እየተሰማ ያለው የሞትና የእልቂት ዜና የብዙዎችን ልብ የሚሰብር፣ የሰላሙን አየር የሚያውክና ቤተ ክርስቲያንን የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል፡፡” (ያዕ.፫፥፲፰)

  • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
  • የተወደዳችሁ ምእመናንና ምእመናት

በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው ጦርነት ቆሞ በእግዚአብሔር ቸርነት የሰላም አየር እየነፈሰ ያለበት ወቅት በመሆኑ፤ ሰላሙ ከፍጻሜ እንዲደርስ በወቅቱ መልእክታችንን ማስተላለፋችን የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ማለትም በአርባ ምንጭ እሥር ቤትና በዐባያ ወንዝ አካባቢ በእሥረኞች ላይ የደረሰው ግድያ፣ በትግራይ በሽሬ አካባቢ በዓዲ ዳእሮ ከተማ፣ አሁን ደግሞ በምሥራቅ ወለጋና በሆሮ ጉድሩ እየተሰማ ያለው የሞትና የእልቂት ዜና የብዙዎችን ልብ የሚሰብር፣ የሰላሙን አየር የሚያውክና ቤተ ክርስቲያንን የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሆኑም ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ በእጅጉ የሚያስፈልገው በፍቅር፣ በሰላምና በመከባበር መኖር እንጂ በመገዳደል ምንም ዓይነት ትርፍ አይገኝበትም፡፡

ይልቁንም ደግሞ በታሪክ የሚያስወቅስ፣ በሞራል የሚያስጠይቅና በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ተግባር በመሆኑ በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ መንግሥትም በመላው የሀገራችን ክፍል ሰላም እንዲሰፍን ሕግ የማስከበር ተግባሩን እንዲያከናውን እና መላው ሕዝበ ክርስቲያንም ሀገራችን ፍጹም ሰላም እንድትሆን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንዲማጸን አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአምስተኛው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ዕረፍት የተሰማንን ኀዘን እየገለጽን፣ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት እንዲያሳርፍና ለመላው ሕዝበ ክርስቲያንም መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ የሞቱ የወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን! አሜን፡፡

                            አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

                       ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ

                     ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

 

ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ..

አዲስ አበባኢትዮጵያ