥናቱ በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እና በእስልምና መካከል ስላለው ታሪካዊና አሁናዊ መስተጋብሮች ያሏቸውን መልክ በጥልቀት የዳሰሰ ለቀጣዮች ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶችም ወንድማማችነትንና አብሮነትን የሚያዳብሩ መስተጋብሮችን ያመለከተ ነው፡፡