‹‹እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል›› (መዝ.፱፥፯)

መምህር ሃይማኖት አስከብር
ግንቦት ፲፩ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው አምላካችን እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ በምድር ላይ ያሉ የምናያቸው አስደናቂና አስገራሚ የምንላቸው ነገሮች ሁሉ ያልፋሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን እነዚህን ሁሉ አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፡፡‹ ‹‹እምቅድመ ዓለም ወእስከለዓለም ሀሎ እግዚአብሔር በመንግሥቱ፤ ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በመንግሥቱ አለ›› እንዲል ቅዳሴ::

ለባሕርዩውም ኅልፈት ውላጤ ሞት የለበትም፤ ሁሉንም አሳልፎ ይኖራል እንጂ አያልፍም፤ ከሰማይ እስከ ምድር ያሉት የሚታዩት አስደናቂና ግሩማን ፍጥረታት ያልፋሉ፤ ያረጃሉ፤ ይለወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለዚህም ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ‹‹ወግብረ እደዊከ እማንቱ ሰማያት እማንቱሰ ይትኃጉላ ወአንተሰ ትሔሉ ወኩሉ ከልብስ ይበሊ ወከመ ሞጣሕት ትዌልጦሙ ወይትዌለጡ አንተሰ አንተ ክመ ወዓመቲከኒ ዘኢይኅልቅ፤ ሰማያት የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱ ግን ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጎናፀፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ትለውጣቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዓመቶችህ ከቶ አያልቁም›› በማለት ልበ አምላክ ዳዊት የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አምላክነት እንዲህ ተናግሯል፡፡ (መዝ.፻፩፥፳፮)

ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ ላይ ይህን ቃል አጽንዖት ሰጥቶ ሲያስተምር የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ አምላክነት ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትክ፤ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም  ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደልብስ ያረጃሉ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ዕብ.፩፥፲) ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ጳውሎስ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ስለ እግዚአብሔር ዘለዓለማዊነት ተናግረዋል፡፡ እግዚአብሔርም ዘለዓለማዊ አምላክ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ለዚህም በምድር ላይ ያሉት አስፈሪና ግሩማን የምንላቸው ያልፋሉም አልፈዋልም፡፡ ይህችን ዓለም በሥልጣናቸው እና በጉልበታቸው ተመክተው እንደ ገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው የገዙአትም ሄደዋል፤ ሙተዋል እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል፡፡

እነ ፈርኦንም አልፈዋል፤ በእስራኤል ላይ መከራና ሥቃይ ያደረሱ ብዙዎች ሞተዋል፤ እነ ዖዝያን እግዚአብሔርን ረስተው ሥልጣናቸውን እና ጉልበታቸውን ትምክህት አድርገው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ደፈሩ፤ በዚህን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ መናገር እያለበት ዝም አለ፤ ከማይሞተው እግዚአብሔር ይልቅ የሚሞተው ዖዝያንን ፈርቶ ዝም አለ፤ ከዘለዓለማዊው እግዚአብሔር ጊዜያዊው ባለሥልጣን ዖዝያን ኢሳይያስን አስፈራው፤ ዖዝያን ሲሞት እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም አለ፡፡

ነቢዩ በመጽሐፉ ላይ ሲገልጽ ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት በማለት የተናገረውም ለዚህም ነው፡፡ (ኢሳ.፮፥፩) በዙሪያው ያሉ ኪሩቤና ሱራፌል ክንፎቻቸውን በመዘርጋት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ከክብርህ ትሞላታላህ›› እያሉ ያመሰግናሉ፡፡

እግዚአብሔርስ ለኢሳይያስ ለምን ተገለጸለት?

፩. ኢሳይያስ ዖዝያንን መምከር መገሥፅ ሲኖርበት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሲዳፈር አፍሮ ፈርቶ ሳይመክረው ሳያስተምረው ቀረ፤ ‹‹ያ የፈራኸው ያፈርከው ንጉሥ አለፈ፤ ሞተ፤ እኔ ግን በባሕርዬ ሞት በመንግሥቴ ኅልፈት የለብኝም፤ በዘባነ ኪሩብ ስወደስ ስመሰገን እኖራለሁ›› ሲለው ነው፤ ‹‹አንተ ግን የፈራኸው ያፈርከው ሞተ›› ዖዝያን የሚሞት ንጉሥ እንደሆነ ሲያስረዳው እግዚአብሔር በዙፋኑ ተገለጸለት፡፡

