‹‹እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን›› (ራእ.፪፥፲)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ሐምሌ ፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የክርስትናን ሕይወትና ጉዞ መጀመር ቀላል ሲሆን ዳገት የሚሆነው መፈጸሙ ነው፡፡ ‹‹እስከ ሞት›› የመባሉም ዋናው ምክንያት ይህ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕለተ ምጽአቱ ባስተማረበት የወንጌል ክፍልም ከዚህ ኃይለ ቃል ጋር በእጅጉ አንድ በሆነ መንገድ ‹‹እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል››  በማለት ያስተማረው ትምህርት መፈጸም እንደመጀመር ቀላል እንዳልሆነ የሚያስረዳን ነው፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፫)

ዛሬ በብዙዎቻችን ሕይወት እንደሚስተዋለው ክርስትናችንን የምንገልጥባቸውን አገልግሎቶች፣ አኗኗሮች፣ አካሄዶች ለመጀመር ያህል ልንጀምራቸው እንችላለን፤ በጀመርንበት ልክና ከፍ ሲልም በመንፈሳዊ እድገቶች ቀጥለን ለመፈጸም ግን እንቸገራለን፡፡ በንስሓ ጀምሮ በንስሓ መፈጸም፣ በመንፈሳዊነት ጀምሮ በመንፈሳዊነት መፈጸም፣ በቁርባን ጀምሮ በቁርባን ጸንቶ መፈጸም፣ በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ጀምሮ በዚያው መፈጸምን ተቸግረናል፡፡ ይልቁንም ሐዋርያው እንደመሰከረው በመንፈስ ጀምረን በሥጋ የምንፈጽም ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው፡፡ ‹‹የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከጀምራችሁ በኋላ የሥጋን ሕግ ልትሠሩ ትመለሳላችሁን?›› እንዳለ፡፡ (ገላ.፫፥፫) ይሁዳ በሐዋርያነት ጀምሮ በምንደኝነት፣ ዴማስ በስብከተ ወንጌል ጀምሮ በፍቅረ ዓለም ፈጽመዋል፡፡ (ማቴ.፳፮፥፶፣ ፪ጢሞ.፬፥፲) በመንፈስ ጀምረን በሥጋ፣ በመልካምነት ጀምረን በክፋት፣ በቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን ጀምረን በለዘብተኝነት የምንፈጽም ሰዎችን ዳግም ወደ ነበርንበት ሕይወት መመለስ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይሀን በተመለከተ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲያስተምራቸው ‹‹አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሓ ማደስ የማይቻል ነው” በማለት ተናግሮዋል፡፡ (ዕብ.፮፥፬)

ከጀመርነው መንፈሳዊ ሕይወት ወደ ኋላ ማፈግፈግ ጥፋቱ አደገኛ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በምን ዓይነት መልኩ እንደገለጠው እናስተውል፡፡ ሰው ፈቃደ እግዚአብሔርን ፈጽሞ በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ሊያገኝ የፈለገውን መልካም ነገር ሁሉ ለማግኘት እስከ መጨረሻው መጽናት ያስፈልገዋል፡፡ ልትጾም፣ ልትጸልይ፣ ልትሰግድ፣ ልትመጸውት፣ ልትቆርብ፣ ልታገለግል ትችላለህ፤ በእነዚህ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞዎች ውስጥ በሚገጥሙህ ውጣ ውረዶች ተሸንፈህ እንደ ገና ወደ ኋላ የምትንሸራተት ከሆነ ግን እግዚአብሔርን ታሳዝናለህ፤ ሥጋህንም ነፍስህንም ትጎዳለህ፡፡ ሐዋርያው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች አጽንዖት ሰጥቶ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከልም አንዱ ይህንኑን ነው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል፡፡›› አያይዞም ‹‹ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፤ ሊመጣ ያለው ይመጣል፤ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም›› ይለንና ምን መሆን እንደሚገባን ሲያስተምረን ‹‹እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት አይደለንም›› በማለት በጀመሩት መንፈሳዊ ነገር መጽናት ታላቅ ነገር መሆኑን ይነግረናል፡፡ (ዕብ.፲፥፴፮)

ከብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተማር!

በሰማዕትነት የተደመደመ አገልግሎታቸውን ዘወትር የሰማዕትነት መታሰቢያቸውንም በየዓመቱ ሐምሌ ፭ ቀን በታላቅ ድምቀት ከምናከብርላቸው ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም የምንማረው ትልቅ ትምህርት በመከራ እሳት፣ በፈተና ማዕበል በአገልግሎት ውጣ ውረድ እየተመላለሱ እስከ ፍጻሜ በመንፈሳዊነት ጸንቶ ለክብር መብቃትን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ከጀመሩ በኋላ የማፈግፈግን አስከፊነት ሲገልጽ ‹‹በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋልና፡፡ አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና፡፡ ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል›› በማለት በግልጽ አስተምሮናል፡፡ (፪ጴጥ.፪፥፳፩-፳፪)

የሐዋርያት ልጆች ከሆንን መንገዳቸውን መንገዳችን ማድረግ ይገባናል፡፡ በመንገዳቸው ሳንመላለስ ከገቡበት መግባት አንችልም፡፡ ዛሬ በዓለም እንደሚስተዋለው ብዙ ሰው ከሐዋርያት መንገድ አፈንግጧል፡፡ የማፈንገጣችንም ማሳያ ምክርና ትምህርታቸውን መተዋችን፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ንቀን ወደ ገዛ ፈቃዳችን ማዘንበላችን፣ በሚገጥሙን ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች ተስፋ ቆርጠን እምነታችን አንሶ ወደ ኃጢአት ተጨልጠንና ተገርኝተን መግባታችን ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ያልወጡበት የመከራ ዳገት፣ ያልወረዱበት የፈተና ቁልቁለት ያልተመላለሱበት፣ የውጣ ውረድ ሸንተረር በእውነት የለም፡፡ ስለ ክርስቶስና ስለ ፈጸሙት አገልግሎት ተሰደዋል፤ ተገርፈዋል፤ በወኅኒ ተጥለዋል፤ ሁሉን አጥተዋል፤ በክፉዎች ሸንጎ ፊት ቆመዋል፤ ሀገር ለሀገር ተንከራትተዋል፤ ታምነውባቸው በነበሩ ሰዎች ተክደዋል፤ የካዷቸውንም ታግሠዋል፤ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ጸጋ በገንዘብ ይሸጡ ዘንድ የደለሏቸውን ሰዎች ገሥጸው አሳፍረዋል:: (ሐዋ.፭፥፲፰18 ፣ ፲፮፥፲፱፣ ፰፥፲፰፣ ፪ኛቆሮ.፲፩፥፳፬-፳፰) ግርግር፣ ሁካታ፣ አጥፊ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ ግለኝነት፣ ስግብግብነት፣ ቀቢጸ ተስፋ፣ ክሕደት እንዲሁም ኑፋቄ በነገሡበት፣ ግብረ ሰዶምና ተፈጥሯዊ ማንነትን መጠየፍ ክፉዎች በክፋት መሠልጠን መቀንቀን በጀመሩበት በዚህ ዘመን የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርትና እምነት መያዝ በመንገዳቸውም መጓዝ ውስብስብ ከሆኑ ችግሮችና ዓለም ከጋረጠብን መከራ መዳኛ መንገድ ነው፡፡

ከብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!