እንኳን ለበዓለ ትንሣኤ አደረሳችሁ!

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን                                           ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ

በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን                                            በታላቅ ኃይልና ሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን                                                          ሰይጣንን አሠረው

አግዐዞ ለአዳም                                                         አዳምን ነጻ አወጣው

ሰላም                                                                            ሰላም

እምይእዜሰ                                                                     ከእንግዲህ

ኮነ                                                                                  ሆነ

ፍስሐ ወሰላም                                                                   ደስታና ሰላም

‹‹እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም›› (ማቴ. ፳፰፥፮)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሚያዚያ፤ ፳፻፲፬ .

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁ? እንኳን ለዚህ ዕለት አደረሳችሁ! በእግዚአብሔር ቸርነት የጾሙ ጊዜ ተፈጽሞ፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችን ለተበሠረበት ዕለት ደረስን! በቸርነቱ ለዚህ ያደረሰን ፈጣሪ ይመስገን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቤተ ክርስቲያናችን ከትንሣኤ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ ሰላምታ ስንሰጣጥ እንዴት መሆን እንዳለበት ሥርዓትን ሠርታለች፤ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ሰላምታችን ከላይ በገለጽነው መሠረት ነው፤ የጌታችንን ትንሣኤውን፣ እኛም ከሰይጣን ባርነት ነጻ መውጣታችንን እየመሰከርን ሰላምታ እንለዋወጣለን! መልካም!

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ከኃጢአት ነጻ ሊያጣ በፈቃዱ በመስቀል ተሰቅሎ ከሞተ በኋላ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አደረ፤ በሦስተኛውም ቀን አስቀድሞ ንጉሥ ዳዊት በትንቢት  እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ›› እንዳለው በገዛ ሥልጣኑ በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ (መዝ.፸፯፥፷፭)

የጌታችንን መቃብር ለማየት ሄደው ለነበሩ ለነ መግደላዊት ማርያም የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ ሲል ትንሣኤውን አበሠራቸው፡፡ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ መቃብሩን ኑና እዩ›› አላቸው፡፡ (ማቴ.፳፰፥፭)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን አስቀድሞ በነቢያት አንደበት እንዳናገረው በኋላም ራሱ በዚህ ምድር ሲመላለስ በፈቃዱ እንደሚሞትና ሞትንም ድል አድርጎ እንደሚነሣ እንዲህ ብሎ ነበር :: ‹‹የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ለሕዝብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱ፤ ይተፉበታልም፤ ይገርፉትማል፤ይገድሉትማል፤በሦስተኛውም ቀን ይነሣል በማለት በተናገረው መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓርብ በመስቀል ተሰቀለ፤(ማር.፱፥፴፫) ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው በክብር ገንዘውት በመቃብር አኖሩት፡፡

ከዚያም ልጆች አምላክ ነውና በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አበሠረን፤ እኛም ለማንም በማይቀረው የሥጋ ሞት የምንወሰድ ብንሆንም ሕያዋን ሆነን ለመኖር የሚያስችለን የክብር ትንሣኤ እንዳለን መድኃኒታችን አብነት ሆኖናል፤ ይህ በዓል የማይሞተው ስለእኛ  ሞቶ የሞትን ቀንበር ሠብሮ ትንሣኤያችንን ያበሠረበት የደስታ ዕለት ነው፡፡

ልጆች! በዓሉን ስናከብር ካለን ለሌላቸው ወገኖቻችን እያካፈልን ሊሆን ይገባል፤ ደግሞም በጾም ጊዜ ለጸሎት እንተጋ እንደነበረው በዘመነ ትንሣኤም በርትተን ማመስገን አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ደግሞ የራሳቸው የሆነ  መጠሪያ ስያሜ አላቸው፤ በእያንዳንዱ ዕለት የጌታችንን  ውለታውን እያሰብን ሳምንቱን እናዘክራለን፤ እስኪ እንመልከታቸው!

የትንሣኤ ማግት/ ሰኞ ማዕዶት (ሽግግር) ወይም ጸአተ ሲኦል ትባላለች፤ ነፍሳት ከሲኦል እሥራት ነጻ መውጣታቸው፣ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራቸው የሚታሰብበት ዕለት ነው ፡፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ፶፻፭፻ (አምስት ሽህ አምስት መቶ) ዘመን በሲኦል እስራት፣ በጠላት ዲያቢሎስ ግዛት የነበሩትን ነፍሳት ነጻ አውጥቶ አዳምና ልጆቹን ወደ ቀድሞ ርስታቸው የመለሰበት ዕለት መታሰቢያ ነው፤ ይህቺን ዕለት አጥተን የነበረውን ነጻነት ማግኘታችንን፣ ዳግመኛ ልጆች መሆናችንን፣ ሰላም ይናፍቁ የነበሩ አዳምና ልጆቹ ሰላማቸው ታውጆ፣ ጭንቀታቸው ርቆ፣ በደስታ ወደ ገነት መመለሳቸውን እናስብበታልን፡፡