፪. እርሱ በሰማያውያን ኪሩቤል ላይ የሚመሰገን አምላክ እንደሆነ ሲገልጽለት ነው፡፡ ኢሳይያስ መናገር ሲኖርበት ዝም ብሏል፤ እርሱ ግን በሰማያውያን ኪሩቤል ያለ ድካም የሚያመሰግኑት እንደሆነ ሲገለጽለት ነው፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‹‹እኔ ፊተኛ ነኝ እኔ ኋለኛ ነኝ›› ከእኔ ሌላ አምላክ የለም፤ (ኢሳ.፵፬፥፮) ስለዚህም ለዘለዓለም ያለው የሚኖረው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ታዲያ ‹‹እግዚአብሔር በባሕርዩው ሞት ኅልፈት የለበትም›› ካልን ስለ ምን ሞተ ተነሣ ዐረገ እያልን እንናገራለን ቢሉ እውነት ነው፤ በአምላክነቱ በጌትነቱ በባሕርይ ፈጣሪነቱ ሞት ኅልፈት ውላጤ የለበትም፡፡ ነገር ግን ሞት የማይገባው ጌታ እኛን ከሞትንበት ያነሣን ዘንድ የሚሞት ሥጋን ተዋሕዶ ሰው በመሆኑ በሥጋ ሞተ፤ ተነሣ፤ እንላለን፡፡ የእኛ የሰዎችንም ባሕርይ ባሕርይ ስላደረገ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ቆጠርንለት እንላለን እንጂ በባሕርይ አምላክነቱስ የማይሞት ዘመን የማይቆጠርለት አምላክ ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ በሥጋ ሞተ፤ በባሕርየ መለኮቱ ግን ሕያው ነው ብሎ ተናግሯል፡፡ (፩ጴጥ.፫$፲፰) ይህም ሟች ሥጋን ቢዋሐድም የማይሞት ዘለዓለማዊ አምላክ እንደሆነ ህያው ነው ብሎ ተናገረ፤  ለዚህም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንደ ሰውነቱ ሞቷልና ይገንዙት ነበር፤ እንደ ዘለዓለማዊ አምላክነቱ ግን ያናግራቸው ነበር፤ ምክንያቱም የማይሞት አምላክ ነውና፡፡ ታዲያ የማይሞተው አምላክ የሚሞት ሥጋን ተዋሕዶ ሟች ሰውን ሕያው አደረገው፤ አንድም በስውር የገባ ሰይጣንን በስውር ድል ይነሣው ዘንድ ሰይጣን አዳም ድል ሲነሳው በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ ነበርና እንዲሁም ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሕያው ያደርገው ዘንድ የሰውን ሥጋ ለበሰ፡፡ ‹‹ወከመ ተኃብአ ሰይጣን በጉሕልቱ ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በተሰውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድኅነ፤ሰይጣን በስጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን እንዳሳተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም በሥጋ ብእሲ ተሰውሮ መጥቶ አለምን እንዳዳነ›› እንዲል፤ (ትርጓሜ ወንጌል ገጽ ፳፰)

ስለዚህም እግዚአብሔር ሰው መሆኑ በስውር የገባውን ሰይጣን አስወጥቶ ያድነን ዘንድ የሚሞት ሥጋን ተዋሐደ፡፡ በዚህም ምክንያት በሥጋ ሞተ፤ ተነሣ፤ ዐረገ፤ እያልን እንናገራለን እንጂ እርሱስ ሞት የሌለበት ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፡፡ ‹‹የወደቀውን የሰውን ልጅ ያነሣው ዘንድ እርሱ ዝቅ አለ፤ ገዳይ ሞትን ይገለው ዘንድ የማይሞተው እግዚአብሔር ሞተ›› ተብሎ ተነገረለት፡፡ በሞቱ ሞትን ገድሏልና ሰይጣንን ድል ነሥቷልና፤ እግዚአብሔር ሰው በመሆኑ ሰይጣን ግራ ገብቶት ነበር፤ ግራ የገባውም እንደ ሰውነቱ እያየ ድል ይነሣው ዘንድ ይቀርብ ነበር፤ ግን ድል ተነሥቶ ይመለስ ነበር፤ እራሱ ሰይጣን እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ‹‹ይህ ማነው? ሥጋ ለብሶ ድል የነሳኝ ያሸነፈኝ›› እያለ ይናገር ነበር፡፡ ዛሬም የሰይጣን የግብር ልጆች ዘለዓለማዊ አምላክነቱን ረስተው ሰው ሆኖ መታመም መሞቱን አይተው እንደ ፍጡር ለመቁጠር ያስባሉ፤ እርሱስ ሞትን ሊገድል የሞተ እንጂ ፍጡር አይደለም፤ ቅዱስ ዮሐንስም ስለሞተው ክርስቶስ ዘለዓለማዊ አምላክነቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹የነበረውና ያለው የመጣው እና የሚመጣው ሁሉንም የሚገዛ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ›› ይላል፤ (ራእ.፩፥፰) በማለት ዘለዓለማዊ አምላክ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ኪሩቤልም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ አምላክ›› እያሉ ቀንና ሌሊት ያመሰግኑታል፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለምም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ (ራእ.፬፥፰፰)

ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ የዘለዓለማዊው አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን!