‹‹እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ›› (ሉቃ.፳፬፥፵፱)

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
ሰኔ ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የሰላም አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያርግበት ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› በማለት ከነገራቸው በኋላ እንዳረገ ቅዱሱ መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፵፱) ጌታችን ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ፲፪ቱ ደቀ መዛሙርት፣ ፸፪ቱ አርድእት፣ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በጽርሐ ጽዮን በቅዱስ ማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በጾምና በጸሎት ይተጉ ጀመር፡፡ በዕርገቱ ዕለትም ለሐዋርያቱ በገባላቸው ቃል መሠረት ተሰብስበው በአንድነት ሳሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በዐሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ዕለት ጧት በሦስት ሰዓት እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ መንፈስ ቅዱስም ባደላቸው መጠን በየሀገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መናገር ጀመሩ። (ሐዋ.፪፥፩-፬) ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ ‹‹በዓል ጰራቅሊጦስ›› በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጎልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች) ሆነዋል፤ ፍርሃት ከውስጣቸው ተወግዶ መንፈሳዊ ድፍረት አግኝተዋል፤ ጽኑዓን ሆነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል፡፡ ቀድሞ ይናገሩት ከነበሩት ከዕብራይስጥ ቋንቋ በተጨማሪ ፸፪ ቋንቋዎች ተገልጸውላቸው ምሥጢራትን ተርጉመዋል፡፡ የሀገሩ ሁሉ ቋንቋ የተገለጸላቸውም ሁሉንም በሀገሩ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ነው፡፡ ከተለያየ ክፍለ ዓለም የመጡም ነበሩ፡፡ ሕዝቡም ‹‹እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንዴት የእኛን ሀገር ቋንቋ ሊናገሩ ቻሉ?›› በማለት ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው ‹‹እንጃ ይህ ምን ይሆን?›› ተባባሉ፡፡ ከአይሁድ ወገን አንዳንዶቹም ሐዋርያትን ‹‹ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ሰክረው የሆነ ያልሆነውን ይቀባጥራሉ›› ይሏቸው ነበር፡፡

ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሐሳባቸውን በመንፈስ ቅዱስ ዐውቆ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፤ ‹‹የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ! ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን! ቃሎቼንም አድምጡ፡፡ ሰክረዋል የምትሉ ለእናንተ እንደመሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደለም፡፡ ጊዜው ማለዳ፣ ሰዓቱም ገና ሦስት ሰዓት ነውና፡፡›› (የሐዋ.፥፪፥፲፬-፲፭) ዳሩ ግን በነቢዩ ኢዩኤል ‹‹እግዚአብሔር ይላ፥ በኋለኛይቱ ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ህልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮች ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡ ድንቆችንም በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር ደምም፣ እሳትም፣ የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ የታወቀችዋም ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል፤ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፡፡›› (ኢዩ.፪፥፳፰-፴፪) ይህም ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ‹‹ይህንን ድንቅ ተአምር ያደረገው እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› በማለት ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ ምሳሌ የመሰሉለት አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም በክብር በምስጋና መጥቶ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈረድ መሆኑን እንደሚመሠክሩ በአይሁድ ፊት ልብን የሚመስጥ ትምህርት ሰጠ፡፡
በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት ‹‹ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?›› አሏቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይሠረይ ዘንድ ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው፤ ስለዚህ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ዓለም አድኑ›› ብሎ መከራቸው፡፡ በዚህ ቀን ሦስት ሽህ ሰዎች አምነው ተጠመቁ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፡፡ (ሐዋ.፪፥፩-፵፩)ይህም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ያደረባቸው የማሳመን ጸጋና ተአምራትን የማድረግ ኃይላቸው እንደ በዛላቸው ያመላክታል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ይህ የጰራቅሊጦስ በዓል በግሪኮች ቋንቋ ጰንጠቆስጤ ማለት ሲሆን ትረጉሙም ‹‹ሃምሳኛ›› ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሃምሳኛው በዓለ ሃምሳ (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠበት፤ ብዙ ሽህ ምእመናን የተገኙበት ዕለት በመሆኑ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል በሚገባ አነጋገር ‹‹የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን›› ብሎታል፡፡ ይህ በዓል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዓልም (በዓለ ሰዊት) ይባላል፡፡ እስራኤል የነጻነት በዓላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዓለ ፋሲካ ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው ይሰነብታሉ፡፡ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊትን (የእሸት በዓላቸውን) ያከብራሉ፡፡ በሀገራቸው ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወቅት በሀገራችን ከመስከረም እስከ ኅዳር እንዳለው የእሸት ወራት (የጸደይ ወራት) ነውና። የእሸት በዓላቸውን የሚያከብሩት በኦሪት ዘሌዋውያን (ምዕራፍ ፳፫፥፲-፲፯) ላይ በታዘዘው መሠረት ማንኛውም እሥራኤላዊ ገበሬ ከዘራው ሁሉ በያይነቱ እሸቱን ቆርጦ ተሸክሞ ወደ ምኵራቡ ይመጣል፡፡ በቤተ መቅደስ የሚያገለግለው ካህን ተቀብሎ ባርኮ ጸልዮ የሚጠበሰው እየተጠበሰ የሚታሸው እየታሸ በማኅበር አንድነት ‹‹ቀዳምያት›› (የመጀመሪያው) ይባላል፡፡ ከማንኛውም በረከት የመጀመሪያው እግዚአብሔር ፊት መቅረብ፣ ለእግዚአብሔር መስጠት እንዳለበት ታዟልና፡፡

