‹‹እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል›› (መዝ.፯፥፱)

መምህር ሃይማኖት አስከብር

ሚያዚያ ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል›› በማለት አስተምሯል፡፡ (መዝ.፯፥፱) ከዚህም ቃል እንደምንረዳው አምላካችን የሚሣነው ነገርም ሆነ ከእርሱ የሚሠወረውም ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ሁሉንም ሳንነግረው የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ ያሰብነውን ብቻም ሳይሆን ገና ያላሰብነውን እግዚአብሔር ያውቃል፡፡

በሕይወታችን ውስጥ በጎም ሆነ ክፉ የምናደርገው ሁሉ ከእግዚአብሔር አይሠወርም፡፡ ተግባራችን በሰው ፊት እንዲታይ ወይንም እንዳይታይ ብለን ሳይሆን አምላካችን እንደሚያይና እንደሚያውቅ በመረዳት በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ተሠውሮ የማይገለጥ ነገር እንደሌለ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነግሮናል፡፡ ‹‹እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሠት ወአልቦ ኅቡእ ዘኢይትዓወቅ፤ የማይገለጥ የተከደነ የለምና፤ የማይታወቅም የተሠወረ የለምና›› እንዲል፤ (ማቴ.፲፥፳፮)

ተሠውሮ የሚቀር የማይታወቅ ነገር የለም፤ የምንሠራው ሥራ መንፈሳዊም ሆነ ክፉ ነገር እንደማይታወቅ አስበን የምናደርገው ሁሉ ከእኛ ቀድሞ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይደርሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የምናደርጋቸው መንፈሳዊ ሥራዎች በሰዎች ዘንድ ካልታየ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚደርስ አይመስለንም፡፡ መልካም ስናደርግ ሰዎች ካላጨበጨቡልን እግዚአብሔር የተቀበለን አይመስለንም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አንተ ግን ስትጸልይ ቤትህን ዘግተህ ጸልይ፤ በስውር ለሚያይህ አባትህ ንገረው፤ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሀልና፡፡›› (ማቴ.፮፥፮)

ስለዚህም የምናደርጋቸውን ሁሉ አግዚአብሔር ክፉም ይሁን በጎ የሚያውቅ አምላክ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ የእኛን ልቡና እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያውቀው ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹የሰው ልቡ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደመንገዱና እንደ ሥራው ሁሉ ፍሬውን እሰጠው ዘንድ ልቡናውን እመረምራለሁ፡፡›› (ኤር.፲፯፥፲)

እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን ልቡና መርምሮ እንደሥራችን እንደሚከፍለን ነቢዩ ገልጾልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን በጎም ይሁን ክፉ ሥራ የሠራነውን ዐውቆ እንደሥራችን እንደሚከፍለን እንደዚህ ብሎ ተናግሯል፤ ‹‹ወይፈድዮ ለኲሉ በከመ ምግባሩ፤ ለሁሉም እንደየሥራው ይሰጠዋል፡፡ የእያንዳንዳችን ልቡና መርምሮ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ አምላካችን የሚወደውን ሥራ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እርሱ አያውቅም ብሎ በማሰብ  ክፉ መሥራት አያየኝም ብሎ ኃጢአት መሥራት እንደሌለብን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡

ከእግዚአብሔር ምንም ነገር የሚሰወር እንደሌለ ወንጌላዊ ሉቃስም ሲጽፍ እንደዚህ እያለ ይገልጻልናል፡፡ከክፉ መዝገባችን ክፋት ከመልካም መዝገባችን መልካምነት እንዳለ እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ሲገሥፃቸው እንዲህ ያለው ለዚህም ነው፡፡ ‹‹ራሳችሁን በሰው ፊት የምታመጻድቁ እናንተ ናችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልቡናችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፡፡›› (ሉቃ.፲፮፥፲፭)

ከላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ ጊዜ ክብር ከእግዚአብሔር ለማግኘት ከምንጥረው በላይ በሰው ዘንድ እንድንከብርና እንድንወደስ እንሽቀዳደማለን፡፡ አገልግሎታችን ሰው ካልሰማው ጸሎታችን በሰው ዘንድ ካልታየ ያገለገልን፣ የጸለይን የማይመስለን፣ ስጦታችንን እልል ብለው ካልተቀበሉን እግዚአብሔር የተቀበለው የማይመስለን፣ የማስመሰል ጸሎተኞች እጅግ እየተበራከትን መጥተናል፡፡ ከእግዚአብሔር ክብር እናገኛለን ስንል ክብራችን ግን በሰው ዘንድ ቀረብን፡፡ ከአምላካችን ዘንድ ግን ክብራችንን አጣነው፤ በምድራዊ ዋጋ ቀይረን ከንቱ ውዳሴን በመሻት የክርስቶስን ዋጋ አጣን፡፡ ከአባቶቻችን ታሪክ እንደምንረዳው የእነርሱ ጸጋ ሲበዛላቸው በሰው ዘንድ ቅድስናቸውና ክብራቸው እንዲገለጽ አይፈልጉም ነበር፡፡ ይልቁንም ክብራቸው እንዳይታወቅባቸው ከሰው ዘንድ ይሸሹ ነበር፤ ብዙ ሠርተው እንዳልሠሩ፣ ብዙ ደክመው እንዳልጀመሩ በማመን ካለፈው የበለጠ ወደፊት ይተጉ ነበር፡፡ በሠሩት ከመመጻደቅ ይልቅ ያልሠሩትንና ገና የቀራቸውን በማሰብ ተግተዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ በርቱ፡፡ ይህንንም ብታደርጉ ከቶ አትሰነካከሉም›› በማለት አስተምሯል፡፡ (፪ ጴጥ.፩፥፲) በዚህ ቃል መሠረት ጻድቃን አባቶቻችን ወደፊት ስለሚሠሩት ሥራ ይተጉ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ትንሽ ሠርተን ብዙ እንደሠራን፣ ትንሽ ሩጠን ብዙ እንደሮጥን በማድረግ ብዙዎቻችን ራሳችን እየተመጻደቅን የእግዚአብሔርን በረከት አጥተናል፡፡ አባቶቻችን ሥራቸውን ይሠሩ የነበረው የልቡናቸውን መሻት ከሚያውቀው ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እና በመጸለይ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከማስመሰልና ከታይታ ይልቅ በተግባር በመግለጽ ነበር፡፡ እኛ ግን በተግባር ከመኖር ይልቅ ለማስመሰል እና ለታይታ እናደርገዋለን፡፡ አባቶቻችን የድርሻቸውን ከሠሩ በኋላ የቀረውን ለእግዚአብሔር ይሰጡ ነበር፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ነህና እንደፈቃድህ ይሁን›› በማለት ይጸልዩ ነበር፡፡ (የሐ.፩፥፳፬)

ስለዚህ እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን ልቡና እንደሚያውቅ በመረዳት ከማስመሰል ይልቅ በእውነት በመኖር ከኃጢአት በመራቅ እና ልቡናችንን በማንጻት ለእግዚአብሔር የተመቸ ማደሪያ እንሆን ዘንድ ይገባናል፡፡ በኃጢአት ያለ ልቡና ከእግዚአብሔር የራቀ ነው፤ ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹ስለሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደእሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋው ሳይኖር እንዳይቀጣጠል ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤ የልቡናችሁን ሸለፈት አስወግዱ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ኤር.፬፥፬) ስለዚህም እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን ልቡና መርምሮ የሚያውቅ በመሆኑ በኃጢአት በማስመሰል የተሸፈነ ልቡና እንዳይኖረን ልቡናችንን በመንፈሳዊ ሕይወት ልንጠብቀው ይገባል፡፡