ማክሰኞ /ማግ ሰኞ/ ቶማስ ይባላል፡-ጌታችን መነሣቱን ለሐዋርያተ በገለጸ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና የጌታንን  ትንሣኤ ሲነግሩት ‹‹ካላየሁ አላምንም›› በማለቱ ጌታችን እርሱ ባለበት ዳግመኛ ለሐዋርያ ተገለጸ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስንም ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፣እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንክ እንጂ ያላመንክ አትሁን›› አለው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የእጆቹን ጣቶች ጌታችን በዕለተ ዐርብ ሌንጊኖስ በተባለ ጭፍራ በወጋው ጎኑ ሰደደ፤ የዚህን ጊዜ እጁ ኩምትር አለች፤ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ጌታዬ አምላኬ›› ብሎ መሥክሯል፡፡ የዚህን ድንቅ ተአምራት መታሰቢያ ከትንሣኤ በሁለተኛው ቀን ይታሰባል፡፡ ምንም አንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው በዳግም ትንሣኤ ቢሆንም የሐዋርያው መታሰቢያ ሆኖ ዕለተ ማክሰኞ ቶማስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡(ዮሐ.፳፥፳፯-፳፰)

ረዕቡ ልዓዛር ይባላል፡-አልዓዛር ማለት እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የማርያና የማርታ ወንድም ነው፤ በቢታንን ይኖር የነበረው የጌታችን ወዳጅ አልዓዛር ታሞ ሞተ፤ በዚህን ጊዜ ጌታችን በዚያ ሥፍራ አልነበረምና እንደ አምላክነቱ ባለበት ቦታ ሆኖ የወዳጁ አልዓዛርን መሞት አወቀ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ‹‹ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷልና ላሥነሳው ወደ ቢታንያ እንሂድ›› አላቸው ወደ ቢታንም መጣ፤ ከሞተ ዐራት ቀን የሆነውን አልዓዛርን ከመቃብር አሥነሳው፤ ጌታችን ይህን ድንቅ ተአምር ማድረጉን በዚህ ወቅት ይታሰባል፡፡ (ዮሐ.፲፩፥፩-፵፮)

ሐሙስአዳም ሐሙስ ይባላል፡- አዳም በበደለ ጊዜ በደሉን አምኖ ንስሓ ገባ ተጸጸተ፣እግዚአብሔርን መበደሉንና ትእዛዙን መጣሱን አምኖ ለ፻ (መቶ) ዓመት ሲያለቅስ ኖረ፤ ጠላትም አስጨንቆ ገዛው። ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ፣ሔዋን ዓመቷ ለዲያቢሎስ›› ብሎም የዕዳ ደብዳቤ አጻፋቸው፤ አዳምም ስለበዱሉ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ጌታችንም የአዳምን መጸጸትና መመለስ ተቀብሎለት አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ገባለት፤ ይህም ዕለት በዚህ ቀን ይታሰባል፤ አዳም ሐሙስ መባሉ ለዚህ ነው፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፱ አንድምታ)

ርብ፡- በዚህ ዕለት የሚታሰበው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንደመሠረተ ነው፡፡ በሐዋርት ሥራ ላይ ቅዱስ ሉቃስ ‹‹እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ሾመ›› በማለት እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡(የሐ.፳፥፳፰)  ይህ ዕለት የዚህ መታሰቢያው ነው፡፡

ቅዳሜ ቅዱሳ አንስት ይባላል፤ ከመቶ ሃያው የእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል ሠላሣ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ናቸው፤ የትንሣኤውን ብሥራትም ሰምተዋል  ‹‹..መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ….›› በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ፤ እነሆም ኢየሱስ አገኛቸውና ‹‹.ደስ ይበላችሁ›› አላቸው እነርሱም ቀርበው ሰገዱለት ፡፡….›› (ማቴ. ፳፰፥፭-፱) ከትንሣኤ በዓል በኋላ ያለው ቅዳሜ የጌታችንን ትንሣኤ ያበሠሩና የመሠከሩ ቅዱሳን አንስት የሚታሰቡበት ዕለት በመሆኑ ቅዱሳት አንስት ይባላል፡፡

እሑድ ዳግም ትንሣኤ፡- ጌታችን ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ቅዱስ ቶማስ ግን ባልነበረበት ተገልጦ ስለነበር፤ ቅዱስ ቶማስ ባለበት በዚህች ዕለት በዝግ ቤት ሳሉ ተገልጾላቸዋል፤ ‹‹..ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን››  አለው፡፡ ቶማስም ‹‹ጌታዬ አምላኬም››  ብሎ መለሰለት፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፯-፳፰)) በዚህም የተነሣ ይህ ዕለት ዳግም ትንሣኤ ተብሏል፡፡

እንግዲህ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህን እያሰብንና መልካም ሥራ እየሠራን በዓሉን እናክብር! ቸር ይግጠመን ይቆየን !!!

 ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!