በዓለ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ የሚወርድባት ኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ናት። ለዚህም ነው ዘወትር በቅዳሴ መጀመሪያ ላይ ‹‹ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? ይህች ሰዓት ምን ያህል የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት›› የሚባለው። ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው ለእኛም እንዲወርድልን ሁል ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሄድና መገኘት ይገባል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ተለይቶ ጽድቅ የለም። ቤተ ክርስቲያን የመንግሥተ ሰማያት በር ናት። በኦሪት ዘፈጥረት ላይ ‹‹ይህች የሰማይ ደጅ ናት›› እንደተባለው ነው። (ዘፍ.፳፷፥፲፯) በዚህ መሠረት ለእኛም በ፵ ቀንና በ፹ ቀን የተሰጠን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅና ጧት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ይገባል፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ዕርገት እስከ ኀምሳኛው ቀን ቅድመ ጰራቅሊጦስ (ለ፲ ቀናት) ድረስ በጾምና በጸሎት ቆይተዋል፡፡ እነዚህንም ፲ ቀናት የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እያለ ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤… ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› ብሎ የሰጣቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፲፮-፲፰) ይህንን ጾም በመጾም ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ራሳቸውን አዘጋጅተውበታል፡፡ ዛሬም ካህናት ክህነት ከመቀበላቸው በፊት፣ አዳዲስ ተጠማቂዎችም ከጥምቀት በፊት እንዲሁም ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበላቸው በፊት የሚጾሙት ይህንን አብነት አድርገው ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለመቀበል ራስን በጾምና በጸሎት ማዘጋጀት ያስፈልጋልና፡፡

እንግዲህ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላም ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገውታል፡፡ እነርሱ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ (ድኅረ ጰራቅሊጦስ) የጾሙት ስለ ሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ጾሟልና እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ ማግሥት ዕለተ ሰኞ ጀምሮ ሲሆን ፍፃሜው ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም ዐደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበት ዕለት (ሐምሌ አምስት) ድረስ ነው። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ የሐዋርያትን በረከትን ያገኙ ዘንድ ከሰባቱ አጿማት አንዱን ‹‹ጾመ ሐዋርያትን›› ሁሉም እንዲጾመው ዐውጃለች።

በሐዋርያት ጾም የሐዋርያት ክብራቸውና አገልግሎታቸው ይታሰባል፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመላበስ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታችንን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምእመናን እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ እያሰብን በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ የመታዘዝ ፍርሃት የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ፣ የመታዘዝ ፍርሃት የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ ጾምን በመጾም፣ ጸሎትን በመጸለይ ከእግዚአብሔርና በንፁሕ ደሙ ከዋጃት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለንን ፍጹም አንድነት ልናጸና፣ ራሳችንን ከኃጢአት ከበደል አርቀን በመታዘዝ ጸጋ የጾምን በረከት ልንቀበልበት ይገባል፡፡ (ፊልጵ.፪፥፲፪)

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት ይርዳን፤ አሜን፡፡