“እናንተ ኃጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሀሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ” (ያዕቆብ ፬፥፰)

ሰዎች በተፈጥሮአቸው ፍቅርንና ሰላምን የሚሹ በመሆናቸው ከማንነታቸው (ከክርስቲያንነት) የራቁ ቢሆኑ አንኳን እነዚህን የእግዚአብሔርን ፀጋዎች ያጡ እንደሆነ መኖራቸው ትርጉም ያጣል፡፡ ፍጥረት መሆናቸውን ባይዘነጉም ለምድራዊ ድሎት እራሳቸውን በማስገዛታቸው ሀብትና ንብረት እንዲሁም ሥልጣንን በማካበትና ለትዕቢት በመገዛት ፈጣሪያቸውን ይረሳሉ፡፡ ያካበቱት ዓለማዊ ስኬትም ሆነ ተድላ ግን ውስጣቸውን ሁሌም ሰላምና ፍቅርን ያሳጣዋል፤ ሀብትና ንብረታቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምና አይባረክላቸውም፤ አይበረክትላቸውምም፤ እነርሱ ከፈጣሪያቸው የራቁ ናቸውና፡፡

“በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ምኞታችሁ አይደለምን? ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም። ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና” እንዲል። (ያዕቆብ ፬፥ ፩-፫)

የዘመናዊነት አስተሳሰብ ይህን ትውልድ ለሳይንስ ተገዢ በማድረጉ መኖራቸው በፋጣሪ ቸርነት መሆኑን የዘነጉት ይመስል  የየዕለት የግል ተግባሮች የሚያከናውኑትም በራሳቸው ትምክህተኝነት ሆኗል፤ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን ማለት ግን ይገባችኋል” (ያዕቆብ ፬፥፲፫-፲፭) አንደተባለው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል በመተላለፍ ይኖራሉ፡፡

ማኀበራዊና ሀገራዊ ችግሮችንም መፍታት የሚችሉት ቴክኖሎጂ ባፈራቸው ግኝቶች እንደሆነ ያምናሉ፤ በመጽሐፍ ቅዱስም እንደተባለው  “…..ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል” (ያዕቆብ ፬፥፭)

በዓለማችን እየተስፋፋ ያለውን አዲሱ ወረርሽኝ ኮሮና በይበልጥ ይህን ግልጽ እንዳደረገው የማይታበል ሀቅ ነው፤ መድኃኒት ያልተገኘለት መቅሰፍቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የአደጉ ሀገሮቸን ዜጎች ሕይወት በማጥፋቱ የሕክምና ባለሙዎች ሲረባረቡ ከርመዋል፡፡ ሆኖም መከላከያ መንገዱን ማሳወቅ እንጂ ፈውስ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በየትኛውም ዘመን እንደዚህ ዓይነት ተዛማች በሽታ በተከሰተ ቁጥር ሕዝብ በኃጢአትና በጥፋት አዘቅት\ ውስጥ መግባቱን ወንጌል ያስረዳል፡፡ ‹‹ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ›› ብሏል፡፡ (አሞጽ ፫፥ ፪)

አሁንም ይህ መቅሰፍት የእግዚአብሔር ቁጣ መሆኑን ማመን የማይፈልጉ እና የማያምኑ ሰዎች በርካታ ናቸው፤‹‹ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር›› እንዲል። (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩) እነርሱ ፈውሰ ሥጋም ሆነ ነፍስ እግዚአብሔር መሆኑን ዘንግተውታል፤ ድኀነተ ሥጋም ሆነ ድኅነተ ነፍስ የሚገኘው ግን ከፈጣሪ ዘንድ ነው፡፡

ከክርስትና ሕይወት የወጡና ለሃይማኖታቸው ተገዝተው መኖር ያልቻሉ የስመ ኦርቶዶክሶች ከሕገ እግዚአብሔር የወጡና ትእዛዛቱን የሚተላለፉ ሆነዋል፤ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጪ ስለሚያደርጋቸው ለክፋት ሥራ እንዲሁም ለጠላት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የሚሠሩት ኃጢአት በመብዛቱ ለባዕድ ነገርና ለጠላት እንዲገዙ አድርጓቸዋል፡፡

በሌሎች ዓለማት የሚተገበሩትን የንጽሕና መጠበቂያ መመሪያዎችና የበሽታው መከላከያዎች ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ የሥጋዊ ንጽሕናን በመጠበቅ ብቻ ከበሽታው ሊድኑ እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን በእንደዚህ ዓይነት የመከራ ወቅት ላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ ወደ ፈጣሪ መጮህና መማጸን እንዳለባቸው ታዘክራለች፤ ጾሎት፣ ጾም እንዲሁም ምህላንም ታውጃለች፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ገዳማት የሚገኙ ገዳማውያን ሱባኤያትን እንዲይዙም ታሳስባለች፡፡ ወደ እግዚአብሔር ዳግም እንድንመለስና ቁጣውን ወደ ምሕረት እንዲለውጥልን አጥብቀን መጸለይ እንደሚገባ ትመክራለች፡፡ ይህም እንዲተገበር በቋሚ ሲኖዶስ የሚወጡ መግለጫዎች በተደጋጋሚ እያሳወቁ ቢሆንምና ምእመናኑም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በማያፈርስ መልኩ ሥርዓተ አምልኮን ለመፈጸም እየሞከሩ ቢሆንም ከአምላካችን ምላሽ እንድናገኝ ሙሉ ልባችንን ለእምነታችንና ለሃይማኖታችን መስጠት አለብን፡፡

በእርግጥ ካለንበት ሁኔታ አንጻር የተላለፉትን መመሪያ ለመተግበር የእኛ ትኩረትና ጥንቃቄ ቢያስፈልግም ጾሎታችንን፤ ጾማችንን፤ ምህላችንና ሲባኤያችንን አምላክ የሚቀበለን በሙሉ ልብ ለእርሱ ተግዝተን ስናመልከው ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስም “እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል” ተብሏልና። (ያዕቆብ ፬፥፯-፲)

እግዚአብሔር አምላክ ከመዓት ወደ ምሕረት ይመለስልን፤አሜን